ቡድናዊነት የሚፈጠረው በትምህርት (እጦት) ነው የሚቀረፈውም በትምህርት ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(አይናቸው አሰፋ)

ባለፉት ወራት በተለያዩ ቦታዎች ይታይ የነበረው የመንገኝነት ባህሪ ይህው በዩኒቨርሲቲዎችም መታየት ጀምሯል። ወትሮም ቢሆን ዩኒቨርሲቲዎች ለንዲህ አይነቱ ባህሪ በተለይ ተጋላጭ ናቸው። ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ከተለያየ ቦታ የመጡ፣ አብዛኞቻቸው ከትውልድ ቦታቸው ርቀው የማያውቁ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት በዘውጋዊ አስተሳሰብ ታነፀው ያደጉ አፍላ ወጣቶች ሌት ተቀን በአንድ ላይ የሚያሳልፉበት ቦታ ነው ዩኒቨርሲቲ። እናም ይህ የምጡ መጀመሪያ ነው።
ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሆነውን አሳዛኝ ጥፋት ተከትሎ ብዙዎች ሃዘናቸውንና ቁጭታቸውን ሲገልፁ ደርጊቱን ሲኮንኑ በዛው መጠን ብዙዎች የድርጊቱ ባለቤት ነው ያሉትን ትውልድ በጅምላው ሲያውግዙ ሲያንቋሽሹ ታይቷል። ይህ የኋለኛው ችግሩን ያባብስ እንደሆን እንጂ መቼም መፍትሄ አይሆንም።
አንድ ሰው ህይወቱን በሙሉ በቡድን እንዲያስብ ተደርጎ ከተማረ፤ ያንተን ቋንቋ የሚናገር ወገንህ ሌላው ሁሉ ጠላትህ ነው እየተባለ ካደገ፤ ተወልዶ ያደገበት ሀገር መሪ ህግ የሰውነት መስፈሪያው ብሄሩ ነው ካለ፤ በተቧደነ ፖለቲካ በተቧደነ ትምህርት በተቧደነ የአስተዳደር መዋቅር ታንፆ ካደገ በኋላ ዛሬ ዩኒቨርሲቲ ስለገባ ብቻ ከዚያ ከተቀረፀበት የቡድን መንፈስ ወጠቶ እንዲያስብና እንዲኖር ብንመኝ ይሚሆን አይደለም።
በደህናው ጊዜ ያላለማመድነውን በጥሞና ማሰብ፣ ራስን መፈተሽ፣ በሰከነ መንፈስ መወያየት፣ በምክኒያት መከራከር፣ ሃሳብን ማብጠርጠርና መተንተን፣ እልፍ ሲልም ልዩነትን ማቻቻል ወዘተ ዛሬ በድንገት አምጣ ብንለው ከየት ይመጣል?
ጭራሽ ይህ ትውልድ እንዲህ ነው እንዲያ ነው እያልን ብንፈርጀው፤ ‘የኛ’ ካልነው ትውልድ ጋር እያነፃፀርን ብንሰድበው፣ ብናወግዘው፣ ብናላግጥበት ብናጥላላው ችግሩን እያባባስን እንጂ እየፈታን አይደለም።
እዚህ ላይ የቡድን አስተሳሰብን ወይም መንጋዊነትን እያበረታታሁ ፈፅሞ አይደለሁም። ወይም ይህ ህገወጥ እና አስነዋሪ ተግባር አይኮነን እያልኩም አይደለም። ይልቁንም የሃገሪቱን ህዝብ ግማሽ የሚሆነውን ወጣት በጅምላ የድንቁርና ተምሳሌት የኋላቀርነት መገለጫ ማድረግ ከማራራቅ (alienate) እና ልዩነቶችን የበለጠ ከማስፋት የተለየ ፋይዳ የለውም። አያቀራርብም መፍትሄ ለመሻት የሚመች ሁኔታን አይፈጥርም ለማለት ነው።
በሆነው ሁሉ እንደማህበረሰብ እንደሃገር ልናፍርበት ይገባናል። እነዚህ ወጣቶች ከሰማይ የወረዱ ወይም ከምድር የፈለቁ አይደሉም። በመካከላችን ተወልደው ያደጉ የኛው የአስተሳሰብ እና አኗኗር ውጤት ናቸው። በዘውግ የተሳከረ የፖለቲካ ስርአት የዘረጋንላቸው፣ ሃሳብ አልባ ትምህርት የቀረፅንላቸው፣ ያስተማርናቸው እኛው ነን። አስተማሪዎቻቸው፣ ወላጆቻቸው፣ መሪዎቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው፣ ዘመዶቻቸው፣ እኛው ነን። በልማታቸውም ሆነ በጥፋታቸው እጃቸን አለበት።
ስለሆነም ችግሩን የአንድ ትውልድ ብቻ አድርጎ ከማንቋሸሽና ከደሙ ንፁህ ነኝ አይነት አስተያየት ከመስጠት ይልቅ የጋራ ውድቀታችን መሆኑን አምኖ መቀበልና በጋራ ለመፍታት መጣር ያዋጣል። ችግሩን ማድፈንፈንም፣ የአንዳንድ ‘የግል ጥቅም ፈላጊዎች’ ወዘተ እያሉ መለጠፊያ መፈለጉም፣ የተበላሸ ትውልድ ውጤት ነው የሚለውም ሁሉም የትም አያደርስም። የህግ እርምጃም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፀጥታ ሃይሎችን ማሰማራትም ለጊዜው ችግሩን ያቃልል እንደሆን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም።
ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣው በትምህርት ብቻ ነው። ቡድናዊነት የሚፈጠረው በትምህርት (እጦት) ነው የሚቀረፈውም በትምህርት ነው። የትምህርት ስርአታችንን ከስር መሰረቱ ከነይዘቱ ከነመዋቅሩ ማሻሻል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply