በደቡብ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት ከአሥር በላይ ሰዎች ሞቱ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦታው ተገኝተው ማኅበረሰቡን ሊያነጋግሩ ነው

በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት ከአሥር በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ ዘጠኝ ሰዎች ከባድ፣ ከ80 በላይ ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከ3,000 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውንና ንብረቶችም መውደማቸውን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ የጠፋው የንብረት ግምትና ዝርዝር መረጃው ባይታወቅም ከፍተኛ ግምት እንዳለው ግን ገልጸዋል፡፡ እጅግ በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረው ግጭት በአገር ሽማግሌዎች፣ በፌዴራልና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሊረግብ መቻሉንም አክለዋል፡፡

በክልሉ ከሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በወልቂጤ ከተማ በእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት፣ ወደ ወላይታ ሶዶና ወደ ሲዳማ ማኅበረሰቦች ተዛምቶ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በማስከተሉ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

በተለይ የሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› በሐዋሳ በመከበር ላይ እያለና 1439ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሚከበርበት ዕለት በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉ፣ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙና ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገቢ አለመሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ በአካባቢዎቹ ተገኝተው ማኅበረሰቡን እስከሚያነጋግሩ ድረስ በአካባቢው የተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃና ክልከላ እንዲያደርጉ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር እንዳትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች የክልሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚታወቁበትን የፍቅርና አብሮነት የሚያደፈርስ፣ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጭና የሚያለያይ ተግባር ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲገነዘበው አሳስበዋል፡፡

በዚህ ሳምንት ውስጥ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ ተገኝተው ከማኅበረሰቡ ጋር ለመነጋገር ዕቅድ መያዛቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያነሳውን ጥያቄ ለመስማትና አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ ለመስጠት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ሌላውን ወገን በመግፋት፣ በመግደልና በማቁሰል የሚገኝ ነገር እንደሌለ የአካባቢውም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሰላም ሁሉም ወገኖች ትርጉም እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ ማንኛውም ጥያቄና ማንኛውም ፍላጎትና ልማት ወደሚፈለገው መንገድ ሊያደርስ ቢችልም፣ ወደ ሰላም ሊያመጣ ስለማይችል በረብሻና በግጭትም የሚመለስ ጥያቄ እንደማይኖር ማኅበረሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የክልል ጥያቄ እንዳለ መስማታቸውን የገለጹትት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንኳን የክልል ጥያቄ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል በሕገ መንግሥቱ መፈቀዱን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በብልህነት፣ በመደማመጥና በመግባባት መወያየት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡ ‹‹መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መገንዘብ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ የተደረገው የወሰን አከላለል ያስገኘው ጥቅም ቢኖርም፣ በወሰን ጉዳይ ግን በሁሉም ክልሎች ጥያቄው የሚነሳ መሆኑን፣ ሕዝቡ ሊገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር ግን አንዱ ክልል ከሌላው ክልል የሚለይበት የድንበር ወሰን የለውም፤›› ብለው፣ ‹‹ያለው የአስተዳደር ወሰን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ሲኖር አንደኛውን ሥፍራን ከሌላኛው ሥፍራ የሚለይበት ሰው ሠራሽ (አርቲፊሻል) የሆነና ለአስተዳደር ጉዳይ እንዲጠቅም ተደርጎ የተሠራ እንጂ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ መቀመጡንም አስረድተዋል፡፡ ድፍን አፍሪካ አብረን እንሥራ እያለ በሚናገርበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሄዶ እንዳይሠራ ወይም እንዳይኖር ማድረግ በጣም ኋላ ቀርና አሳፋሪም መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የክልል ጥያቄ በተናጠል አንድ አካባቢ ብቻ የሚነሳ ሳይሆን በድፍን ኢትዮጵያ ያለ ችግርና ጥያቄ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ላለፉት 27 ዓመታት የክልል አወሳሰን ‹‹ምን አስገኘለን? ምንስ አሳጣን? ምን ችግርስ አመጣ?›› የሚለውን ለማወቅ ከሁሉም ወገን የተውጣጣ ጠንከር ያለ ኮሚሽን አቋቁሞ ለማጥናት ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ክልል ‹‹ተወስዶብኛል›› እንጂ ‹‹ወስጃለሁ የሚል የለም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሲዳማ ጥያቄ ቢመለስ የወልቂጤ ጥያቄ መኖሩን፣ የወልቂጤ ቢመለስ የኦሮሚያ፣ የኦሮሚያ ቢመለስ የአማራ፣ የአማራ ቢመለስ የትግራይ ጥያቄ ስለሚኖር፣ መፍትሔው በአገር ደረጃ ከወሰን አከላለል ‹‹ምን አገኘን? ምን አጣን?›› የሚለውን በዕውቀት፣ በጥበብና በጥናት ምላሽ በመስጠት ለዘመናት አብሮ የሚወስድ መንገድ መከተል የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ክልሌ ተወስዶብኛል በሚል በሶማሌና በኦሮሚያ፣ በኦሮሚያና በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአማራ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ችግሮችና ጥያቄዎች መኖራቸው በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡

