ተስፋን አጨልሜ ከመፀፀት የቻልኩትን ያህል አበርክቼ ባይሳካልኝ፣ ብሸወድና ባዝን እመርጣለሁ!! ገመቹ መረራ ፋና

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አንድ መንግሥት ነው የማውቀው፤ ኢህአዴግን። ደርግ ሲወድቅ ብዙ የማስታውሰው ነገር የለም። በሚኖሩበት አካባቢ ሰው የተጠሉ፣ በሥነ ምግባራቸው የዘቀጡ፣ በሌብነታቸው ወደር የሌላቸው፣ ሕዝቡን ለሞት፣ ለእስር እና ለስደት ዳርገው ሰላማዊ እንቅልፍ ተኝተው የሚያድሩ፣ ሀገር ሳይሆን ቤተሰብ ማስተዳደር የማይችሉ፣ እንጥፍጣፊ የሕሊና ጥያቄ የሌለባቸው ሰዎችን አምጥቶ ለዘመናት ያሰለጠነብንን ኢህአዴግን ነው የማውቀው።

ባወቅኩት ጊዜ ሁሉ «አጋምን የተጠጋ ቁልቋል» ሆኜ ሳለቅስ ኖሬኣለሁ። በግፍ ያለጥፋቱ በፖለቲካ ምክንያት ታስሮ የሚያውቅ ሰው ጓደኛ ነኝ። በግፍ ያለጥፋቱ በፖለቲካ ምክንያት ታስሮ የሚያውቅ ሰው አድናቂ እና ተስፋ አድራጊ ነኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በግፍ ያለጥፋቱ በፖለቲካ ምክንያት ታስሮ የሚያውቅ ሰው ልጅ ነኝ። የነዚህ ሰዎች ቤተሰብ ሆኖ በሰቆቃው ከመሰቃየት፣ በሰዎቹ ቦታ እስረኛ መሆን እንደሚሻል አምናለሁ። እናም ከግፍ እስር መፈታት፣ ከሞት ፍርድ ሁሉ ጋር ለተፋጠጡት ዓላማ ላላቸው ለእስረኞቹ ሳይሆን ለቤተሰቦቻቸው ምን ማለት እንደሆነ አሳምሮ ይገባኛል። ይሆናል ብዬ በማላስበው፣ ለማመን በቸገረኝ መጠን እና ሁኔታ፣ ለያውም ኢህአዴግ ራሱ በሥልጣን ላይ እያለ ይሄ ሰቆቃ ሲያልፍላቸው ማየቴ አሁንም ይደንቀኛል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ ብዬ አውቃለሁ፤ «ኢህአዴግ ከሁሉም የከፋው ትልቁ በደሉ ሀገራችንን አማራጭ ተተኪ የሚሆን ተቃዋሚ/ተገዳዳሪ ፓርቲና መሪዎች ማሳጣቱ ነው»። እንዲህም ብዬ አውቃለሁ፤ «የኢህአዴግ ብቸኛው ሥርየት ቢዘገይም የማይቀርለትን ውድቀት ተገንዝቦ ሕዝቡ በፍትሓዊ ምርጫ ለመወዳደር የሚችሉ አቅም ያላቸው አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩት ያደረገ እንደሆነ ብቻ ነው»። አይቀሬው ውድቀቱ በጉልበት የመጣ እንደሆን በየመንደሩ በሚነሱ አደገኛ የጎበዝ አለቆች ፉክክር ምክንያት ከማንወጣበት አዘቅት ውስጥ ከመግባት የሚያድነን ተስፋችን ይህ ብቻ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ነበር ሥርየት ይሆንለታል ያልኩት። አሁን አንድ ይሄንን ሥርየት ያሳካል ብዬ የማምንበት ሰው በኦቦ ለማ መገርሣ ክስተትነት አግኝቻለሁ። ዶ/ር አብይ አህመድን። ድርጅቱን ሳይሆን ግለሰቡን። እሱን እና በዙሪያው ያሉ «ሀገር» የምትታያቸውን ጥቂት ሰዎችን።

ይኼንን ተስፋዬን የሚያሳጣኝ ነገር እስኪከሰት ድረስ ይሄ ፎቶ በከቨር ፎቶነት ይቀመጣል። በምችለው ሁሉ ቀናውን እያሰብኩ የበኩሌን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ። ዳር ቆሜ በትችት ናዳ ዕውነተኛ ተስፋን አጨልሜ ከመፀፀት የቻልኩትን ያህል በእምነት አበርክቼ ባይሳካልኝ፣ ብሸወድና ባዝን እመርጣለሁ!!

ገመቹ መረራ ፋና

ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ/ም

Share.

About Author

Leave A Reply