ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ! (ኤፍሬም እንዳለ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

‘ዳያስፖራ’ ነው፣ ከረምረም ብሎ ሊያየን ይመጣል፡፡ ከወዳጆቹ ጋር ማታ፣ ማታ ዞር፣ ዞር ይላል፡፡ እና በእሱ ድምዳሜ አገራችንን አያት፣ የቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ፣ የቺቺንያ አካባቢ ሌሊት ህይወት የእኛ ኑሮ መለኪያ ሆነለት፣ ወሰነም… “ተመችቷችሁ የለም እንዴ!” አለ፡፡

“ኸረ እባክህ አልተመቸንም! የእኛን ኑሮ ለማወቅ የሌሊቷን ቺቺንያ ሳይሆን የቀኗን የእኛን ጓዳ ጓዳችንን ተመልከት” ተባለ፡ በእጄ አላለም፡፡ እዚህ አገር እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነችና እሱ እድለኛ እንደሆነ ምናምን ነገር ይነግሩታል፡፡ ለካስ እሱ አሜሪካ አልተመቸችውም፡፡ ምን በል ጥሩ ነው… “እናንተ ምን አለባችሁ!”

“እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር ምንድነው? ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገር አለብን እንጂ!
ኑሮ እያደቀቀን፣ ብሶታችንን የሚሰማን እያጣን… “ኸረ ወገኖቻችን ከሰውነት ውጪ ሆኑ!” የሚል እያጣን ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገር አለብን እንጂ!

መፈጠርን የሚያስጠላ ደረጃ የሚያደርስ የቤት ኪራይ አለብን፡፡ ያውም በየሦስት ወሩ የሚጨምር…ያውም አሮጌ ወንበር ስናስጠግን በታየ ቁጥር የሚጨምር…ያውም ግንባራችን ላይ የተንጠፈጠፈው ላብ የምቾት ሆኖ በታየ ቁጥር የሚጨምር፡፡

የሆነ ታሪክ ነው…እዚቹ አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ ሰውየው አንዲት በጣም ጠባብ የሆነች፣ እግር እንኳን ሙሉ ለሙሉ የማይዘረጋባት ክፍል ተከራይቶ ይኖራል፡፡ ያከራዩት እናት ማንንም ሰው እንዳያመጣ አስጠንቅቀውታል፡፡ አንድ ጊዜ የሆነ ወዳጁ ችግር ይገጥመውና ደብቆ ሊያሳደረው ቤቱ ይወስደዋል፡፡

እንግዳውን “እግርህነ ሰብስብ፣” ካለ በኋላ በሩን የጠረቅመዋል፡፡ እንግዳው በሌሊት ወጥቶ ይሄዳል፡፡ ጠዋት ላይ አከራዩዋ ይመጡና ተከራዩን “ውጣልኝ፣” ይሉታል፡፡ “ምን አጠፋሁ?” ይላቸዋል፡፡ ለካስ ሴትዮዋ ማታ እንግዳው እግሩን ሳይሰበስብ በፊት ጫማውን አይተውት ኖሯል፡፡ ተከራዩም ወጣ፡፡ እንዲህ አይነት ኖሮ እየተኖረ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

ሰዎች ከትውልድ ቀዬአቸው ወጥተው በሌላ አካባቢ ንብረት አፍርተው፣ ቤተሰብ መስርተው፣ ወልደው፣ ከብድው ለአስርት ዓመታት ከኖሩበት ስፍራ “ውጡልን፣ ድራሻችሁ ይጥፋ!” እየተባሉ የትናንት አምራቾች፣ የዛሬ ተፈናቃይ እርዳተያ ጠባቂዎች ሲሆኑ እየታየ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ!

