በጋራ ቆመን ሀገራችንን እንታደግ !!! (የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል!)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባሳለፍነው የሀዘን ሳምንት መላውን ኢትዮጵያዊ ሆነ የአለምን ህዝብ ልብ የሰበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋና እልቂቱን ስንዘክረው ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ለሰለባዎቹ ሁሉ ነፍስ ይማር ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይስጥልን ስንል ከፍተኛ ሃዘን እየተሰማን ነው።

ከላይ በአደጋ ያለቁትን ስናስታውስ ሀዘናችንን የሚያከብደው ሰው ሰራሹ የወያኔ ክልል መዋቅር ለሀያ ሰባት አመት በስሎ ዛሬ እነሆ መርዛማ ፍሬውን በየቦታው ህዝባችን እንዲያፍሰው እየተደረገ ይገኛል። የጠበበ ዘረኝነት እንደ ተስቦ እየተሳበ ህዝባችንን እያፈናቀለ ህፃናትን እሪ እያስባለ አረጋዊያንን እህ እያሰኘን በውጭ ያለነውንም በጭንቀት እየረበሸን ይገኛል።

ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በጌዲዮ፣ በለገጣፎ፣ በወለጋ፣ በጎንደር፣ በጅጅጋ፣ በሀረሬ በሌሎች በገጠር በከተማም ህዝብ ዋስትና አጥቶ፤ በሁሉ የኔ ነው ባይ ዘረኛ የሺህ ዘመን እኛነትን እየተለበለበ ይገኛል፤ በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ላይ ያሉ የጌድዮና ለሌሎች ወገኖቻችን አፋጣኝ እርዳታ ብሎም ዘላቂ መፍትሄ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን።

የአለም አቀፍ መገናኛ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና ማእከላዊ መንግስቱን በእጅጉ የናቁ ወይም ከመንግስት ጋር በጥምረት እየሰሩ ባሉ ቀበኞች አማካኝነት አዲስ አበባ ዙርያዋን የሚጨሰው የዘረኝነት ጭስ እያፈናት ይገኛል፤ ይሄንንም ሴራ በመረዳት ህብረ ብሔራዊዋን አዲስ አበባን ለመታደግ የባልደራሱን ስብሰባ የጠሩትንና የተሳተፉትን አዲስ አበቤዎች እያደነቅን ዘላቂ ለሁሉም የሚበጅ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ እስክትገነባ በጠራና በፈጠነ መንገድ አደረጃጀታችሁ እንዲፋጠን የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብር ሃይል ከመመኘት በተጨማሪ ሁለንተናዊ ድጋፋችን እንደማይለያችሁ ይገልፃል፤ እንዲሁም የፌደራልና የአዲስ አበባ ፓሊስ በነዋሪዎቿ ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ኢፍትሃዊና አድሏዊ አካሄድ እያወገዝን አሰራሩንም እንዲመረምርና ከህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፤ ይህንንም ስንል መልካም የሰሩትን የሰራዊቱ አባላትን እያመሰገንን ነው።

ዛሬ በአገራችን የሚታየውን ምስቅልቅል ሁኔታንና የነገውን አስፈሪ ቀን ለማስቀረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነቅቶ እንዲታገልና መንግስትም በአስቸኳይ ሁሉንም ያካተተ ውይይት እንዲጀምር የዜግነት ማሳሰቢያችንንም እናቀርባለን።

አክራሪነት በየትኛውም መልኩ አጥብቀን እንጠየፋለን !!!
ፈጣሪ ኢትዮዽያንና ህዝቧን ይባርክ !!!

የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል!

Share.

About Author

Leave A Reply