በኢትዮጵያ ሕግ ተፈጻሚ የማይሆን ቅጣት ተወስኖብናል ያሉ እስረኞች አቤቱታ አቀረቡ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በተለይም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ ለፖሊስ በሰጡት ቃል ብቻ ሞትና በኢትዮጵያ ሕግ ተፈጻሚ የማይሆን የ80 ዓመታት ቅጣት ተወስኖብናል ያሉ እስረኞች አቤቱታ አቀረቡ፡፡

በማረሚያ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ያረፈባቸው፣ ክስ ተመሥርቶባቸው እየተከራከሩ የሚገኙና በተጠረጠሩበት ወንጀል የጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ በሐሰት ክስ ያለማስረጃና ያለምንም ጥፋት ተፈርዶባቸው ታስረው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ታሳሪዎቹ ብሶታቸውንና አቤቱታቸውን ያሰሙት ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ማረሚያ ቤቱን ለጎበኙት፣ በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለተሾሙት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና አቶ ሰለሞን አረዳ ነው፡፡

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ፍርድ ያረፈባቸው፣ ክሳቸው የቀጠለና በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሴት ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያን፣ ቻይናውያንና የሌሎች አገሮች ዜጎች ይገኛሉ፡፡ ከወንዶች ኢትዮጵያውያን ጋር በርካታ የኬንያ፣ የናይጄሪያ፣ የጂቡቲና የተለያዩ አገር ዜጎችም ተካተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቶቹና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ዋና ዓቃቤ ሕግና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እስረኞቹን በጎበኙበት ወቅት ለታራሚዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎች አቅርበውላቸዋል፡፡ በምን ዓይነት ወንጀል እንደተፈረደባቸው፣ ስንት ዓመት እንደተፈረደባቸውና ስንት ዓመት እንደቀራቸውና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ታሳሪዎች ሰጥተዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሲገቡ ነፍሰጡር የነበሩ ወልደው እያሳደጉ መሆኑን፣ አንዲት እናት በቀላል የወንጀል ድርጊት ከሦስት ልጆቻቸው ጋር የታሰሩ መሆናቸውን፣ ያለምንም የወንጀል ድርጊት በሐሰተኛ ምስክርና ማስረጃ ሞት እንደተረፈደባቸው፣ ደረቅ ቼክ የፈረመው እያለ ለሌላ ሰው ሰጥታችኋል ተብለው የታሰሩ መሆናቸውን፣ ፖሊስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27 መሠረት በሰጡት ቃል ብቻ ሞት እንደተፈረደባቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ ሕግ የመቅጫ ጣሪያ 25 ዓመታት መሆኑ እየታወቀ 80 ዓመታት እንደተፈረደባቸውና ሌሎችንም ምላሾች ሰጥተዋል፡፡ ታራሚዎቹ በደረቅ ቼክ፣ ሰው በመግደል፣ ሰነድ ላይ በመፈረም፣ በስርቆት፣ በሐሺሽ ዝውውር፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ አሲድ በመድፋት፣ ከመሬት ጋር በተያያዙና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች እንደተፈረደባቸው ተናግረዋል፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ከሦስት ዓመታት በላይ እየተመላለሰች የምትገኝ ታሳሪ ደግሞ የባንክ ሠራተኛ መሆኗን ተናግራ፣ ቢፈረድባትም ከዚህ በላይ እንደማይሆንና ፍትሕ ማጣቷን አስረድታለች፡፡

