ብሔርተኝነት Vs ኢትዮጵያዊነት (መሀመድ አሊ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በብሔርተኝነት መደራጀት የተለዬ ችሎታና የፖለቲካ ብቃት አይጠይቅም። የሃይማኖት ልዩነትን መሠረት አድርጎ መሰባሰብም እንዲሁ ነው። ያኛው/እነዚያኞቹ “ጠላቶችህ ናቸው” ማለት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። “ዘላቂ ጥቅምህን ሊጎዱና ህልውናህን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ; መቼም የማይተኙልህ ናቸው በሚል ብቻ በሥጋት ልትሞላው ትችላለህ። ጥቅምና ህልውናውን ጥያቄ ውስጥ አስገብተህ ለዚህ “አለኝታህ እኔ ነኝ” በማለት ብቻ እንደፈለክ ልትጋልበው ትችላለህ። ስለተፈፀመበት በደል ወይም ስለተወጠነለት ሴራ ደጋግመህ እየነገርክ አንተን ከማመንና ከመከተል ውጭ ሌሎች አማራጮችን; ግራ ቀኝ እንዳያይ እንደጋሪ ፈረስ ትሸብበዋለህ። ሌሎችን እንዳይሰማም በጥላቻ ድስኩር ታደነቁረዋለህ። በዚህ መልኩ እየመራህ/እየገፋህ ወደፈለከው አቅጫ; ወደ ገደል አፋፍም ቢሆን ልትወስደው ትችላለህ።

የብሔርተኝነት ፖለቲካ የጠራ አይዲዮሎጅና የፖለቲካ ራዕይ እንዲኖርህ ግድ አይልም። በባህሪውም ስትራቴጂያዊ እይታህን ይጋርድብሃል። እናም ጭፍን ያደርግሃል። በደመ-ነፍስ ብቻ እየተንቀሳቀስክ ወደማታውቀው አቅጣጫ ታመራለህ። ከጀመርከው ጉዞ የሚገታህና የሚያግዲህ ነገር ላይኖር ይችላል። በቁልቁለት እንደመንደርደር ልትቆጥረው ትችላለህ። ተንደርድረህ ማረፊያህ/መውደቂያህ ግን በቀላሉ የማትወጣው አዘቅጥ ሊሆን ይችላል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያዊነት ውስብስብና ፈታኝ ነው። እንደብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለስሜት ቅርብ አይደለም። አስተሳሰቡ ሰዎችን “እነሱና እኛ” በሚል አጥር ከልለህ በተበዳይነትና በጥላቻ ስሜት እንድትሸብባቸው አይፈቅድልህም። ይልቁንም እርስ በርስ ሊያስተሳስሯቸው የሚችሉ ባለብዙ ቀለም ክሮችን ፍለጋ ልትናውዝ ትችላለህ። እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ ክሮችን ብታገኝም የተለያዬ እምነትና ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ማስተሳሰር ከፍተኛ ብልሃትና ትዕግስትን ይጠይቃል።

በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ዙሪያ ተደራጅቶ መጓዝ እልህ አስጨራሽ ሊሆን ይችላል። ሂደቱ አልጋ በአልጋ አይደለም። ይልቁንም በብዙ ውጣ-ውረዶች የተሞላና አድካሚ ነው። አቀበት እንደመውጣት ልትቆጥረው ትችላለህ። አቀበቱን ከወጣኸው ግን ከፍታው ላይ ትደርሳለህ። ከፍታው ላይ ቆመህ የሞራል የበላይነትህን ልታውጅ ትችላለህ።

ወገኖቼ:- ቁልቁለቱን ትተን አቀበቱን ብንወጣ አይሻልም? መቼም ደካሞች ካልሆን በስተቀር በቁልቁለቱ ተንደርድረን አዘቅጥ ውስጥ መውደቅን የምንመርጥ አይመስለኝም።

Share.

About Author

Leave A Reply