ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ “የፊደል ገበታ” አባት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መጋቢት 22/2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆነው ፊደልን በበለጠ ያዳበሩትና መሃይምነትን ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ዘ ብሄረ ቡልጋ የተዘከሩበት እለት ነው:: እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ‹‹የፊደል ገበታን›› ለህዝብ ያበረከቱ የተማረ ትውልድ እንዲበዛ በኋለኛው ዘመን ጠንክረው የሰሩና ይህ አንፀባራቂ ታሪካቸው ከትውልድ ትውልድ ተሻግሮ በዚህኛው ዘመንም ቢሆን ትልቅ ዋጋ የሚያሰጣቸው የፊደል አባት ለመሆን በቅተዋል::

በቡልጋ የተወለዱት ተስፋ ገብረስላሴ በወጣትነት እድሜያቸው ያቋቋሙት ማተሚያ ቤት ዛሬም በቦታው ላይ ቢገኝም፤ ለአገር ፋይዳ ያላቸው በርካታ ስራዎችን ያበረከተው ይህ የህትመት ስፍራ አሁን የተጋረጠበት ችግር በርከት ያለ መሆኑን በዚህ ታሪካዊ ክብረ በአል ወቅት ለመታዘብ ችለናል:: ሮምሀይ ኤቨንትስና ኦርጋናይዝ ከተስፋ ገብረ ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር በራስ አምባ ሆቴል ያዘጋጁት ዝክረ100ኛ አመት ላይ ታላቁ የፊደል ሰው በተገቢው መንገድ ተከብረዋል፣ተወድሰዋል ማለት ይቻላል:: የቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ባለቤት፣ልጆች፣የልጅ ልጆች ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት በደማቅ ስነስረአት የተከናወነውን ዝግጅት የተከታተለው የግዮን ባልደረባ ክብረ በአሉን በዚህ መልክ ያስቃኘናል::

የተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቤት ጉብኝት “እውቀት ይስፋ፣ድንቁርና ይጥፋ፣ ይህን ይላል የኢትዮጵያ ተስፋ” በሚል መርህ ቃል እየታገዙ ፊደልን፣ ግፅዝንና ሌሎች የእውቀት ማዳበሪያ ፅሁፎችን በማተም ስራውን የጀመረው ተስፋ ገብረሰላሴ ማተሚያ ቤት በሚገኝበት (4 ኪሎ ከቱሪሰት ሆቴል ገባ ብሎ) ስፍራ ስንደርስ ማተሚያ ቤቱ በብዙ መልኩ ከዕይታ ተሰውሮ ነበር:: ለበርካታ ዘመናት የአካባቢው ልዩ ምልክት ሆኖ መግቢያና መውጫው ከፊት ለፊት የሚታየው እድሜ ጠገቡ፤ ታሪካዊው ማተሚያ ቤት ዛሬ በየት በኩል እንደሚገባ የሚገልጽ አመላካች ወይም ጠቋሚ ማስታወቂያ የለውም:: ቢኖረውም ዙሪያውን በከበቡት አዳዲስ ግንባታዎችና ጅምር ፎቆች የተዋጠ በመሆኑ በፍለጋ መድከም ግድ ይሆናል::

ማተሚያ ቤቱ በቤት እድሳትና ለውጥ ደረጃ በተለያየ ጊዜ የግንባታ እድሳት የተደረገለት ቢሆንም በህትመቱ ዘርፍ ግን ከቆየበት ዘመን አንፃር አጥጋቢ ለውጥና ትልቅ እመርታ አሳይቷል ማለት አይቻልም:: ማተሚያ ቤቱ በተለያ ስርአቶች ውስጥ እንደማለፉ በየጊዜው እድገትና ለውጡን ለማምጣት በሚንቀሳቀስበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ብናውቅም “ተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቤት” ቅርስ የመሆኑን ያህል ተገቢው ትኩረት በሚመለከታቸው አካላት ተሰጥቶታል:: ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም:: አሁን ያሉትና ዘመናዊ ናቸው ተብለው የተተከሉት ማሽኖች ከሌሎች የግል ማተሚያ ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ “የፊደል ገበታ” አባት ቤቶች አንፃር ሲተይ በተወሰነ መልኩ ወደኋላ የመቅረት ሁኔታ በግልፅ ይስተዋልበታል::

