በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ሰሞኑን 28 ጉማሬዎች ሞተው ተገኙ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ከሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ትላንት አመሻሽ ድረስ 28 ጉማሬዎች ሞተው መገኘታቸወን ፓርኩ አስታወቀ።

የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ ወይዘሪት ባህሯ ሜጋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በአንድ ቀን ብቻ 15 ጉማሬዎች ሞተው ተገኝተዋል።

በአጠቃላይ ከሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ትላንት አመሻሽ ድረስ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ 28 ጉማሬዎች ሞተው መገኘታቸውን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

አደጋው በተለይም በዕድሜ አንጋፋ በሆኑት ጉማሬዎች ላይ የበረታ መሆኑንም ወይዘሪት ባህሯ ጠቁመዋል።

የሞት አደጋው እየደረሰ ያለውም ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ጉማሬዎች በሚኖሩበት ስፍራ ላይ መሆኑ ነው የተገለፀው።

ጉማሬዎች በምን ምክንያት እየሞቱ እንዳሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የጉራጌ ዞን አስተዳደር ባለሙያዎች እያጣሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከፌዴራል ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም ከሰበታ ብሄራዊ የእንስሳት ምርምር ማዕከል የተውጣጡ ባለሙያዎች ፓርኩ ወደሚገኝበት ስፍራ በዛሬው ዕለት ማምራታቸውን አንስተዋል።

በጉራጌ ዞን በአሽጌ፣ እነሞርና ኤነር እንዲሁም ቸሀ ወረዳዎች ላይ የሚገኘው ፓርኩ 36 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፥ በህገ ወጥ ተግባራት ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁም ተገልጿል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የደን ጭፍጨፋ እና ሰፈራ ፓርኩ ላይ የተጋረጡ ችግሮች ሲሆኑ፥ በዚህም በአበሽጌ ወረዳ ካለው የፓርኩ 35 በመቶ ይዞታ ግማሽ የሚሆነው የደን ሀብት መጥፋቱን ወይዘሪት ባህሯ አንስተዋል።

ከህገ ወጥ ተግባሩ ጋር በተያያዘም በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አንድ የፓርኩ ጥበቃ ባለሙያ ህይወቱን አጥቷል ነው ያሉት ሃላፊዋ።

በእነዚህና መሰል ድርጊቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና አፋጣኝ አለመሆንም የፓርኩን ህልውና እየተገዳደረ እንደሚገኝ ወይዘሪት ባህሯ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም በፓርኩ ላይ ህገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላትን በማጋለጥ ለፓርኩ ህልውና መጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

FBC

Share.

About Author

Leave A Reply