“ባንድ ሆድ – ብዙ ዓይነት ጉድ” (አሳዬ ደርቤ የቃሊቲ ፕሬስ ጸሀፊ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

እኛ ኢትዮጵያውያን ሆደ-ሰፊዎች ነን፡፡

ሆደ-ሰፊነታችን በጎ ያልሆኑ ነገሮች ለማቆር ሲሆን እየተለጠጠ ይሄዳል፡፡ በርካታ ጭቆናን፣ ግፍን፣ ድህነትን፣ የፍትህ እጦትን የመሸከም አቅም አለው፡፡ ለዚያም ነው 25 ዓመት ሙሉ ‹ባንድ ሆድ ብዙ አይነት ጉድ› ተሸክመን ‹ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል› በማለት ስንጠባበቅ የኖርነው፡፡

በሌላ መልኩ ግን ይሄ ‹ከአገር የሚሰፋ ሆዳችን› ለመልካም ነገሮች ሲሆን የተሸማቀቀ ነው፡፡ ወላ… ሳንበላው ሁሉ ልንጠግብ እንችላለን፡፡ ለዚያም ነው ኢህአዴግ ለ25 ዓመታት ከጋተን ብሶት በላይ የዶክተር አቢይ መልካም ቃላት ሆዳችንን ጠብዝራ የምታስጨበጭበን፡፡

ስለዚህም ከባድ ልፋት የሚጠይቀው እኛን ማስከፋቱ እንጂ ማጽናናቱ አይደለም፡፡ እኛን ለማሳዘን ብዙ ጉልበትና በርካታ ዓመታት ያስፈልጋል፡፡ እኛን ለማስደሰት ግን ጥቂት ቃላትና ሙጭቅላ ድርጊት በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚከብደን ጎሚ መያዙ እንጂ አውፍ ማለቱ አይደለም፡፡

ችግሩ ግን… ባሳለፍናቸው ዓመታት በዚህ ስርዓት ውስጥ ሲቀያየሩ የነበሩ ባለስልጣኖች ሁሉ ይሄን መልካም አጋጣሚ ከመጠቀም ይልቅ አጋጣሚውን ማክሰም ላይ የሚረባረቡ መሆናቸው ነው፡፡ ዝምታችን እንደ ምቾት፣ ታጋሽነታችን እንደ አለዋቂነት  በመቁጠር… ቅሬታችንን በተግባር ቀርቶ በጥሩ ንግግር ለመፍታት ተስኗቸው ሰፊው ሆዳችንን ‹‹ጥበትና ትምክህት›› በሚል ቃል መሙላቱን ተያያዙት፡፡ በዚህም የተነሳ የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ የሚገነፍለውም ገነፈለ፡፡

እንደ እኔ እምነት የዚህን ህዝብ ፍላጎት ማሟላትም ሆነ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ በጣም ቀላል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የእኛ ህዝብ የሚጠይቀው ‹ያጣውን› እንጂ ‹የሚመኘውን› አይደለም፡፡ መቼም ቢሆን መሰረታዊውን እንጂ የቅንጦቱን አይጠይቅም፡፡

ለማስረጃም ያህል፡- አታፈናቅሉኝ እንጂ አትምጡብኝ ብሎ አይሞግትም፡፡ ማንነቴን አታጥፉብኝ እንጂ ምቾቴን ጠብቁልኝ ብሎ አይጮህም፡፡ አታስርቡኝ እንጂ አጥግቡኝ ብሎ አይቸካቸክም፡፡ አትሰሩኝ እንጂ ‹‹ይታሰሩልኝ›› ብሎ አያምጽም፡፡ አትግደሉኝ እንጂ አሳክሙኝ ብሎ አያድምም፡፡ ችግር አትሁኑብኝ እንጂ መፍትሄ አምጡልኝ ብሎ አይገግምም፡፡ የልማት ጥያቄ ቢያነሳ እንኳን ከመንገድ፣ ከውሃ፣ ከመብራትና ከክሊኒክ አይዘልም፡፡

