በጠሚ ዓብይ የምህረትና የይቅርታ የእስር ፍቺ ያላስተዋለው ሌውትናንት ኮሎኔል ጌታዬ አለሜ ላይ የተፈፀመ ግፍ!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሌውትናንት ኮሎኔል ጌትዬ አለሜ ይባላል። ትውልዱ ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ ነው። ከ1978 ዓም ጀምሮ ከኢህዴን ጋር ታግሏል። 108 ኮር፣ 31 ክፍለ ጦር የተለያየ ቦታ ላይ ሰርቷል። ከ1997 ዓም በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ዋና መስርያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰርቷል። የግንባር አዛዥ ዘመቻ የስራ አስፈፃሚ ፕሮቶኮል ኃላፊ ነበር። ጀኔራል አበባው ታደሰና ጀኔራል ሳሞራም ጋር በቅርበት ይሰራ እንደነበር ተገልፆአል።
.
በ1997 ዓም በነበረው ሰልፍ ተሳትፈሃል የሚል ግምገማ ተደረገበት። ወቅቱ በርካታ የአማራ የመከላከያ ሰራዊት አባላት “ቅንጅት” ተብለው የተፈረጁበት ወቅት ነበር። የታሰሩና የተባረሩም ብዙ ናቸው። ጌትየንም በፍረጃ አላለፉትም። ለ7 ወር አስረውታል። በወቅቱ በ8 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተፈትቶ ወደ ስራው ቢመለስም ከትህነግ/ህወሓት አዛዦች ጥርስ ውስጥ ገብቷል። እስከ 2006 በወከባ ስራ ላይ ቆይቷል።
.
በ2006 ዓም የመከላከያ ሰራዊት የሰው ኃይል ኃላፊ በሆነው አብርሃ በተባለ ሰው ትዕዛዝ ከስራ ታግዶ፣ ማዕረጉም ተነጥቆ ከስራ እንዲባረር ተደረገ። ማዕከላዊ ታስሮ ድብደባ ተፈፀመበት። በሽብር ክስ ተመስርቶበት ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ እያለ ልታመልጥ ነበር ተብሎ በጥይት ተመትቷል። በአራት ጥይት እግሩን የተመታው ሊያመልጥ ሲል፣ ወይም ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ አይደለም። ቤት ውስጥ አስቀምጠው ነው የመቱት። በዚህም ምክንያት አንድ እግሩ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።
.
በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆኖም ለረዥም ጊዜ ቃሊቲ እስር ቤት ጨለማ ቤት ታስሯል። አሰፋ እና ለታይ የተባሉ የቃሊቲ እስር ቤት ኃላፊዎች ህክምና እንዳያገኝ ከልክለውታል። በሌ/ኮ ጌትዬ ላይ ይህ በደል የተፈፀመበት በማንነቱ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ተገልፆአል። ለዚህ ሽፋንም <<የቅንጅት ሰልፍ ላይ ተገኝተሃል፣ የሀገር ከፍተኛ ሚስጥርን አባክነሃል>> የሚል ነው ተብሏል።
.
(ኮ/ል ጌትዬ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን ቤተሰቦቹ ደብዛው እንደጠፋባቸው በገለፁት መሰረት ከአንድ ወር በፊት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መጥፋቱንና ያለበትን የሚያውቁ ካሉ እንዲጠቁሙ በፃፍነው መሰረት፣ ቃሊቲ እንዳለ ተነግሯቸው ከጠፋ ከአራት አመት በኋላ ሊያገኙት ችለዋል)

(ጌታቸው ሽፈራው)

Share.

About Author

Leave A Reply