በቻይና ሞት ስለተፈረደባት ናዝራዊት አበራ ወንድሟ ያየህይራድ ስለተፈጠረው ነገር ሲያስረዳ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

“በቻይና እስር ቤት የምትገኘው እህቴ ናዝራዊት አበራ እና እቃውን አድርሺልኝ ያለቻት ጓደኛዋ ስምረት ትውውቃቸው እሚጀምረው ገና ከሃይስኩል ጀምሮ ነው። ውሏቸው ሁሉ ወይ እኛ ቤት ወይ ተ/ሃይማኖት አካባቢ ያለው እነሱ ቤት ነበር።

ከትምህርት በኋላ ወደ ስራ አለም ሲገቡ ፤ ናዝራዊት መሃንዲስ፣ ስምረት ደሞ የአየር መንገድ ሆስተስ ሆኑ። የዛሬ 3 ወር ገደማ ናዝራዊት በኢንጅነርነት እምትሰራበት ድርጅት የፊኒሺንግ እቃዎችን እንደሚፈልግ የምታውቀው ስምረት አንድ ሃሳብ ታመጣለች።

ከኔጋ አንድ የጉብኝት ፕሮግራም ወደ ቻይና ላመቻችና አብረን ተዝናንተን እንመለስ። ከዛ ድርጅቱ እቃ ሲፈልግ ልምዱ ስላለሽ አንቺን እንዲልክሽ ሀሳብ አቅርቢ ትላታለች።

በሃሳቡ ተስማምታ አብረው ሊጓዙ ቅድመ ዝግጅቱ ሁሉ ካለቀ በኋላ ስምረት “ክፍለ ሀገር ገጠር ያለው አባቴ ስለሞተ እኔ መሄድ አልችልም። አንቺ ግን እድሉ እንዲያመልጥሽ ስለማልፈልግ መቅረት የለብሽም። እንደኔ ሆነው አገር እሚያሳዩሽ ሃሪፍ ሃሪፍ ጓደኞቼ እዛ ስላሉ ደሞ ምንም አይደብርሽም” ብላ ታሳምናታለች።

የበረራዋ ቀን እራሱ ድንገት ከምትሰራበት ቦታ አቻኩላ ጠርታ ትኬት አስቆርጣ ነው እኛ ሳንሰማ የሸኘቻት። በኋላ በስልክ ደውላ ነው “የት ጠፋች እንዳትሉ። አሁን መሄድ አለብሽ ብላኝ ጉዞ ጀምሬ ነው” ያለችን።

ሄድኩ ካለችን በኋላ ትደርሳለች ብለን ካሰብንበስ ሰዓት ጀምሮ ለ2 ቀናት ያህል ብናይ አትደውልም፣ ብናይ Online አትሆንም። ጭንቀታችን ሲበዛ ቻይና ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደወልን። ሙሉ ስሟን ከጠየቁን በኋላ ያልጠበቅነውን አስደንጋጭ ዜና አረዱን።

ይዛ በመጣችው እቃ ውስጥ አደንዛዥ እፅ ተገኝቶባት ከኤርፖርት ነው ቀጥታ ወደ እስር ቤት የተወሰደችው። በሃገሪቱ ህግ መሰረት ደግሞ ከ10 ግራም በላይ ይዞ የተገኘ ሰው የእድሜ ልክ እስራት፣ 50 ግራም ከሆነ ደሞ የሞት ፍርድ እሚያስቀጣ ወንጀል ነው። እሷም አንድ ነገር ካልተደረገላት የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃት አረዱን።

ወድያው የጓደኛ ተብዬዋ ስልክ ላይ ደጋግመን ስንደውል አላነሳ አለችን። በሂደት ስታነሳ የተፈጠረውን ነገር አስረድተናት እምታውቀው ነገር ካለ ስንጠይቃት ፤ መጀመሪያ “በምን ልትታሰር ትችላለች?” ምናምን እያለች ካቅማማች በኋላ “እዛ ያሉ ጓደኞቼ ይሄን ነገር ብታመጪ በጣም ትርፍ አለው፣ በአንዴ ትለወጪበታለሽ ብለውኝ ከብራዚል ያመጣሁትን አንድ እቃ አድርሺልኝ ብዬ ሰጥቻት ነበር። በሱ ይሆናል የተያዘችው” ብላ አመነች።

እኛም ያሉንን 3 የሰው ምስክሮችና በስልክ የቀዳናትን ይሄን ንግግር ይዘን ወደ ፖሊስ በመሄድ አመለከትን። በወቅቱ ልጅቷ ሀገር ውስጥ ስላልነበረች በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዛ እንድትታሰር ተደረገ። እሷም ለፖሊስ የእምነት ቃሏን ሰጥታ በዋስ ስለተፈታች የክስ ሂደቷን በተመላላሽ እየተከታተለች ነው።

ቻይና ስላለው ጉዳይ በተመለከተ ላለፉት 3 ወራት ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ የፊታችን አርብ ጉዳይዋ ለአቃቤ ህግ ተላልፎ ክስ እንደሚመሰረትባት ተነግሮናል።

አደንዛዥ እፁ እጇ ላይ ስለሆነ የተገኘው እና ከዚ በላይ ማስረጃም ብዙ ስለማያስፈልግ ከአንድ ግዜ በላይ ቀጠሮ ሳያበዙ ሊፈርዱባት እንደሚችሉም ሰምተናል። እናታችን ይሄንን ስትሰማ በድንጋጤ ግማሽ ሰውነቷ ፓራላይዝ ሆኖ ተቀምጣለች።

እኔና ሌሎች በርታ በርታ ያልን ቤተሰቦቿ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረግን ነው። 1ኛ~ የቻይና መንግስት እህታችንን ወደ ሀገሯ እንዲመልስልን ፒቲሽን እያሰባሰብን ነው።

2ኛ~ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መፍትሄ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው።  3ኛ~ ምናልባት በቅርቡ ደግሞ ሰልፍም አስበናል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በሚችለው ሁሉ ድጋፉን ያደርግልን ዘንድ በየዋኋ እህታችንና በበሽተኛ እናታችን ስም እንማፀናለን።

 

Share.

About Author

Leave A Reply