የማህበረሰቡን እንተወውና የሶሻል ሚዲያውን ተጠቃሚ ነጥለን ብንመለከት እንኳን…. በባለፉት ዓመታት ዘመቻ ሲያካሂድባቸውና ተቃውሞውን ሲያሰማባቸው የነበሩት አጀንዳዎች ተረቅቀውና ጸድቀው ሲላኩለት የነበረው ከመንግስት እንጂ ከተቃዋሚ ወገን አልነበረም፡፡ ችግር እየፈጠረ፣ ሴራ እያዋቀረ ሲያስጮኸን የነበረው ራሱ መንግስት ነው፡፡ ከፖለቲካ ነቆራዎች ጋር የተለያዩ ወጎችና ግጥሞች፣ ልቦወለዶችና ፎቶዎች ሲለጠፉበት የነበረውን የፌስ-ቡክ ምድር ወደ ፖለቲካ መድረክነት የቀየረውና….  በተለያዩ ዘውጎች ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ጸሐፊዎችና ገጣሚዎች ወደ ፖለቲካ አክቲቪስትነት የቀየራቸውም እራሱ ነበር፡፡

እስኪ ለአፍታ መለስ ብላችሁ በሶሻል ሚዲያ ላይ የጮኽንባቸውንና የዘመትንባቸውን አጀንዳዎች ሁሉ ተመልከቷቸው፡፡ አንዳቸውም ውስጥ የመንግስት እንጂ የእኛ ችግር አልነበረም፡፡ ‹እነ እንትና ፍቱልን› እንጂ ‹እነ እንትናን እሰሩልን› የሚል ዘመቻ አልነበረም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የዋልድባ መነኮሳትን፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶችንና ጋዜጠኞችን እያሰረ…. ኮሽ ባለ ቁጥር በጅምላ እየገደለ፣ በሚወጥናቸው ሴራዎች አንዱን አፈናቅሎ ሌላውን እየተከለ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየጣለ፣ ይታደሳል ሲባል ፈራርሶ ከች እያለ፣ እንደ መንደር ውርጋጥ የቴዲ አፍሮን የአልበም ምርቃትና ኮንሰርት እየከለከለ፣ ጩኸቱን ሰጥቶ መጮኸን፣ ቅዋሜን ፈጥሮ መቃዎምን እየከለከለ፣ ሲያስጮኸን የነበረው እራሱ ነበር፡፡

እናም ከእነዚህ ሁሉ እውነታዎች ስንነሳ በባለፉት ጥቂት ዓመታት…. መንግስት መልስ ፍለጋ ሲሰበሰብና ሲበተን፣ ሲታደስና ሲበሰብስ የነበረው የህብረተሰቡን ሳይሆን የራሱን ችግሮች ለመፍታት ነበር፡፡ ምንም እንኳን በአገሩ ላይ መቧገት ያንገሸገሸው ማህበረሰብ በተስፋ ቆራጭነት ያነሳውን ተቃውሞ እድገቱ እንዳመጣው አድርገው ‹‹ሞጋች ማህበረሰብ ፈጠርኩ›› እያለ ሊመጻደቅበት ቢሞክሩም ‹አልቢን› እየተዋዋሰ ሲያጭድ የነበረው የራሱን አዝመራ ነበር፡፡

እንጂማ…. ይሄ ማህበረሰብ ካቻምና ያረደውን በግ የአምናው ፋሲካ ላይ መግዛት ሲያቅተው ዶሮ ገዝቶ በማረድ ፈንታ ቢለዋ ይዞ ወደ አደባባይ አልወጣም፡፡ መንግስት ግን ይሄን የህብረተሰቡን ቻይነትና ሆደ-ሰፊነት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ ምድሩን እንዳይመለከት እንደ ነፍሰ-ጡር የተወጠረ ቀፈቱ አግዶት… የህዝቡን ርሃብ እንዳይመለከት የራሱ ጥጋብ አስረስቶት በእጦት ላይ እጦት፣ በጭቆና ላይ ጭቆና ሲሞላን ከረመና ሰፊው-ሆዳችን የሞላ እለት ሁሉም ነገር ከቁጥጥሩ ውጭ ወጥቶ አረፈ፡፡

