“በአንዳርጋቸው እግር ስር ወድቄ ረጅም ሠዐት መነሳት ተስኖኝ ነበር” እየሩሳሌም ተስፋው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግዮን፡- በግንቦት ሰባት ታስራችሁ ከረጅም ጊዜ እስር በኋላ ስትፈቱ የክሳችሁ ዋና መነሻ የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ በወቅቱ አለመፈታቱን ስታውቁ ምን ተሰማሽ?

እየሩሳሌም፡- እኔ እስሬን ጨርሼ ነው እንጂ የወጣሁት በምህረቱ አይደለም:: እኔ ከመውጣቴ አንድ ወር በፊት ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይለቀቃሉ የሚለውን ነገር ሰምቻለሁ:: በፍጹም አዕምሮዬ ውስጥ አንዳርጋቸው ይወጣል የሚል እምነት መቼም አልነበረኝም:: አሁን ስወጣ ሳየው ነው ያረጋገጥኩት እንጂ እስከመጨረሻው ሠዐት እምነቱ አልነበረኝም::

ግዮን፡- ለምንድን ነው አይፈታም ብለሽ ያመንሽው? እየሩሳሌም፡- ምክንያቱም አንደኛ ብዙ ወጪ አውጥተው የያዙት ሰው ነው:: ያንን ወጪ ሲያወጡ ደግሞ ለድርጅቱ ቁልፍ ሰው መሆኑን ያውቃሉ::

አንዳርጋቸውን ሲይዙት እንደ ግለሰብ ሳይሆን ድርጅቱን እናሽመድምደዋለን ብለው ነው አስበው የያዙት:: ግንቦት ሰባትን እንደዛ እያሰቡት አንዳርጋቸውን ይፈቱታል ብየ አላሰብኩም ነበር::

ግዮን፡- አንዳርጋቸው እንደሚፈታ ሰምታችሁ፤ ኮሚቴ አዋቅራችሁ ለአቀባበሉ ስትዘጋጁ ነበር:: ከቅዳሜ ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ድረስ ፍቺው ሲዘገይ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ?

እየሩሳሌም፡- ተሰብስበን ስንነጋገር ሁላችንም ውስጥ የነበረው አንዳርጋቸው መጥቶ ከእኛ ጋር ይሆናል ብለን ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ ለአንዳርጋቸው ጥሩ አመለካከት እንዳለውና ፍርሀቱን መስበር እንደሚችል አባቱ ቤት መጥቶ አሳይቷል:: አንዳርጋቸው እንደሚፈታ ማመን ጀምሬ ቢሆንም እንደኔ ኢትዮጵያ ህዝብ መሀል ይቀላቅሉታል ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ እንግሊዝ ይልኩታል ብዬ ነው ያሰብኩት:: ቢልኩትም ግን ህዝቡ አባቱ ቤት መጥቶ ቤተሠቡን “እናመሠግናለን” እንዲል እና ለአንዳርጋቸው ያለውን ክብርና ፍቅር እንዲገልጽ ነው ጫና ስናደርግ የነበረው:: በነጋ ቁጥር የማስበው መፈታቱን፤ በሆነ ቀን ይለቁታል የሚለውን እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አልነበረም::

ግዮን፡- የአንዳርጋቸው ድርጅት አመለካከትና የአቋም ጥንካሬ ደግፈሽ፤ ከመደገፍም አልፈሽ በርሃ ድረስ ትግሉን ለመቀላቀል መንገድ ጀምረሽ ነበርና፤ አይተሸው የማታውቂውን አንዳርጋቸው የተፈታ ዕለት በአካል ስታይው ምን ተሰማሽ?

እየሩሳሌም፡- አንዳርጋቸውን ማወቅ የጀመርኩት “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ” የሚለውን መጽሐፉን ካነበብኩኝ በኋላ ነው:: ከዛ ቀጥሎ የእርሱን ቃለ መጠይቆችና ንግግሮች እየተከታተልኩኝ ማየት ጀመርኩኝ:: አንዳርጋቸው ታሠረ ሲባል እኔን በሕይወቴ እንደዛ ቀን አዝኜ የማውቅበት ቀን እስካሁን ድረስ የለም:: የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀዘን ቢሆንም በጣም ነበር ያዘንኩት:: ቃሊቲ እያለን እኛ ፊት ለፊት ነበር የታሰረው:: ብዙ ጊዜ በቀዳዳ እያሾለኩ እርሱን ለማየት እጥር ነበር:: ሁሌ ከታሰረበት ክፍል የሚያስወጡት ቅዳሜ 8ሠዐት ስለሆነ እርሱ ሲወጣ ለማየት ሁሌም እጥር ነበር አልተሳካልኝም:: የሁልጊዜ ህልሜ አንዳርጋቸውን ማየት ሆኖ ሳለ ባልገደሉትና ይሄን ያህል ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ ሽምግልና መሠዋዕት የከፈለበትን ትግል ቢያይ ሁሌ እመኝ ነበር:: ያንን ፕሮግራም ስናዘጋጅ እንኳ አንዳርጋቸውን አየዋለሁ የሚል እምነት የለኝም ነበር:: ልክ አንዳርጋቸውን የያዘ መኪና ሲመጣ መጀመሪያ ያገኘነው እኛ ነበርን:: እጁን ሳምኩት፤ እስከሆነ ሠዐት ድረስ ራሴን አላውቅም ነበር:: ከመኪና አውጥተን እቤት አስገባነው:: እግሩ ስር ወድቄ ረጅም ሠዐት መነሳት ተስኖኝ ነበር:: እኔንጃ በጣም ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ስለተሳማኝ አስር ጊዜ እጁን እስመው ነበር:: ይሆናል ብለህ የማታስበው ነገር ሆኖ ሲታየው በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው አጠገቤ ሆኖ ሳገኘው፣ ሳየውና ስዳብሰው በጣም ከባድ ነበር::

ግዮን፡- ከአንዳርጋቸው ጽናት ጥንካሬ ምንድነው የምትማሪው?

እየሩሳሌም፡- ተስፋ አለመቁረጥን ነው:: ከተፈታ ሠዐት ጀምሮ እያለ ያለው ነገር አሁንም ወደ ኋላ እንደማይመለስ ነው:: መቶ ዓመት ቢሆኝ እንኳ ጥያቄአችን እስካልተመለሰ ድረስ ወደ ኋላ አልልም ሲል ነበር:: በምንም አይነት ሂደት ወይም መስዋዕትነት ውስጥ ዋጋ እየተከፈለም ቢሆን ጥያቄው እስካልተመለሰ ድረስ ምንም ነገር ሊገድበን እንደማይችል አስተምሮናል:: አንዳርጋቸው መጀመሪያ ከእነሱ ጋር ስልጣን ውስጥ ነበር ያ ሳይሆን ሲቀር እንግሊዝ ገባ:: በተደጋጋሚ በሠላማዊ መንገድ ቢታገልም ያለመለት ዓላማ ሊሳካ ስላልቻለ ድርጅት መስርቶ በርሀ ገባ፣ ታሠረ:: ሲፈታ የሁላችንም ግምት ወደ ትግሉ ይመለስ ይሆን? የሚል ነበር:: አሁንም ግን አንዳርጋቸው ጽኑ ነው፤ የማይበገር ብረት ነው:: የዓላማና የመርህ ሰው መሆንን ነው ከአንዳርጋቸው የተማርኩት::

 

ግዮን፡- ወደ ኋላ ልመልስሽና ወደ ትጥቅ ትግል ስትሄጅ የተያዝሽበት ቀን እና እንዴት እንደተያዝሽ በአጭሩ ግለጭልኝ::

እየሩሳሌም፡- ማይካንድራ የሚባል ኢትዮ ሱዳን ድንበር ላይ ነው የተያዝነውና፤ ስንደርስ እንደምንያዝ ባውቅም ስንያዝ በጣም ደንግጬ ነበር:: ከዚህ የሄድነውን እኔን ጨምሮ፣ ብርሃኑንና ፍቅርማርያምን ያውቁናል ያን ያህል የሠራዊት ኃይል ለኛ ምን ያደርጋል? በጣም ብዙ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ደህንነቶችና ወታደሮች፤ አየር ወለድ ቡድን ሁሉ ሳይቀር ነው ከበባ የተደረገብን:: በጣም ከመደንገጤ የተነሳ “እጅ ወደላይ” ሲባል እንኳ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር::

ግዮን፡- ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ አንዳርጋቸው ተፈቶ ግንቦት 22 ቀን 2010ዓ.ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ተገናኝቷል:: አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ ለዓመታት ካሠረች ሀገር መሪ ጋር መገናኘት ምን አይነት ስሜት ፈጠረብሽ?

