ቤተ ክርስቲያንን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሚከላከል አካል እንዲቋቋም ተጠየቀ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ቤተ ክርስቲያንን ከፖለቲካ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚከላከል አካል በቀጣይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባኤ እንዲሰየም እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የአማኞች ቁጥር የቀነሰበትን ምክንያት የሚመረምርና መፍትሄ የሚያስቀምጥ ራሱን የቻለ አካል እንዲቋቋም የሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን ማህበረ ካህናት ጠየቁ፡፡
ማህበረ ካህናቱ “ከተዋሃደው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባኤ ምን እንጠብቅ?” በሚል ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ ሁለቱ ሲኖዶሶች ከተዋኃዱ በኋላ የሚደረገው ምልዕተ ጉባኤ፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ ሊበጅ የሚገባውን ጉዳይ አመላክተዋል፡፡
“ታላቅና ገናና ስም የነበራት ቤተ ክርስቲያናችን፤ የአማኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ፣ ተደማጭነቷ እየቀነሰ፣ ልዕልናዋ እየተደፈረ፣ ክብሯ እየተሸረሸረ መጥቷል” ያሉት ማህበረ ካህናቱ፤ “የሰው ኃይል፣ የገንዘብ አቅምና የእውቀት ችግር የሌለባት ቤተ ክርስቲያን፤ እንደ ተራ ተቋም፣ ለቁጥር በሚያዳግት ችግሮች ተተብትባ ልትቀጥል አይገባትም” ብለዋል፡፡
ይህን ለማረቅም የተዋኃደው ቅዱስ ሲኖዶስ ከምንግዜውም በላይ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትና በመሰረታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ላይ አተኩሮ ሊወያይ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በተለያየ ጊዜ ታላላቅ ውሳኔዎችን ያሳልፍ የነበረ ቢሆንም ውሳኔዎቹ ወደ ተግባር መለወጣቸውን የሚከታተል አካል ባለመኖሩ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፣ በዚህኛው ምልዐተ ጉባኤ ግን የውሳኔዎችንና መመሪያዎችን አፈፃፀም የሚከታተል ጠንካራ አካል ሊቋቋም ይገባል ብለዋል – ማህበረ ካህናቱ፡፡
የአማኞች ቁጥር እየቀነሰ የመጣባቸውን ምክንያቶች ጨምሮ መፍትሄ የሚያመላክቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሚከላከሉና፣ ለቤተ ክርስቲያን መዳከም አስተዋፅኦ ያደረጉ ችግሮችን አጥንቶ መፍትሄ ማበጀት የሚችሉ ራሳቸውን የቻሉ አካላት እንዲቋቋሙም ማህበረ ካህናቱ ጠይቀዋል፡፡
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ከውድመት በመታደግ ሂደትም ቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በግንባር ቀደም ተነሳሺነት በቂ የሰው ኃይልና ገንዘብ በጅታ እንድትንቀሳቀስም በአቋም መግለጫው ተጠይቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያቱን በጠንካራ መዋቅር ለመምራትና የዕዝ ሰንሰለቱን ለመጠበቅ፣ ወቅቱንና የሀገሩን ህግ ያገናዘበ በባለሞያ የተጠና መተዳደሪያ ህግ (ደንብ) እንዲዘጋጅ ሃሳብ ያቀረቡት ማህበረ ካህናቱ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሙሰኞች፣ የሌቦችና የጎጠኞች መደበቂያ መሆኗም እንዲያበቃ፣ ወሳኝ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱም አመልክተዋል፡፡
ሁለቱ ሲኖዶሶች ከተዋኃዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ፤ የሀገሪቱ መንግስት ከጀመረው የለውጥ መንገድ ጋር የሚተካከልና የቤተ ክርስቲያኒቱን ታላቅነት ወደ ነበረበት የሚመልስ ውሳኔ እንደሚጠብቁ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማህበር ካህናት ዘሰሜን አሜሪካ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ በጅግጅጋና አካባቢው እንደተከሰተው ቤተ ክርስቲያንን ኢላማ የሚያደርግ ጥቃትን አስቀድሞ የሚያጠና እንዲሁም የመከላከል ስራ የሚሰራ የአደጋ ዝግጁነትና ትንተና መምሪያ በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ሰኞ በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ይመክራል ሲሉ ቅዱስ ፓትርያርኩ አመልክተዋል። ይህ መመሪያ በአግባቡ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል በሚል በባለሙያዎች ተጠንቶ የተዘጋጀው መሪ እቅድ፤ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመርምሮ ወደ ተግባር እንዲገባ፣ ለአተገባበሩም የትግበራ ጽ/ቤት ራሱን በቻለ የሰው ኃይልና በጀት እንዲቋቋም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ቅርስን ጉዳይ በተመለከተም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንግስት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲያበጅ ተወስኗል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply