ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን አንቀጽ 39 ምን ይዞልን መጣ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

እ ኔ በአንድ ተአምር ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን እድል ቢያጋጥመኝ የመጀመሪያው ቀን ቢሮ ገብቼ የምሠራው ሥራ ቢኖር ሁሉንም በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ሰብስቤ ሁላችሁም ከዛሬ ጀምሮ አንድ ዓመት ጊዜ ይሠጣችኋል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የብሔራችሁን መሬት ድንበር አስምራችሁ ችካል ቸክላችሁ አሳዩኝ ብዬ ለሁሉም ፓርቲዎች ትዕዛዝ ነው የማስተላልፈው ታዲያ ይህ ድንበር በሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያለውና አጨቃጫቂ መሆን የለበትም እነዚህ ፓርቲዎች ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ከዚያ ቀን በኋላ ህልውናቸው ያከትማል::

ወደ አንቀጽ 39 ስንመጣ ብሔር ብሔረሰቦች እራስን በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል ሲል ምን እንደሚገነጥሉ በዝርዝር አስቀምጠው መሬትን ከሆነ ከላይ እንደተጠቀሰው ያ መሬት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድና አጨቃጫቂ ባልሆነ መንገድ በሚገባ ተለይቶ መቀመጥ ነበረበት አለበለዚያ ሕዝቦች በፍቅር በሰላም እንዳይኖሩ የጠብ አጀንዳ ማዘጋጀት ነው የሚሆነው::

አንቀጽ 39 ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን ማን ለልማት ተጠቃሚ ማን ደግሞ የበይ ተመልካች እንደሆነ ለማስረዳት ማንኛውም ዜጋ ሊመሰክረው የሚችለው ጉዳይ ነው:: ከምንም በላይ በየክልሎች በየዓመቱ የሚሠበሰበውን የታክስ ገንዘብና የሚያዘውን በጀት ብቻ መመልከት በዕጅጉ ጊዜ ቆጣቢና በቀላሉ መልስ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ነው:: በቀላሉ ለንጽጽር እንዲረዳ የሶስት ክልሎችን በጀት ብቻ ለማሳየት ልሞክር:: አዲስ አበባ የቆዳ ስፋት 540 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ለ2011 በጀት ዓመት የተያዘ በጀት 45 ቢሊዮን ብር፤ ኦሮሚያ 353 000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የተያዘ በጀት 63 ቢሊዮን ብር፤ አማራ ክልል 160 000 ሺ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የተያዘ በጀት 43 ቢሊዮን ብር፤ ይህ አሐዝ የሚያሳየን ምን ያህል በክልሎች ውስጥ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የበጀት ልዩነት እንዳለ ነው::

አዲስ አበባ አንድ ሺ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የማትሞላ ክልል 45 ቢሊዮን ብር በጀት ስትይዝ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ 670 ጊዜ በስፋት እየበለጠች የያዘችው በጀት 63 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው:: ታዲያ በዚህ ገንዘብ ክልሉ ምን ዓይነት ልማት ነው ሊያመጣ የሚችለው? ለወጣቱ ትውልድስ በምን መልኩ ነው የሥራ ዕድል የሚፈጠረው? ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ክልሎች ለምንድን ነው በቂ ታክስ መሰብሰብ ያልቻሉት? ይህንና መሰል ጥያቄዎችን እያነሳን ሰፊ ውይይት ማድረግ ይቻላል ነገር ግን ሥልጣን የያዘው መንግሥት እንዲህ ያለ በቀላሉ የሚታይ የዕድገት ልዩነት ሲታይ በቂ ጥናት በማድረግ የፖሊሲ እርማቶችን ለማድረግ የማይተጋው? አሁን በአገሪቱ የሚታየው ብጥብጥና ሁከት የሶማሌ ሕዝብ ኦሮሞን ጠልቶ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ትግሬን ጠልቶ ሳይሆን ተደጋጋሚ ብሶት ስለ አለበትና ይህንን ብሶት ለመግለጽ የሚወስደው የተሳሳተ እርምጃ ነው አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ያለው::