‹‹የዋልድባ ገዳም አባል ነህ›› ተብሎ በሽብርተኛነት ተጠርጥሮ ከተያዘ 11 ዓመታት ቢሆነውም ፖሊስ ጣቢያም ሆነ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደማያውቅ የተናገረው መምህር ዘካሪያስ ገብረ ፃዲቅ ደግሞ፣ ‹‹ጥፋቴ ምንድነው?›› በማለት ጠይቋል፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስና ሌላም ሕመም ያለባቸው ታራሚዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ መንግሥት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጉብኝት ያደረጉት ኃላፊዎች በየታሳሪዎቹ ክፍል ገብተው ጉብኝታቸውን እንደጨረሱ ከየዞኑ የተውጣጡ ተወካዮችን በስብሰባ አዳራሽ አነጋግረዋል፡፡ የዞን አንድ ተወካይ በእነሱ ዞን የተፈረደባቸው ግለሰቦች ወንጀል የፈጸሙ ሳይሆኑ፣ በዓቃቤ ሕግ የውሸት ክስ የተፈረደባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሲከራከሩ የሚሰማው የዓቃቤ ሕግ ብቻ መሆኑን፣ ጥፋተኛ ሲባሉ ማቅለያ እንደማይያዝላቸው፣ በይቅርታ፣ በምሕረትና ክስ በማቋረጥ ከእስር የሚፈቱ ሰዎች ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርት እንደሚያውቁትና አምስት ዓመት የሚቀረው ሲፈታ ወራት የቀሩት ታስሮ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አራቱ ሊቃነ መናብርት በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው የገቡት ቃል ለእነሱ ለምን እንዳልተከበረላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በርካታ ተቋማትን እየጎበኙና መፍትሔ እየሰጡ መሆኑንና ውጭ አገር ሄደው እስረኞችን አስፈትተው እየመጡ ለምን እነሱን እንዳልፈቱ ጠይቀው፣ ይቅርታ ቢደረግላቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው በልማት እንደሚክሱ አስረድተዋል፡፡ ሞት የተፈረደባቸው በ12 ዓመታቸው በይቅርታ ሲፈቱ፣ 25 ዓመታትና ዕድሜ ልክ የተፈረደባቸው ግን ታስረው እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ሕጉም ሆነ ሕገ መንግሥቱ ፍርደኛ በቤተሰቡ አካባቢ እንዲታሰር የደነገገ ቢሆንም፣ በክልል ተፈርዶባቸው አዲስ አበባ በመታሰራቸው በችግር ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የተፈረደባቸው ‹‹ቀኑና ወሩ ባልታወቀበት ጊዜ በፈጸሙት ወንጀል›› በሚል የዓቃቤ ሕግ ክስ እንዴት ሰው ዕድሜ ልክ፣ ሞትና 25 ዓመታት ፍርድ ይሰጣል?›› ያሉ ታራሚ፣ ሕጉን ያባላሸው የፍትሕ አካሉ ፍርድ ቤት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአንድ ክስ የሚጠቃለልን ሀተታ 30 ክስ በማድረግ ሲቀርብለት፣ ፍርድ ቤት እንዳለ ተቀብሎ መፍረድ እንጂ ሕግ እየተረጎመ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተለያዩ ክሶች፣ በተለያዩ መዝገቦች በአንድ ተከሳሽ ላይ ሲቀርቡ ‹‹ይጣመርልኝ›› ሲባሉ ለየብቻ በመፍረድ ከሕጉ ድንጋጌ ውጪ ከ25 ዓመታት በላይ እስራታቸውን እየፈጸሙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአንድ መዝገብ ሁለት አፈጻጸም በመምጣቱ መፍታት አቅቷቸው ታራሚ ከተፈረደበት በላይ እየታሰረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፊርማቸው በፎረንሲክ ተመርምሮ የእነሱ አለመሆኑ ቢረጋገጥም፣ ‹‹ተሰርዟል›› እየተባሉ መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም ዞኖች (ስምንት ዞኖች) የተወከሉ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተው ሁሉም መንግሥት በምሕረት፣ በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ከእስር እንዲፈታቸውና እንዲደመሩ ጠይቀዋል፡፡

በተለይ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቆርቆሮ በቆርቆሮ በመሆኑ ሲሞቅ ግለቱ፣ ሲበርድ ቅዝቃዜው አስቸጋሪ መሆኑን፣ ለሕፃናት ማቆያ ትምህርት ቤት እንደሌለውና በማረሚያ ቤቱ ለአንድ ታራሚ በቀን የተያዘው 15 ብር በጀት በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ከአምስት ወራት ወዲህ ጥፍር ነቀላ መቆሙን፣ ነገር ግን ጨለማ ቤት ቀርቶ በማግለያ ቤት መተካቱን፣ እንደ አጠቃላይ ግን አዲስ የተሾሙት አስተዳዳሪዎች ጥሩ መሆናቸውንና መሻሻሎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ታራሚዎቹ ዘርዘርና ሰፋ ያሉ አስተያየቶችና አቤቱታቸውን ካሰሙ በኋላ ወ/ሮ መዓዛና ሌሎቹም ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥራ ስትጀምሩ በማረሚያ ቤት ጉብኝት በማድረግ መጀመር አለባችሁ ብለው በመከሩን መሠረት ነው የመጣነው፤›› በማለት ንግግር የጀመሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ የፍትሕ ችግር ከጥንት ጀምሮ የነበረና የቀጠለ በመሆኑ፣ በሁለትና ሦስት ወራት መፍታት ቢያስቸግርም በሒደት ግን እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ ለውጥ ለማምጣት በቆራጥነት እየሠሩ መሆናቸውንና ከታራሚዎቹ የሚጠይቁት ትዕግሥት ብቻ መሆኑን አክለዋል፡፡ ለ40 ዓመታት የተጠራቀመ ችግር በመሆኑ ጊዜ እንደሚፈልግ፣ ነገር ግን ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ የተከሰሱና የተጠረጠሩ ሰዎች አፋጣኝ ፍትሕ ማግኘት ስላለባቸው፣ በቀጠሮ ረዥም ጊዜ መቆየታቸው ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ሦስት ዓመታት መቆየት ተገቢ ባለመሆኑ በአፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኙ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡ የምሕረትና የይቅርታ አሰጣጥን በሚመለከት ሕጉን ዓይተው በሕጉ መሠረት እንዲፈታ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

ከቀትር በኋላ በርካታ ተጠርጣሪዎች በሚገኙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉብኝታቸውን የቀጠሉት ኃላፊዎቹ፣ ከተጠርጣሪዎቹ በርካታ ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ ያለማስረጃ መታሰራቸውንና ከወር በላይ በቀጠሮ ሲመላለሱ ቆይተው፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወደ ፌዴራል ፖሊስ በመዛወር ምርመራቸው እንደገና እንደሚጀመር፣ በጨለማ ቤት እንደሚታሰሩ፣ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት እንደማይችሉና ሌሎችንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚደርስባቸው ለኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ ኃላፊዎቹም እንደሚነጋገሩበትና መፍትሔ እንደሚሰጡ በማስረዳት ጉብኝቱ ተጠቃሏል፡፡

በዚህ ጉብኝት ወቅት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ አብረዋቸው ከታሰሩ ግለሰቦች ጋር ተጎብኝተዋል፡፡ አቶ አብዲ ፍርድ ቤት ከሚናገሩት በተለየ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለወ/ሮ በመዓዛና ለኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

(ታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር)

Share.

About Author

Leave A Reply