“በአመራር ላይ ያሉ ግለሰቦችን መልካም ፈቃድ ተቀብለን እንጂ የምንተማመንባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ስላሉ አይደለም ወደ ሚዲያው የተመለስነው” እስክንድር ነጋ ለቃሊቲ ፕሬስ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያው ምክኒያት ለእስር ተዳርጎ ከወራት በፊት የተፈታው አንጋፋው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ መመለሱን ለቃሊቲ ፕሬስ ገልጿል።

የሀገሪቱ ህግ በሚጠይቀው መስፈርት መሰረት ለአገልግሎት የሚውሉ ቢሮዎችን አራት ኪሎ አካባቢ መከራየቱንና ከሰሞኑም የሚዲያ ፈቃድ በማውጣት የመጽሄት ህትመት እንደሚጀምር አስረድቷል።

“አሁን በሀገሪቱ ውስጥ የተሻለ የዴሞክራሲ ተቋም አለ ብለን ሳይሆን በአመራር ላይ ያሉ ግለሰቦችን መልካም ፈቃድ ተከትለን ነው ዳግም ወደዚህ ሙያ የተመለስነው” በማለት የገለጸው እስክንድር ሚዲያውንና ባለሙያዎቹን የሚጠብቅ ተቋማት ሊፈጠሩ ይገባል ብሏል።

“ከዚህ ቀደም ቢሮ ለመከራየት ስንል ግለሰቦች እንደ ጦር ይፈሩን ነበር። አሁን ግን ደስ እያላቸው ነው ቤታቸውን ለጋዜጣ ቢሮነት የሚያከራዩት” በማለት በህዝብ ዘንድ የተሻለ አስተሳሰብ መስፈኑን ተናግሯል።

በሀገሪቱ ውስጥ የግል የሚዲያ ተቋማት ያሉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ለስላሳ ጉዳዮችን ብቻ በማንሳት ፖለቲካዊ እንዲሁም ጠንከር ያሉ የህዝብ ችግሮችን ለማንሳት አይደፍሩም ከዚህ አንጻር እናንተ የምትመሰርቱት አዲስ የሚዲያ ተቋም ምን ለውጥ ያመጣል በማለት ከቃሊቲ ፕሬስ የተጠየቀው እስክንድር “ሁሉም የአቅሙን ሰርቶ እዚህ ደርሷል። ሁሉም የሚችለውን አድርጓል። እኛም እነሱ በጀመሩት መንገድ ቀጥለን ለመጓዝ እና ተጨማሪ ግብአት ለመሆን ነው ሀሳባችን።” ሲል ተናግሯል።

በቅርቡም በመጽሄት ህትመት ስራውን እንደሚጀምርና በሶሻል ሚዲያም እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ከዚያም ባለፈ የሳተላይት ቴሌቪዢን ለመጀመር የአክሲዮን ማደራጀት ስራ እንደሚጀምር ተናግሯል።

 

Share.

About Author

Leave A Reply