ጥያቄ ያላቸው ክልሎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለሚቋቋመው ኮሚሽን ሲያቀርቡ፣ ኮሚሽኑ በአገር ደረጃ የተሠራውን ሥራ ገምግሞ ጥቅምና ጉዳቱን ከለየ በኋላ ጉዳቱን ቀንሶ ጥቅሙን የሚያጎላ ተጨማሪ ዕርምጃዎች ስለሚወስድ፣ በአገር ደረጃ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ማንኛውም አካል ጥያቄውን ለማስፈጸም ኃይል መጠቀም ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑንም አክለዋል፡፡

መንግሥት በሰዎች ሕይወት፣ መብትና ንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዜጎቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ሒደት ወይም እንቅስቃሴ ውስጥ ተጨማሪ ጉዳትና ቁርሾ እንዳይፈጠር፣ ማኅበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ጉዳት እንዳይደርስ፣ በንግግርና በውይይት ብቻ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት መንገድ እንዲከተል አሳስበዋል፡፡

በሲዳማ አካባቢ የውሸት ወሬ በተደራጀ መንገድ አሠራጭተው ሕዝቡን ሊያጋጩ የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ መንግሥት እንደሚያውቅ ጠቁመው፣ የሲዳማ ሕዝብ ግን ባለው ድልብ ባህልና የአገር ሽማግሌዎች ተጠቅሞ ወጣቶች ወደ ሌላ ግጭትና ጥፋት እንዳይገቡ ባሉበት እንዲቆዩ እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ የወላይታ ሶዶም ማኅበረሰብ በሲዳማ ወንድሞቹ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳያደርስ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ እሳቸው በክልሉ ተገኝተው ሁሉንም የማኅበረሰብ አካል ስለሚያወያዩ፣ እስከዚያው ድረስ የፀጥታ አካላት ችግሩ እንዳይስፋፋ፣ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ አደጋ እንዳያጋጥም ጥንቃቄ የተመላበት ጥበቃና ክልከላ እንዲያደርጉም ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞንና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞንም በነዋሪዎች መካከል ከሦስት ሳምንት በፊት በተነሳ ግጭት ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ከፍተኛ ንብረት መውደሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በርካታ የጌዴኦ ተወላጆች ለበርካታ ዘመናት በጉጂ ዞን ውስጥ እየኖሩ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም. ‹‹ውጡልን›› በሚል የጉጂ ነዋሪዎች በፈጠሩት ግጭት የሰው ሕይወት ቢጠፋም፣ በክልሎቹ አመራሮችና በአገር ሽማግሌዎች ስምምነት ተፈጥሮ የተፈናቀሉ የጌዴኦ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የጉጂ አካባቢ ነዋሪዎች ተደራጅተው እንደገና ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠራቸው፣ የጌዴኦ ነዋሪዎች በድጋሚ እየተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውና ቤታቸውም እየተቃጠለ መሆኑን አክለዋል፡፡ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት ሲዘዋወር ቢታይም፣ ግጭቱን ግን ሊያስቆም አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም እየደረሰ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርትም በአካባቢው ከ200 ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ በነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በነዋሪዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አውግዟል፡፡ ድርጊቱን ሐብሊንና ኦሕዴድን እንደማይወክልም ገልጾ፣ የደረሰውን ጉዳት የክልሉ መንግሥትና ሕዝቡ ተባብረው እንደሚያካክሱት ማዕላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply