በኤርትራ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ የኦነግ አባላት በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በኤርትራ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ የኦነግ አባላት በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተገልጿል።

በዚሁ ቀን ለግንባሩ አመራሮችም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ነው የተገለጸው።

ከ1300 ስስከ 1500 ያህል ታጣቂዎቹ ነገ ጠዋት በዛላንበሳ በኩል የሚገቡ ሲሆን፥ በአዲግራት ህዝብ አቀባበልና የቁርስ ፕሮግራም እንደሚኖራቸው በትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽ አቅም ግንባታ ሃላፊ የሆኑት አቶ ወልደ ገብረኤል አስገዶም ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ በተመሳሳይ መልኩ በመቀሌ ከተማም አቀባበልና የምሳ ፕሮግራም እንደሚኖራቸውም አቶ ወልደ ገብሬኤል ገልጸዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክሎች በተለያዩ ከተሞች አቀባበል እንደሚደረግላቸውና ወደ ስልጠና ካንፖች አንደሚገቡም ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ጎን ለጎን አስመራ ከሚገኙ የኦነግ አመራሮች ጋር ወደ ሀገር ቤት በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና ከኦሮምያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ጋር በአስመራ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ግንባሩም ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ልዑካኑን ልኮ ከመንግስት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱም ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply