በአማራ ክልል የአተት በሽታ ወረርሺኝ ተከሰተ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሀገሪቱ የተከሰተውን የአተት በሽታ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር 205 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች መሰማራታቸውን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር በየነ በመግለጫቸው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምትና በየዳ ወረዳዎች እንዲሁም ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ ወረዳ 174 ሰዎች በአተት በሽታ ወረርሽኝ መጠርጠራቸውን ተናግረዋል ።

በዚህ መሰረትም በአበርገሌ ወረዳ 61 ሰዎች፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ 110 ሰዎች እና በበየዳ ወረዳ ደግሞ 4 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተጠርጥሯል ብለዋል።

በበሽታው የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው በተመለከተም እስካሁን ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ነው ዶክተር በየነ የተናገሩት ።

ከተጠቀሱት ወረዳዎች አካባቢ በሚገኙ አጎራባች ወረዳዎች ያለውን የበሽታውን ሁኔታ ኢንስቲትዩቱ ቅኝት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

በሽታውን በፍጥነት ለመቆጣጠርም ባለፉት ስድስት ሳምንታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየቱን የጠቀሱት ዶክተር በየነ፥ አሁን ላይም ከፌዴራል፣ ክልልና ዞን የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ወደ አካባቢዎቹ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል ።

ከዚህ ባለፈም በሽታውን ለመቆጣጠር እና በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ለሚደረግ የጤና አገልግሎት 74 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ወጪ መደርጉን አንስተዋል።

በተጨማሪም 205 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሰማራት የተለያዩ አገልግሎችን እየሰጡ መሆናቸውን ነው ጠቆሙት ።

ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለው የመንገድና የስልክ ኔትወርክ ችግር ባለሙያዎች በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት ማስተጓጎሉ ነው የተገለፀው።

ህብረተሰቡ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶክተር በየነ፥ የመፀዳጃ ቤት በመስራት እና በአግባቡ በመጠቀም፣ የመመገቢያ፣ የመጠጫ እና የውሃ ማስቀመጫ እቃዎችን በንጹህ ውሃ በማጠብ ፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስ እና ሕፃናትን ካፀዳዱ በኋላ እጅን በመታጠብ፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ በመመገብ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል አሳስበዋል ።

fana

Share.

About Author

Leave A Reply