በአማራ ክልል በቢቸና የደረሰውን ህገወጥ፣ ኢ-ሰብአዊ እና የህዝቦችን አብሮነት የሚንድ ጥቃት በግሌ እና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ስም አጥብቄ አወግዛለሁ – ኡስታዝ አብበከር አህመድ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና ህይወታቸውን ላጡ ሰዎችም የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልፃለሁ፡፡ ይህንን መሰል ጥቃቶች በክልሉ መደጋገማቸው ደግሞ ጉዳዩን በህዝቡ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች ተራ ድርጊት ብቻ አድርጎ ከመቁጠር የአመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣት የፈጠረው ጥቃትን ልማድ የማድረግ ሂደት አስመስሎታል፡፡

በተለይ ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት ብቻ በአማራ ክልል መስጂዶች እና አማኞችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡ ትናንት በቢቸና በደረሰው ጥቃትም መስጂዶች ተደፍረዋል የንፁሃን ህይወትም አልፏል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ከጥቃቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የተጠረጠሩ፣ የታሰሩ እና እርምጃ የተወሰደባቸው አካላት ስለመኖራቸውም የተነገረ ነገር የለም፡፡ ይህ የልብ ልብ የሰጣቸው አካላት ደግሞ ጥቃታቸውን በመቀጠልና በቢቸና እንደተደረገው ደግሞ ስልታቸውን እያሳደጉ በህዝቦች መካከል አብሮነትን ማደፍረስ ያለመ የሚመስል አቅጣጫ እያስያዙት የተከበሩ መሳጂዶች እና ንጹሃን አማኞች ላይ እጃቸውን በማንሳት በምንም የማይካስ ጥፋት እያደረሱ ነው፡፡

በትናንትናው ምሽት ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ እርምጃ የማይወስዱ ከሆነ “ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ናትና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል እምነት እና ብሔርን ዒላማ ያደረግ በዜጎች ላይ የሚደርስን ሞት እና መፈናቀልን ለመከላከል እንሰራለን” የሚሉ የመንግስት ኃፊዎች ንግግር ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡

ይህ በህዝቡ ዘንድ የሚታመን አመለካከት ከመሆኑ በፊት መሰል ጥቃቶች ዳግመኛ እንዳይፈፀሙ የፀጥታ ሀይሎች የአካባቢውን ማሕበረሰብ በማሳተፍ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ሂደቱንም እንደ ዜጋም ሆነ እንደ አማኝ በቅርበት የምንከታተለው ስለሚሆን የሚመለከታቸው አካላት ባለባቸው ኃላፊነት ልክ የወሰዱባቸውን እርምጃዎች ለህዝብ ይፋ እዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡

በቢቸና እና አካባቢው ለሚኖሩ የሁሉም እምነት ተከታዮች፣ የሀገርሽማግሌዎች፣ የሀይማት አባቶች እና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችም አካባቢውን ለሁሉም ነዋሪዎች ምቹ እንዲሆን ሰብአዊ እና ሀገራዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ መፍትሔ በማፈላለጉ ሂደት የማሕበረሰብ ክፍሎችን የማሳተፍ ቁርጠኛ አካሄድ ካለም የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡

ኡስታዝ አብበከር አህመድ

Share.

About Author

Leave A Reply