ሕግ ማውጣትና ማረም የመንግሥት ሥራ እንጂ የዜጎች ሥራ አይደለም መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ስህተቶችን ለማረም እግሩን የሚጎትት ከሆነ በአገር ላይ ለሚደርሰው ጉዳትና አደጋ ተጠያቂ የሚሆነውም መንግሥት ብቻ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም:: ክልሎች በቋንቋ ምክንያት ባለሀብቶች በበቂ ሁኔታ የማያገኙ ከሆነ፤ ክልሎች ተጠሪነታቸው ለራሳቸው ከሆነና የፌደራል መንግሥት በተፈለገው ጊዜ ሊጠይቃቸውና ሊያገኛቸው ካልቻለ፤ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ መንግሥታት እና አበዳሪዎች ጋር እየተዋዋሉ ልማት ሥራ የማይሠሩ ከሆነ ፤ እንደ መንግሥት እውቅና አግኝተው ለዓለም አቀፍ ሕጎች ተገዥ እና ተጠያቂ መሆን ካልቻሉ ክልሎች በውስጣቸው ያሉ ሌሎች ብሔረሰቦች በአግባቡ ማስተዳደር የሚችልበት ሥርአት ካልዘረጉ ወዘተ ልማት እንዴት መመኘት ይቻላል::

ይህስ ሁኔታ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? የአዲስ አበባ ነጋዴዎች አየር በአየር ንግድና ሥራ ብቻ ወደ ክልል ብቅ ብለው ሳንቲማቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ እያመጡ ቋሚ ሀብት የሚያፈሩ ከሆነ ክልሎች በክልላቸው የተፈጠረን ሀብት እንዴት ክልሉ ውስጥ ማስቀረት ይችላሉ? አንቀጽ 39 ሕገ መንግስቱ ሲፀድቅ እኔን ጨምሮ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አልገባንም ነበር፤ አሁን ግን ያመጣው ጣጣ እያንዳንዱ ዜጋ ጓዳ ውስጥ ሳይቀር እየገባ የዜጎችን ሕልውና እያመሰቃቀለው ይገኛል ታዲያ ምን እስኪሆን ነው የምንጠብቀው::

በአንቀጽ 39 ምክንያት በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክልሎች እንዳያገኙ በማድረጉ የተነሳ አገራችን ኢትዮጵያ ማግኘት የነበረባትን ታላላቅ ኢንቨስትመንቶች አጥታለች:: በአገራችን በስፋት የሚታወቁት ባለ ሐብቶች ቻይናውያን ሲሆኑ ቻይናውያን ባላቸው እምነት ልማት ኢንቨስትመንት የሁሉንም ሠዎች አስተሳሰብ ይቀይረዋል የሚል ፍልስፍና (ፊሎዞፊ) ስለ አላቸው ነው በድፍረት ወደ ክልል ሄደው ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት የሚያካሄዱት:: እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡት ቻይናውያን እዚህ አገር በድፍረት ይህንን ሁሉ ሐብት ባያፈሩ ምን ይውጠን ነበር::

እዚህ ላይ ለኢህአዴግ ባለሥልጣናትም ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መጠየቅ የምፈልገው ነገር እኔ በግሌ በዚህ ጽሁፍ ያለኝን ሐሳብ ለማቅረብ ሞከርኩ እንጂ ጠቃሚ የሚሆነው በበቂ ጥናት ላይ የተመሠረቱ ሠፊ ጥናታዊ ጽሁፎች በሕገ መንግሥቱና፤ ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን ያስከተለውም ጥሩም ይሁን መጥፎ ክስተት በስፋትና በጥልቀት መገምገም እንዲቻል አንድ ፕሮግራም ቢዘጋጅ መልካም ነው እላለሁ:: አንድ ትውልድ ከባድ ፈተና በሕገ መንግሥቱ ምክንያት አሳልፎአል ሌላ ትውልድ ይህንን መከራ ተሸክሞ እንዲጓዝ መፍቀድ የለብንም:: በጣም የሚገርመው የመንግሥት ፖሊሲ አንዱ ኢሕአዴግ የሚመራው ብሔራዊ ባንክ የሚከተለው እጅግ የተሳሳተ የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲ ነው:: ኢትዮጵያዊ ውስጥ ያሉ ባንኮች የመንግሥትም የግሉም በሁሉም ያገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ የሚከለክላቸው የለም በመሆኑም በመላው አገሪቱ ሊባል በሚችል መልኩ ቅርንጫፍ ይከፍቱና የሰበሰቡትን ተቀማጭ ገንዘብ ያለ ምንም ገደብ አብዛኛውን ወደ አዲስ አበባ ያጓጉዙበታል ከዚያም ለአዲስ አበባ ተበዳሪዎች ያቀርባሉ:: ይህ አሠራር ከፍተኛ የሆነ የካፒታል ስደት የሚፈጥር ሲሆን ገንዘቡ በተገኘበት አካባቢ ለብድር መቅረብ ሲገባው ሌላ ቦታ ለብድር ሲቀርብ በአገሪቱ ፍትሐዊ ያልሆነ ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል:: ይህንን አሠራር ለማስቀረት 1ኛ የገጠሩ ገበሬ መሬቱን አስይዞ መበደር እንዲችል ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት:: 2ኛ ባንኮች አሠራራቸው በዞን ተከፍሎ አንድ ዞን የተገኘ ወይም ተቀማጭ የሆነ ገንዘብ ሌላ ዞን እንዳይሄድ የሕግ እገዳ ሊጣልበት ይገባል:: ከፍተኛ ባለ ሐብቶች ከአንድ ዞን ወደ ሌላ ዞን ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ከብሔራዊ ባንክ ልዩ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባል::