እየሩሳሌም፡- እጠብቅ ነበር:: በሆነ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያናግሩታል ብየ አስብ ነበር:: ዶ/ር ዐብይ እስካሁን ሲያደርግ ከነበረው ነገር አንፃር ቀና ሰው፤ ውስጣዊ መልካምነት ያለው ነው ብየ አስባለሁ በራሴ:: በመገናኘታቸው ደስ ብሎኛል:: አሸባሪ ብለው፤ ብዙ ገንዘብ አባክነው፤ ከሰው ሀገር ድረስ ሄደው አፍነው አምጥተው፤ በእነ መለስ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የማይታሰብ እና ሊሆን የማይችል ነበር:: ያሁሉ ነገር ተቀርፎ በክብር ቤተመንግስት ገብቶ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋራ ስናየው ሁሉም የተሰማውን ስሜት ተሰምቶኛል::

ግዮን፡- የኢትጵያ የፖለቲካ ምህዳር፤ ፖለቲከኞች ከእስር መፈታትን ተከትሎ ሠፍቷል ማለት ይቻላል?

እየሩሳሌም፡- ምህዳሩ ሠፍቷል ማለት አይቻልም:: አንዳንድ መልካም ሂደቶች አሉ አንዳርጋቸው ተፈቷል፤ ቤተመንግስት ሄዶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝቷል:: ግን ዐብይ በራሱ ፍላጎት ነው ያን ያደረገው ለማለት ይከብደኛል:: ምክንያቱም ቅድሚያ ሊሠሩ የሚችሉ፤ ለምሣሌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አልሰረዘም:: እንደ ዐብይ ግን ይሰርዘዋል ብየ አላስብም ነበር:: እስካሁን እንዳይሰርዝ ያደረገው የሆነ ነገር አለ ማለት ነው:: ሌሎች ነገሮችም እንደዛው በመሆናቸው የፖለቲካ ምህዳሩ ሠፍቷል ብዬ አላስብም:: ግን ጥሩ ጅማሬ ነው ማለት ይቻላል::

ግዮን፡- የእነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የጀዋር መሀመድ እንዲሁም የኢሳትና የኦ ኤም ኤን ክስ መቋረጥን እንዴት ታየዋለሽ?

እየሩሳሌም፡- ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ ስናነሳ ጥሩ ጅማሬ ነው ከምንለው አንደኛው ይሄ ጉዳይ ነው:: ምናልባት ግንቦት ሰባትና ሌሎቹ “አሸባሪ ድርጅቶች አይደሉም” ብሎ ከሽብር ክስ ነፃ ማድረጉ የመጀመሪያ መልካም እርምጃ ሊሆን ይችላል::

ግዮን፡- በመጨረሻ ቀረ የምትይው ወይም ማስተላለፍ የምትፈልጊው ነገር ካለ?

እየሩሳሌም፡- የማስተላልፈው መልዕክት እኔ ከእስር ከወጣሁ በኋላ ዘመቻ አድርገን ነበር:: ከዚያ በፊትም ብዙ ዘመቻዎች ነበሩ፤ አሉም:: ከዘመቻው ጀምሮ አንዳርጋቸው እንዲፈታ ጥረት ያደረጉ ሰዎች፤ የአቀባበል ፕሮግራሙ የደመቀና ታሪካዊ እንዲሆን ያደረጉ በሀገር ውስጥም፤ በውጭም ያሉ ሰዎችን በአጠቃላይ በአንዳርጋቸው ስም ከልብ አመሰግናለሁ::

Share.

About Author

Leave A Reply