አሁን…. በተወሰነ መልኩም ቢሆን የዶክተር አቢይ ጠቅላይ-ሚኒስቴርነት ሰሚ አግኝቷል፡፡ የህዝቡን ብሶት በጥቂት ቃላቶቻቸው ማጥፋት ባይችሉ እንኳን ማስታገስ ችለዋል፡፡ እንደ ኢህአዴግ በጥላቻ ዓይን ከመታየት ድነው በጥርጣሬ ለመታየት በቅተዋል፡፡ የህዝቡንም ስሜት ከመንግስት ይቀየርልን ‹‹እንዲህ ይደረግልን›› ወደሚል ሃሳብ አምጥተዋል፡፡

በእስካሁኑ ሂደትም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ህዝባቸውን ማነጋገራቸው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ህዝብ ጥያቄ የመለወጥ ብቻ ሳይሆን የመደመጥም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ለዘመናት መተንፈስ የተከለከለውን ማህበረሰብ የውስጡን ቃጠሎ እንዲተነፍስ ማድረግ በራሱ ቀላል መፍትሄ አይደለምና ያደረጉት ነገር መልካም ነው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን በፖለቲካው ዓለም ከተግባር ይልቅ ንግግር ለተወዳጅነትም ሆነ ለተጠሊነት ይዳርጋል፡፡ እስካሁን ድረስ በተባ አንደበታቸው ከቀድሞው ጠቅላይ-ሚኒስቴር መብለጥ ችለዋል፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ከብዙ ቃላት መሃከል አንድ ‹ብስናት› ያመለጠ እለት በተወደዱበት አንደበት መጠላት ሊመጣ ይችላሉ፡፡ እነ አለምነውን ከመጠን በላይ ህዝቡ ሊጠላቸው የቻሉት ከብአዴን በተለየው ተግባራቸው ሳይሆን ተገቢነት በሌለው ንግግራቸው ነው፡፡ ስለዚህም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ከአፋቸው የሚወጣውን ቃል ቆጠብ አድርገው ወደ አፋችን የሚገባውን እህል ቢያመቻችቹልን ደግ ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም የተቃወሰው የሃገራችን ፖለቲካ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በቃላት ሊረጋጋ ይችላል፡፡ የዳሸቀው ኢኮኖሚ ግን ድርጊትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ገባያውን ማረጋጋትና የውጭ ምንዛሬውን ማግኘት የፖለቲካ ስነ-ምህዳሩን እንደ ማስፋት በኢህአዴግ ስራ-አስፈጻሚ ውሳኔ የሚመጣ ስላልሆነ ከአሁን ቢታሰብበት ጥሩ ነው፡፡ ይሄን ስል ታዲያ ‹ዶላር ለማፈላለግ› በሚል ሰበብ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር አውሮፓና አሜሪካ ተሻግረው ዲያስፖራውን መሰብሰብ ይጀምሩ› ማለቴ አይደለም፡፡

ባንድ ወቅት እንደውም የአባይን ቦንድ እንዲሸጡ ወደ ውጭ አገር የተላኩት ሚኒስቴሮች ካመጡት ዶላር ይልቅ ይዘውት የሄዱት ዶላር በልጦ ነበር አሉ፡፡ ማለትም…. ከቦንድ የተገኘው ዶላር ለእነሱ ሆድ ከወጣው ጋር ሲወዳደር… ሆዳቸው ግፍን ቻይ ሆዳችንን ባይበልጠውም ግድባችንን በልጦት አረፈ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡

እናም……

ቃሊቲ ፕሬስ

Share.

About Author

Leave A Reply