ይህ አሠራር በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራር ሲሆን ከአገር አገር ብቻ ሳይሆን ከአንድ ዞን ወይም ክልል ወደ ሌላ ክልል ወደ ሌላ ዞን ገንዘብ እንዳይዘዋወር ማገድ ክልሎች መልማት እንዲችሉ ሠፊ ዕድል ከመስጠቱ በተጨማሪ ባለሐብቶች በቂ ካፒታል ወደ አለበት አካባቢ እየሄዱና እንዲሰሩም ዕድል ይከፍታል ፤ይህ ፖሊሲ እስከ አሁን አለመተግበሩ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል መንግስትም መልማት ወዳለበት እና ኋላ ቀር የሆነ አካባቢ በቂ ገንዘብ እንዲኖር በማድረግ ያለሙ አካባቢዎች ልማት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል::

በአንቀጽ 39 መሠረት ክልሎች መሬታቸውን የማስተዳደር ሙሉ መብት ያላቸው ሲሆን ፌደራል መንግሥት ሰፋፊ መሬት ክልሎች የማስተዳደር (ባለፉት 27 ዓመታት) ባለ መቻላቸው በተውሶ በሚል አባባል የፌደራል መንግሥት እንዲያስተዳድራቸው ተደርጓል ነገር ግን መሬት ሠጭ ፌደራል መንግሥት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሠጭ ሆኖ ደግሞ ክልሎች በመሆናቸው በባለ ሐብቶች ላይ ከፍተኛ ወከባ ሲደርስ ቆይቶአል::

ሰፋፊ እርሻ እንዳይስፋፋና በምግብ ምርት እራሳችንን እንዳንችል ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች አንዱና ትልቁ ይህ ምክንያት ነው፤ በተጨማሪ አሁንም ወርቅ ሸጠን ስንዴ ወደ አገር ውስጥ እያስገባን ነው:: በኢንዱስትሪ ፓርኮች በከፍተኛ ግንባታ ቦታ አድካሚ ሥራ የሚሠሩ ዜጎቻችን አሁንም በቂ ምግብ ሳያገኙ ነው የሚሠሩት ይህ ደግሞ ለከፍተኛ የጤና ችግር እያጋለጣቸው ነው::

ይህ ማለት አሁንም በአንቀጽ 39 መሠረት እየተራብን ነው ማለት ነው:: የከተማ ሰው የገጠር መሬት ያለምንም ውጣ ውረድ ገዝቶ ገበሬ የሚሆንበት፤ የገጠር ሰው ያለ ምንም ውጣ ውረድ የገጠር መሬቱን ሸጦ የከተማ ሰው የሚሆንበት አሠራር አሁንም የለም:: ይህ አሠራር ዜጎች የፈለጉትን ሥራ በፈለጉት ቦታ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያግድ ከመሆኑም በላይ አሁን ላለንበት ድህነት፣ ስደትና ኋላ ቀርነት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቶልአል::