የተስፋ ገብረስላሴ ልጆችና የልጅ ልጆች ብሎም የቅርብ ሰዎች በዚህ ዙሪያ ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል:: በመንግስት ረገድም ቢሆን ማተሚያ ቤቱ ቅርስነቱን ጠብቆ ባለበት ቦታ እንዲቆይ ከማድረግ ባሻገር ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል ብለን እናምንለን:: ታሪካዊ ስራን በፎቅ እየጋረዱና እያጥለቀለቁ ልማት ነው ማለት ብዙም አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም:: ጋዜጣዊ መግለጫውና ቀጣይ ስራዎች በእለቱ በራስ አምባ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ጥበቡ ተስፋ ገብረስላሴ፣ቆንጂት ተስፋ ገብረስላሴና ጥሩ ወርቅ ተስፋ ገብረስላሴ ፕሮግራሙ የአባታቸውን ታሪክ ከመዘከርና የማተሚያ ቤቱን ክብረ በአል ከማክበር ባሻገር ወደፊት ሊሰሯቸው ያሰቧቸውን ስራዎች በመጠኑም ቢሆን ለመግለፅ ሞክረዋል:: ተስፋ ገብረስላሴ ከፊደል ገበታና ህትመት ዘርፍ ባሻገር በጦር ሜዳ ላደረጉት ተጋድሎየቀኝ አዝማች ማዕረግ በጊዜው የተቸራቸው ቢሆንም አሁን ላይ ግን እሳቸውን የሚዘክር ቋሚ ሐውልት፣መንገድ፣ ትምህርት ቤት ወይም የጤና ተቋም አለመኖሩ ብዙዎችን አሳዝኗል::

ይህን ያህል የተለያዩ አኩሪ ገድሎችን የሰሩ አባት አስቀምጦ ለትናንሾችና ለውጪ አገር ዜጎች ሐውልት ለማቆም የሚሯሯጠው የመንግስት አካል በርግጥ የሚሰራውን ያውቃልን? እንድንል አስገድዶናል:: ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ስላሴ ለሰሩት ስራ መታሰብያ ይሆን ዘንድ ያለ ማንም ግፊትና ጥያቄ በራሱ ተነሳሽነት አቢሲኒይ ባንክ አራት ኪሎ የሚገኘውን ባንኩን ‹‹ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ስላሴ ቅርንጫፍ›› በማለት ሰይሞታል:: ይሄ ሊወደስና ሊደነቅ የሚገባ በጎ ተግበር ነው:: ከዚህ በዘለለ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር አንድ ታሪካዊ መዘከሪያ ለእኚህ ሰው መደረግ ያለበት ከመሆኑ አኳያ እዚህ ላይ ሌሉች መንግስታዊና የግል ተቋማት ከአቢሲኒያ ባንክ መማር አለባቸው ብለን እናምናለን:: ማተማያ ቤቱን በቀጣይነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አቶ ተስፋ ገብረስላሴ የሰሩትን አኩሪ ተግባር ለአለም ህብረተሰብ በስፋት ለማስተዋወቅ እንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ፕሮፌሰር ጋር ግንኙነት እንደተፈጠረ ያወሱት አቶ ጥበቡ የተስፋ ማተሚያ ቤት ችግር በአስቸኳይ ይፈታ ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ለሚመለከታቸው አካል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል::

ተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቀደም ሲል ከነበረው 7000 (ሰባት ሺህ) ካሬ ሜትር በግንባታ ሰበብ መንግስት አብዛኛውን ቦታ ወስዶበት ለሌላ ተቋማት አስረክቦታል:: አሁን የቀረችው 2500 ካሬ ሜትር ላይ ይህንን ሁሉ ቀጣይ ስራ እንዴት ብለው እንደሚያከናውኑና ዕድገቱን በምን አይነት ሁኔታ እንደሚያፋጥኑ የቸገራቸው መሆኑን የቀኝ አዝማች ልጆች ይናገራሉ:: ማተሚያ ቤቱን ህጋዊ እውቅና ሰጥቶ የመዘገበው የቱሪዝምና ቅርስ ባለስልጣን፤ አዳዲስ ግንባታዎች ሲካሄዱ የሚያዘውን የ20 ሜትር ርቀት ባልጠበቀ ሁኔታ አዲስ አካል ማተሚያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ቁፋሮ ሲያከናውን “ይህ ቦታ ቅርስ ነውና በህግ በተፈቀደው ሜትር ርቀት ላይ ስሩ” ብሎ መፍትሔ ማፈላለግ ወይም ድርጊቱን ማስቆም አልቻለም::

እየተሰራ ያለው ነገር ከአንድ ተቋም ፍላጎትና መመሪያ ውጪ ከሆነ አሰሪው አካል ማን ቢሆን ነው? የሚል ጥያቄ መጫሩ አልቀረም:: የክብረ በአሉ አድማቂ ዝግጅቶች በጋዜጠኞች የማተሚያ ቤቱ ጉብኝትና በፕሬስ ኮንፈረንሱ ምክንያት በአዳራሽ ለበርካታ ደቂቃዎች በትዕግስት የዝግጅቱን መጀመር ሲጠባበቅ የቆየው ታዳሚ የቀኝ አዝማች ገብረ ስላሴ ባለቤትና ልጆች ወደ አዳራሹ ሲገቡ በደማቅ ጭብጨባ ተቀብሏቸዋል:: ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ሊያስብል በሚችል መልኩ በማተሚያ ቤቱ ክብረ በአል ላይ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው ታጅበው የተገኙት የቀኝአዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ባለቤት ወ/ሮ አለሚቱ ንጉሴ የመቶ አመት የእድሜ ባለፀጋ ሆነዋል:: የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት አቶ ጥበቡ ገ/ስላሴ ክብረ በአሉን ለማከናወን የታሰበው ከአንድ ወር በፊት የካቲት 22 ቀን ቢሆንም በወቅቱ በነበረው ያለመረጋጋት ችግር ምክንያት በጊዜው ፈቃድ ሳያገኙ ቢቀሩም ዘግይቶም ቢሆን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ይህን ደማቅ በአል ለማካሄድ እንደበቁ ገልፀዋል::

ከሐይማኖት አባቶች መጠነኛ ትምህርትና ቡራኬ በኋላ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የምሳ ግብዣ የተካሄደላቸው ሲሆን በፕሮግራሙ መሃል የቀኘ አዝማች ተስፋ ገ/ስላሴን የህይወት ታሪክ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ቀርቧል:: ዘማሪት የትምወርቅ ያቀረበችው የበገና ድርድርም ታዳሚውን በእጅጉ ያስደሰተ ነበር:: መዲናና ዘለሰኛ በመሰንቆ፣ የቆሎ ተማሪዎች ዝግጅት፣ ወረብና ቅኔ የፕሮግራሙ ማድመቂያ ሆነው የቀረቡበት “የፊደል ገበታ” አባት የሆኑት የተስፋ ገ/ስላሴ ማተሚያ ቤት 100ኛ አመት በአል ሲከበር ታላቁ ሰው በህይወት ቢኖሩ የ119 አመት የእድሜ ባለፀጋ ሆነው በህይወት እናያቸው ነበር:: መልካም ስራ ዘመን ተሻጋሪ ነውና እሳቸው በአካል ባይኖሩም ልጆቻቸው በዚህ ዘመን ላይ ሆነን “እውቀት ይስፋ፣መሐይምነት ይጥፋ፣ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› እንድንል አድርገውናል::

Share.

About Author

Leave A Reply