ምግብ ለመመገብ እኮ የምንሳቀቅበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ማኛ ጤፍ ኮመኮምን ካልን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሆዳችንን የቀሺም ፊልም ግድግዳ የሚነቀንቅ ‘ሳውንድትራክ’ የሚያደርገው የተቀላቀለበት ጄሶ ሊሆን የሚችልበት ጊዜ ላይ እኮ ነው፡፡ አዎ፣ ጄሶ ነው የተባለው! (ለግንባታ ሥራ “ዋጋው ጣራ ነካ፣” የሚባለው ጄሶ ከጤፍ ለመቀላቀል ከየት አነደሚገኝ አንድዬ የወቀው፡፡)

“ይሄ በርበሬ መልኩ ደስ አይልም! እንዲሁ ቃሙኝ፣ ቃሙኝ ነው እኮ የሚለው፣” ያልንለት በርበሬ እኮ ከቅመሙ ብዛት ይልቅ የቀይ ሸክላ ዱቄቱ በእጥፍ የበዛበት ሊሆን የሚችልበት ዘመን እኮ ነው! ከሆነ ገበያ “የአገልግሎት ጊዜው ገና አንድ ዓመት ይቀረዋል፣” ያልነው የታሸገ ምግብ ምናልባትም የአገልግሎት ጊዜው ከዓመት ከመንፈቅ በፊት ያለቀ ሊሆን የሚችለበት ዘመን እኮ ነው! ይሄ ሁሉ እያለ…“እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ!

በአቅም በልቶ ማደር፣ በቀን ሦስቴ መመገብ መሰረታዊ የሰበአዊ መብት ጉዳይ ሳይሆን ለጥቂት እድለኞች የተሰጠ ቡራኬ ቢመልስን ክፉ ጥሪ ሆነን ሳይሆን የቤታችን ጓዳ፣ የሆዳችን ጓዳ እንደዛ እንድንል ሰለሚገፋፉን ነው፡፡

አየህ ወዳጄ…አንተ እንዳልህበት ስፍራ ሲርበን ዘው ብለን የምንገባበት ‘ሱፕ ኪችን’ ምናምን የለንም፡፡ አንተ እንዳልህበት በጥቂት ዶላር ገዝተን ሦስትና አራት ቀናት የምንመገበው የቻይና ምግብ እንደልብ የምናገኝበት አይደለም፡፡ አየህ ወዳጄ… አንተ ዘንድ ለሁሉም የሆኑት የቻይና ምግቦች፣ በርገሮችና መናኖች እዚህ የሀብታም ምግብ ናቸው፡፡ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ስትል ይህንን ሁሉ እይልና!

አንተ አገር ምግብ ማገኘት የመሰረታዊ ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፣ አነተ አገርና አውሮፓ ወተት ከእናንተ እየተረፋችሁ ትደፉታላችሁ፡፡ አኛ ዘንድ ውሀ የተቀላቀለባትና የወንዝ ውህ ልትመስል ምንም ያልቀራት አንዷ ሊትር ወተት ስንት እንደታወጣ ብነግርህ ለአነጋገረህ ይጸጽትህ ነበር፡፡ ታዲያ… የሀበሻ ልጆች ምነዋ አይኮሰምኑ! ምነዋ ከሰውነት ውጪ አይሆኑ! ምነዋ አሰኮናኝ አይሆኑ! በምግብ እጦት ራሳቸውን የሚስቱ ህጻናት ያሉባቸው ትምህርት ቤቶች ያሉባት አገር እኮ ነች!

የፈረንሳዩዋ ንግሥት ማሪ አንቷኔት ነች ማነች የሚሏት…“ዳቦ” ብሎ ለሚጮኸው ህዝቧ “ለምን ኬክ አይበሉም፣” ብላ ነበር አሉ፣ በኋላ ላይ አንገቷን ሊቀሏት! ይኸውልህ ወዳጄ… እኛ ዘንድ አፍ አውጥተውም ባይሆን በድርጊታቸው “ዳቦ” ስንል… “ለምን ኬክ አትበሉም…” ይሉን የሚመስሉ በጸጉራችን ልክ አሉልህ፡፡ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ስትል ይህንን ሁሉ እይልና! ብዙ፣ በጣም በዙ አለብን፡፡

የእዛ ሰፈር ልጆች በአየገሩ ምርጥ ኮሌጆች ሄደው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ትምህርት የሚያገኙበት፣ የዚህ ሰፈር ልጆች አይደለም ድንበር ሊሻገር፣ ለአገር የማይተርፍ ለብ፣ ለብ ትምህርት የሚያገኙበት ዘመን እኮ ነው! ትናንት፣ ከትናንት ወዲያ ይህግ ተማሪዎቻችን በዓለም አቀፍ ውድድር ያሸንፉ እንዳልነበሩ አሁን የትምህርት ጥራት የሚባል ነገር እኮ ትልቁ ራስ ምታታችን የሆነበት ዘመን ነው፡፡

ጭራሽ… “በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ በየቦታው የገባህ ሁሉ ራስህን አጋልጥ!” የሚባልበት ዘመን እኮ ነው፡፡ ትናተ ለኢነፌክሽን መርፌ የወጋችን ባለሙያ ‘ፎርጅድ’ ልትሆን የመትችልበት ዘመን አኮ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እያለ… “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

ዳያስፖራው ወገኔ… ‘መልካም አስተዳደር’ ምናምን የሚሉ ነገሮች በዩቲዩብ አይለጠፉም እንዴ! አየህ… ‘የመልካም አስተዳደር ችግር’ የሚባለው ነገር ቤታችንን ብቻ ሳይሆን አገር እየነቀነቀ ነው፡፡ አንተ ባለህበት ባለሀበት አይደለም በአስዳደር ጉድለት ሰው እያስለቀሰ፣ አይደለም በአገልግሎት ድክመትና ወገንተኝነት ትንሽ ትልቁን እያስለቀሰ “እከሊት የተባለችውን ሠራተኛ በአጠገቡ ስታልፍ ክንዷን ቸብ አድርጓል፣” ተብሎ ‘ቀይ ካርድ’ የሚሰጥበት ነው፡፡ እንዲሀ አይነት ወሬ ለእኛ ቆንጆ ልእልት እንደሆነችው እንቁራሪት የልጅነት አይነት ህልም ነው፡፡

አየህልኝ ወዳጄ…እዚህ ‘ቀይ ካርዱ’ በአስተዳደሩ ለበደለህ ሰው ሳይሆን “የፍትህ ያለህ፣ ተበደልኩኝ…” ላልከው ለአንተ ነው፡፡ ገና አንድ ነገር ስትናገር ኪም ኢል ሱንግ የሚተኩሷቸውን ሚሳይሎች አቅም ያለው የውግዘት ናዳ ይደርስብሀል፡፡ ሀሳብህን አይሞግቱትም፡፡ “እስቲ አስረዳ፣ ማስረጃ አቅርብ…” አትባልም፡፡ ይልቁንም ወዳጄ… “ልማት ለማደናቀፈ ስውር ዓላማ ያለው ነው…” ትባላለህ፡፡

ይልቁንም ወዳጄ… “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የውጪ ሀይሎች አገራችንን የማተራመስ አላማ አስፈጻሚ ነህ…” ተባላላህ፡፡ ይለቁንም ወዳጄ… እድሜህ ሀያ አጋማሽ ላይ እንኳን ሆኖ “የድሮ ናፋቂ፣ የንጉሡን ፊውዳላዊ ስርአት ለመመለስ የሚፈልግ…” እይትባልክ እንትን የነካው እንጨት ትደረጋለህ፡፡ ይሄ ሁሉ ባለበት ጊዜ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

በምትጠጣው ቢራ እየተፈረጅክ፣ በምትደግፈው የእግር ኳስ ቡድን እየተፈረጅክ፣ በምታዳምጠው ኤፍ.ኤም. ሬድዮ ጣቢያ እየተፈረጅክ፣ በምታዘወትረው መዝናኛ ስፍራ እየተፈረጅክ ምቾታችን ምን ላይ ነው! ወዳጄ… አንተ በድዋይዘር ስለጠጣህ ትፈረጃለህ እንዴ!! ቢቢሲ ሬድዮ ሰማህ፣ ፒ.ቢ.ኤስ ሰማህ ተብለህ የእኛና የእነሱ ተብለህ ትፈረጃለህ እንዴ!…አንተ ሳም ኵክን ብትሰማ፣ ፍራንክ ሲናትራን ብትሰማ፣ ሄሚንግዌይን ብታነብ… “የድሮ ናፋቂ” ትባላለህ እንዴ!…ተው እንጂ ጊዜ “እናንተ ምን አለባችሁ!” አትበለን! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

ለሚስቱ ዳይመንድ፣ ለልጁ ፕሌይስቴሽን፣ ለእንትንዬው ቪትዝ የሚያቀረበውን የቺቺንያው መንደረተኛ የእኛ ኑሮ መለኪያ ማድረግ ልክ አይደለም፡፡ ኮንስርት፣ ፌስቲቫል ምናመን እኮ ለኑሯቸን ጣራ መንካት መስፈሪያዎች አይደሉም፡፡ እኛም የምንገረምማቸው፣ እነሱም በአቅማቸው ዘመናዊ የግንባታ ውጤቶች ሆኑና የሚገላምጡን የሚመስሉት እነኛ ሁሉ አራት ማእዘን፣ ምናመን ማእዘን ህንጻዎች እኛ “ምንም እንደሌለብን” መለኪያ መስፈርቶች አይደሉም፡፡

እዛኛው ሰፈር የልጆች ጥያቄ… “አባዬ አዲስ የወጣውን ሳምሰንግ ጋላክሲ ግዛልኝ፣” ሲሆን እዚህኛው ሰፈር ያለው ጥያቄ የሆነበት ዘመን፡፡ እዛኛው ሰፈ አባት የተባለውን ይገዛል፣ እዚህኛው ሰፈር መልሱ እናንተ በሆዷ እያለቀሰች በአንደበቷ “ታዲያ ከየት አባክ ላምጣልህ፣ እኔ ዳቦ ልሁንልህ!” በምትልበት ዘመን… “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

ካላንደር አንድ ዓመት ወደፊት ሲሄድ ኑሮ ሦስት ዓመት ወደኋላ በሚንሸራተትበት የዓለም ክፍል እያለን፣ “ደግሞ ሌላ ድርቅ መጣባቸው…” “ደግሞ ሌላ ወረርሽኝ መጣባቸው…” “ደግሞ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት መጣባቸው…” በሚባልበት ጊዜ “እናንተ ምን አለባችሁ!” ብሎ ነገር አለ እንዴ! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን እንጂ! ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

አየህ… ከታች እሰከ ላይ “ጎራዴው ሰው በላ!” የሚል በዝቶብን እኛማ ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን፡፡ አንተ ዘንድ እንኳን “ጎራዴው ሰው በላ” ብሎህ ገና በክፉ ሲያያህ 991 “ሀሎ” ትላለህ፡፡ አንተም ዘንድ መቶ በመቶ የሚባል ፍትህ ባይኖርም ከእኛ ጋር ሲተያይ ገና ደረት ሳንመታልህ መንግሥተ ሰማያት እንድገባህ ቁጠረው፡፡ እዝህ አኮ “ይልቅ ተስማማ፣” ትባላላህ፡፡

አንተ ዘንድ ጉልበተኛ ቢመጣብህ “ዝምቤን እሽ ማለት አትችልም፣” ማለት ትላለህ፡፡ እኛ ዘንድ አየደለም “ዝምቤን እሽ ማለት አትችልም፣” ገና ከአፍህ ሳይወጣ አንተኑ ዝምብ ያደርግሀል፡፡ የሚነሰንስብህ ፍሊት በብዙ መልኩ ሊመጣብህ ይችላል፡፡ አየህ ወዳጄ…እኛ ዘንድ አኮ በቴሌቪዥን ካሜራዎች ፊት፣ በብዙ ሺህ ተመልካች ፊት የእግር ኳስ ዳኛውን ትወቅጠዋለህ፡ እናንተ ዘንድ ዳኛውን አይደለም መነካት እላፊ እንኳ ቢናገሩት ምን እንደሚደርስበት ይታወቃል፡፡ ይሄ ሁሉ ባለበት “እናንተ ምን አለባችሁ፣” አትበለና! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን፡፡

አየህ… እኛ ላይ በአገር ሰላም ‘አነጣጣሪ ቅልጥም ሰባሪ’ የሚለን ሞልቷል፡፡ እኛ ዘንድ ከቤትህ ስትወጣ እያፏጨህ ሳይሆን የሰማዩን ጌታ አየተማጸንክ ነው፡፡ “ከጉልበተኛ ጭቃ ሹም፣ ከእብሪተኛ ባለስልጣን፣ ጌታውን ከተማመነ የተራ ሰው ጡንቸኛ ጠበቀን፣” እያልክ ነው የምትወጣው፡፡

አንተ ጠዋት ከቤትህ ስትወጣ የሚያሳስብህ ሜትሮ መጓጓዣው በሰዓቱ መደረስህን ነው፡፡ ስትወጣ “ከጉልበተኛ የሚጠብቀኝ የሚከበር ህግ፣ ሁም እኵል የሚገዛለት ስርአት አለ፣” ብለህ ነው፡፡ እዛ ላይ ያለችው ስቶርሚ ዳንዬልስ ላይ ጫፍ ያሉትን ትረምፕን ስትሞግት… “እንዲህ አይነት ስርአት እኛ ዘንድ በልጅ ለጆቻችን ጊዜስ እውን ይሆን ይሆን?” በምንልበት ጊዜ “እናንተ ምን አለባችሁ፣” ስትል የሄን ሁሉ እይልና!

ዳያስፖራው ወዳጄ…አየህ፣ በክፉ የሚረዳዳ፣ በችግር የሚተጋገዝ፣ “አንቺ ትብሽ እኔ” የሚባባል ህበረተሰብ ነበርን፡፡ በርካታ በጎ የማህበራዊ ኑሮ እሴቶች የነበሩን ህበረተሰብ ነበርን፡፡ ለረጅም ዘመናት ይዘናቸው በቆየናቸው ባህላዊ አለባበሶቻችን፣ አመጋባበችን፣ የደስታና የሀዘን ማህበራዊ ቁርኝታችን ለሌሎች ምሳሌ መሆን የምንችል ነበርን፡፡

አየህ… በአንድም ሆነ በአንድ ሺህ አንድ ምክንያቶች እነኛን ሁሉ እየተነፈግን፣ እየተነጠቅን ነው፡፡ ዜማችን… እንደ ጥንቱ፣ እንደ ጠዋቱ “የጋራችን”“ ሳይሆን “የግላችን” በሚል እየተተካ ነው፡፡ በሌላው ሰው ሳይሆን በራሳችን ጥላም በድንጋጤ እየዘለልን ነው፡፡ ይህ ሁሎ ባለበት “እናንተ ምን አለባችሁ!” አትበለና! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን፡፡

እኛ በምንበላውም በምንጠጣውም፣ በምናነጥሰውም ፖለቲካዊ ትንታኔ እየተፈለገበት፡ ለየእንቅስቃሴያችን ምን ብለው ይፈርጁን ይሆን እያልን እየተሳቀቅን፣ የምንስቅበትና የማንስቅበትን የማንንም መብት ይነካል በሚል ስጋት ሳይሆን “ምን ብልው ይጠመዝዙብኝ ይሆን!” እያለን እየተሳቀቅን ጓዳችንን ሳታይ፣ ጉዳችንን ሳታይ፣ ጉድጋዳችንን ሳታይ “እናንተ ምን አለባችሁ!” አትበለና! ብዙ፣ በጣም ብዙ አለብን፡፡ ቺቺንያ ሌላ፣ እኛ ሌላ!

Share.

About Author

Leave A Reply