በኢትዮጵያ የሚገነቡ ስነ-ህንፃዎች አብዛኞቹ አገራዊ መገለጫነት የላቸውም – ዶክተር ሂሩት ካሳው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በኢትዮጵያ የሚገነቡ ስነ-ህንፃዎች አብዛኞቹ አገራዊ መገለጫነት የሌላቸው መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።
የባህልና ቱሪዝና ሚኒስቴር በቱሪዝም ልማት በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ በዘርፉ ከተሰማሩ አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ጋር ዛሬ ግንቦት 06 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአለምን ቀልብ መሳብ የሚቻለው የሚገነቡ ስነ ህንፃዎች እንዲሁም ቅርሶቻችን “ኢትዮጵያዊ መልክ ሲኖራቸውና እኛነታችንን ሲያንጸባርቁ ነው” ብለዋል።

በዚህም አለም ኢትዮጵያን እንዲከባት ከተፈለገ ከታች ጀምሮ ያሉ ቁሳዊና መንፈሳዊ የባህል ሃብቶቻችን አገራዊ መልክ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም በስነ ህንጻዎች ውስጥ የተደበቀ ታሪክ፣ ማንነትና መስህብ ስላለ ሲገነቡ አገራዊ መገለጫነትን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው የህንጻ አሰራር በአብኛው የምዕራባውያንን፣ የመካከለኛውና ደቡብ ምስራቅ እስያ የህንጻ ጥበብ የሚስተዋልበት ነው።

ምንም እንኳን ዘመናዊነቱ ጥበባችን አለም የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱ መልካም ቢሆንም አገር በቀል የሆነውን ጥበብም መልቀቅ እንደሌለበት ያምናሉ።
የአገሪቱን ባህልና ማንነት ሊያንጸባርቁ የሚችሉ ብሎም ብዙ የሚነገርላቸውና የሚተረክላቸውን ስነ ህንጻዎች መስራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
“ትውልድን ማስተማር የሚቻለው በታሪክ ብቻ ሳይሆን በምንሰራቸው የስነ ህንጻ ጥበባትም ጭምር ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚሰሩ ስነ ህንጻዎች ከስያሜያቸው ጀምሮ ባህላችንን የሚገልጡ፣ ከማንነታችን የሚነሱ፣ ትውልድን የሚያስተሳስሩ ቢሆኑ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህ ረገድ በተለይ አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ስነ ህንጻዎች የኢትዮጵያን አሻራና የማንነት መገለጫ የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አርክቴክቶችና መሃንዲሶችም እንደ አገር የሚሰሩ የስነ ህንጻ ስራዎችን የዲዛይን ውድድር በማድረግና እውቅና በመስጠት አገራዊ ቅርጽ እንዲይዙ ተደርገው እንዲሰሩ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ስነ ህንጻዎች የአገርን ታሪክና ባህል ሳይለቁ ዘመናዊ ሆነው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ ያላቸውን እውቀት በመጠቀም አሻራቸውን ለማሳረፍ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Share.

About Author

Leave A Reply