በአርባ ምንጭ አንገት ያስደፋው ክስተት (ዳንኤል ሺበሺ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 2ቀን፡ 2010 ዓም በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝቼ ለሕዝቡ ንግግር እንዳደርግ ተጋብዤ ነበር፡፡ ወደፊት በስፋት የምመለሰው ሲሆን፤ ለአሁን የገረመኝን ነገር ላካፍላችሁ፡፡

በጎኔ የደቡብ ክልል መንግሥትን ወክለው የተገኙ የደቡብ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ሊ/ር አቶ ኢሳያስ እንድርያስ፤ ምክትላቸው አቶ ለማ ፖሎ እና የከተማው ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማኮ ነበሩ፡፡ ሁሉም ለሕዝቡ መለዕክት ለማስተላለፍ እንደተገኙ ተረድችያለሁ፡፡

በቅድሚያ ወደ መድረክ የዞኑ ሊ/ር ተጋበዙ፡፡ ወዲያው ሕዝቡ እየተቀባበለ “ሌባ ሌባ ! ሌባ! አንሰማችሁም፤ የቀን ጅቦች! ሳትዋረዱ ስቴዲየሙን ለቃችሁ ውጡ!! የሚል ጩሄት ተቃውሞና ፉጨት እየተጋጋለ መጣ፡፡

የሕዝቡን ተቃውሞ እንዳበርድ ተጠየኩ፡፡ እሺ ብዬ ሕዝቡን በድምጸ-ማጉያ ለመንኩት፤ በፈጹም! አንሰማቸውም በማለት በምልክትና በድምፅ ተቃውሞ ቀጠለ፤ እኔም ለአፍታ ቆም ብዬ ሁኔታውን በመከታተል ላይ እያለሁ “ዳኒ ስንጠብቅህ አቢይን ይዘህ መጣህ” “እንወድሃለን! የኛ ጀግና አንተ ተናገር እኛም እንሰማሃለን” የሚል ግጥም እዛው ተገጥሞና ወደ ውዳሴ ሙዝቃነት ተቀየረ፡፡ እኔም ሕዝቤን ፈቃድ አክብሬ በ3ገፅ ያዘጋጀሁትን ንግግሬን በታላቅ ጭብጨባና ክብር አጠናቀኩ፡፡

በሕዝቡ ቁጣ ምክንያት ቀድሞ የተጋበዘው የዞኑ ሊ/ር አንድት ቃል ሳይተነፍስ በመጣበት እየተበሳጨ ሲመለስ ሌሎችም እየተበሳጩ ተከተሏቸው፡፡ “እኛ የማንናገር ከሆነ፤ የእነሱም እንግዳም አይናገርም! በቃ! ሰልፉ ይበተን አለ አንዱ በመልክ የማውቀው ካድሬ ቁጣ እየተናነቀው፡፡ ከመድረክ ተባርረውና ወጥተው አንገታቸው አቀርቅረው ወጡ፡፡ እነርሱ ስቴዲየሙን ለቀው ሲወጡ ሌላ ቡጢ ተከተላቸው፤ “የአርባምንጭ ሕዝብ ጨዋ ነው፤ ባለጌዎችን እንጂ የጨዋዎች አክባሪ ነው” የሚል ሲንኝ ከመቸው ተገጥሞና ተጠንተው የሕዝብ ዜማ እንደሆነ ባላውቅም በከፍተኛ ድምፅ ተከተላቸው፡፡

ወገን ሆይ! ሁሌም እንደምለው ዛሬም እላለሁ <ሕዝብ ታላቅ ነው፡፡>

ሌላው የገረመኝ ነገር የእነርሱ መባረር ሳይሆን፤ አንዱ #ኮማንደር የተናገረውና በጆሮዬ የሰማሁት ነው፡፡ “በቃ ይህ ሕዝብ እናንተን ለመስማት ፍጹም አይፈለግምና ለምን ለቃችሁ አትወጡላቸውም? አንድ ችግር ቢፈጠር ኃላፊነቱ የእናንተ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ የሚትቋቋሙበት ጉልበት ካላችሁ መቀጠል ትችላላችሁ” በማለት ገፍተር ገፍተር እያረጋቸው በቁጣ ያስጠነቀቀበት ሁኔታ በጣም አስደምሞኛል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በሰልፉ ላይ የነበሩ ፀጥታ ሰራተኞችን ማመስገን ግድ ይለኛል፡፡ ከመቸውም ጊዜ በላይ የሙያ ሥነ-ሥርዓትንና ኃላፊነትን የተወጡ ይመስለኛል፡፡ ነገረ ሥራቸው በተወሰነ መልኩ 1997 ዓም አስታውሰውኛል፡፡ ብዙዎቹ በምልክት ቋንቋም ጭምር አድንቀውናል፡፡ ገምሶቹ እቅፍ አድርገው ስመውኛል፡፡ እውነታው ይህ ነው ፡፡ ሰላም!

 

Share.

About Author

Leave A Reply