ብሄራዊ ፈተናዎች፡ የ68 ተማሪዎች ውጤት ተሠርዟል የ846 ተማሪዎች ውጤት ደግሞ በከፊል ማጣራትን ይጠይቃል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ 2011ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ (የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ) ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ውጤት ዛሬ ተለቋል፡፡

በፈተናው 48.5 በመቶ በላይ ተማሪዎች ከ350 በላይ፣ 59 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ማምጣታቸው ተገልጿል፡፡

የዘንድሮ ከፍተኛ ውጤት 645 ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኤጄንሲው ከትናንት በስቲያ ውጤት እንደሚለቀቅ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ለሁለት ቀናት እንደሚዘገይ በመግለጽ ይቅርታ ጠይቆ ነበር፡፡

ከሁለት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንደሚገልጽ ባሳወቀው መሠረትም ዛሬ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ ውጤቱን ተማሪዎች የመለያ ኮዳቸውን በማስገባት በኤጀንሲው ድረገጽ መመልከት ጀምረዋል፡፡

ከውጤት ይፋ መደረጉ በተጨማሪ ከፈተና ደንብ መተላለፍ ጋር በተያያዘ በወቅቱ የቀረቡ ሪፖርችንና መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የ68 ተማሪዎች ውጤት ሙሉ በሙሉ መሠረዙም ታውቋል፡፡

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝች እና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የ846 ተፈታኞች የተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች ያገኟቸውን ውጤቶች ማጣራትን የሚጠይቅ ሆኖ እንደተገኘ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የእነዚህ ተማሪዎች ውጤት በተለዩት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ ውጤታቸው ተይዞ ተጨማሪ ማጣራት እንዲደረግበት እንደወሰነም አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት በተውጣጣ ግብረ ኃይል የሚያደረገው የማጣራት ሥራ እንዲሳካና የጀመረውን የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ጅምር ሥራ እንዲጠናከር የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዳይለይውም ጠይቋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply