ብርሀኑ ነጋ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መቆየቱ ጠቀመን እንጂ ምን ጎዳን?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፕሮፍ ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ መሪ መሆን ቅሬታ የፈጠረባቸው አሉ። ከሚሰጡት ምክኒያቶች አንዱ “አርባ ዐመት ፖለቲካ ውስጥ ቆየ ይብቃው…..” ይገኝበታል።

ጎበዝ የብሬ በፖለቲካው አርባ ዐመት መቆየቱ ይበልጡኑ ተመራጭ ሊያደርገውና ሊጠቅም እንጂ ሊገዳ አይችልም። ሲጀምር ብሬ ወጥ አርባ ዐመት ፖለቲካ ውስጥ አልነበረም። በአፍላ ወጣትነቱን የተቀላቀለው ኢሕአፓ ውስጥ የነበረው ተሳትፎ የአመራሩ (ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ) ሹፌር በመሆንና ቀሪ ቆይታውን በአሲንባ በረኃ ነበር ያሳለፈው። በኢሕአፓ ውስጥ የነበረውን ቆይታ እናስላው ቢባል ዐመታት ከማለት ይልቅ ወራቶች የሚለው በተሻለ ይገልጸዋል።

በአሲንባ ውስጥ የነበሩት የኢሕአሠ አመራሮች ፍጹም አንባገነንነት አባላቱን ለሞትና ስደት ዳርጓል። የዚህ ሰለባ ከነበሩት ውስጥ ብሬ አንዱ ነበር። ብሬ ከታሰበለት የሞት ፍርድ ተርፎ ለስደት ተዳርጓል።

የብሬ የስደት ዘመን የከፍታ ነበር ማለት ይቻላል።

ብሬ በስደት ዘመኑ እንደ አብዛኛው የዲያስፖራ ፖለቲከኛ ሀገር ውስጥ ላሉ ፖለቲካ ፖርቲዎች የብር ድጋፍ እያደረገ እጃቸውን ሲጠመዝዝና እከሌ አመራር ካልሆነ ድጋፍ አቋርጣለሁ እያለ አልኖረም። ይልቅ በትምሕርቱ ገፍቶ ራሱን በዕውቀት አደረጀ፤ በአንጋፋ ዩኒቨርስቲም በመምሕርነት እስከማገልገል ደረሰ፣ አገባ ወለደ ከበደ።

ረጅም የሚባል ዐመታትን ከፖለቲካ ርቆ በስደት ያሳለፈው ብሬ፤ ከፖለቲካ ባሻገር ሀገሩን ለማገልገል ጓዙን ጠቅልሎ ሀገሩ ገባ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስት እስከ ነጻ አገልግሎት በደረሰ በመምህርነት አገለገለ። የኢኮኖሚክስ ሙያ ማኅበራትን በማደራጀትም አገልግሎቱን ከፍ አደረገ።

የብሬ ዳግም ወደ ፖለቲካው መግባት

አንድም የምሁራን በሀገር ጉዳይ(በተለይም በፖለቲካው) የሚያሳዩት ዳተኝነት እጅጉን መብጠልጠል፤ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ ተጋብዞ ስለአካዳሚክ ነጻነት ላይ ያሳየው ተሳትፎ በመንግሥት ያልተወደደለት ብሬ ለእሥር ተዳረገ።

ከላይ የጠቀስኩልኽን ሁለት ገፊ ምክኒያቶች ያዝና 1997ዓ.ም ላይ ስትመጣ የወቅቱን የፖለቲካ ግለት ታገኛለኽ። የታየውን አንጻራዊ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ስታስታዉስ የብሬን ዳግም ወደ ፖለቲካው መግባት አንድም በቂ ምክኒያት ያለው ዐለፍ ሲልም የዜግነት ግዴታው መሆኑን ትረዳለኽ።

የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውና ስለቅንጅት ፓርቲ የፖለቲካ ሱታፌውና ከዛ በኋላ በሕይወቱ ስለተበየነበት ዳግም የሞት ፍርድ አናወራም።

ይልቅ የብሬን ትላንት በተመሠረተው “ኢዜማ” ፓርቲ ላይ ዛሬ የሊቀመንበርነት ቦታውን መቆናጠጥ ትክክለኛነት አድምቀን እንዝጋው።

ብሬ ከፍፍፍ ያለ የምጣኔ ሀብት ዕውቀት አለው፣ የኢትዮጲያን ታሪክ ጣፊያና ብልቱን በዘርፍ በዘርፍ ጠንቅቆ የተረዳ ነው፣ የነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ ቀላል የሚባል አይደለም፣ አንባቢ ነው፣ ነቄ ያራዳ ልጅ ነው፣ ደብረ ዘይት ይወለድ እንጅ ማሊያው የፒያሳ ልጅ ነው፣ ሀብታም ነው ……. ብዙ ነው።  በርግጥ የፖለቲካ ሀ ሁ የጀመርከው ክልሎች በንቅናቄዎች መነቅነቅ ከጀመሩ በኋላ ከሆነ ብሬን መረዳት ዳገት ሊሆንብህ ይችላል።

የዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል ብሬ የኢትዮጲያ ጠሚ ሲሆን እመለስበታለሁ።

(ጆ ማን መርጉ)

Share.

About Author

Leave A Reply