በመሆኑም እጅግ አስፈላጊው ሥራ ተሠርቶ በመላው ዓለም ያለውን አሠራር ለመከተል መትጋት አለብን:: አንድ ባለሐብት የገጠር መሬት ገዝቶ እሴት ከጨመረበት በቀላሉ በመቶ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ከገጠር ወደ ከተማ ስደት ይቆማል፤ ውቅያኖስ አቋርጦ ስደት መሄድ ይቆማል፤ ሌሎ አገሮች ከተፈጥሮ ጋር ግብ ግብ ፈጥረው በረሐ አልምተው ሕዝባቸውን ሲመግቡ ከራሳቸውም አልፈው ሌሎችን ሲረዱ እኛ 70 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት ይዘን ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚሰሩ እጆች ይዘን እየተራብን ነው:: ይህ የሆነው ሥልጣን የያዘው መንግሥት እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ የተሳሳተ ፖሊሲን አልቀይርም በማለት በሚያራምደው አሠራር ምክንያት ነው:: በተለይ ይህ ከፍተኛ ውጪ የወጣበት የኢንዱስትሪ ፓርክ በድጎማ የተመረተ ርካሽ የምግብ ምርት እያቀረብን ሠራተኞች ተመጣጣኝ ምግብ እየበሉ ምርታማ ካልሆኑ የተገነባባት ዕዳውን እንኳን መክፈል አቅቶን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው የምንገባው::

በአንቀጽ 39 ምክንያት ክልሎች የተለጠጠ ሥልጣን ሕገ መንግሥቱ ስለ ሠጣቸው ሕዝባቸውን እያገለገሉበት ሳይሆን በሕዝባቸው እየተገለገሉ ነው ማለት ይቻላል፤ በቅርቡ በሶማሌ ክልል ይህ ሁሉ የዜጎች ሰቆቃ ሲከሰት የፌደራል ደህንነት መሥሪያ ቤት 1ኛ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት መፍትሄ ማፈላለግ አለመቻሉ 2ኛ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ክልሉ ጥያቄ እስኪያቀርብለት ድረስ ያሁሉ ወንጀል ሲፈፀም ዝምታን የመረጠበት ምክንያት ይኸው የአንቀጽ 39 ውጤት ነው:: እንደሚታወቀው አሜሪካ የፌደራል ሥርዓት ከሚከተሉ አገሮች ቀዳሚዋ ነች::

በዚች አገር ውስጥ ኤፍ.ቢ.አይ የሚባል መሥሪያ ቤት አለ፤ ይህ መሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊነቱ በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ማንኛውንም ዓይነት የፀጥታ ችግር በከፍተኛ ፍጥነት መፍትሄ በማፈላለግ ዜጎች ያለ ሥጋት እንዲኖሩ ያደርጋል የክልሉን ጥያቄ እስኪቀርብ አይጠብቅም:: እኛ አገር ግን ዜጎች ሰቆቃ የሚደርስባቸው በታጠቀ አሸባሪ ድርጅት ሳይሆን ከሕዝብ የተሰበሰበ የታክስ ገንዘብ የሚበሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል የሚባሉ ታጣቂዎች ነው፤ ይህ ሁኔታ እጅግ ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ ነው ሕዝብን ሊጠብቁበት በታጠቁት የጦር መሣሪያ በሕዝብ ላይ ጥቃት መፈፀም የአገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ መዳኘትም ያለባቸው በዚህ መሠረት ነው::

የፌደራል መንግስቱም ሕገ መንግስቱ አይፈቅድልኝም እያለ በየቀኑ አሰቃቂ ዜና ስንሰማ በዝምታ ከማለፍ በአስቸኳይ ሕገ መንግሥታዊ እርማት እንዲደረግ ተግቶ ቢሠራ የተሻለ ነው እላለሁ፤ አገር ከፈረሰ በኋላ ሕገ መንግሥቱ ከሚፈርስ አገር ሳይፈርስ ሕገ መንግሥቱ ቢፈርስ ይሻላል፤ የኛን ዓይነት ሕገ መንግሥት ያለው አገር በየትም የዓለም ጥግ የለም እኛ ደግሞ ከዓለም ሕዝብ የተለየን የምንሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤ ይህንን ለማድረግ ወኔ፤ ፍላጎት አቅም ካጣን አሁን ያለው የችግር አዙሪት ማለቂያ አይኖረውም:

(መታሰቢያ መላከህይወት)

Share.

About Author

Leave A Reply