ነገ ለሚጀመረው 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎችና የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት ላይ ናቸው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ነገ ከሰዓት በኋላ ለሚጀመረው 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎችና የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በጅማ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ ውይይት ላይ ናቸው፡፡

ውይይቱ ዛሬን ጨምሮ እስከነገ ከሰዓት እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በውይይታቸውም በዘጠነኛው የኦህዴድ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የቀረበ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርት ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በጥቅሉ ሪፖርቱ 158 ገጾች መያዙ የተጠቀሰ ሲሆን÷ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ግምገማ፣ የስምንተኛው ድርጅታዊ መደበኛ ጉባዔ አቅጣጫ፣ የትራንስፎርሜሽንና የኢኮኖሚ አብዮት ሽግግር አፈጻጸም እና ሌሎችም አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ ተብሏል፡፡

የነገውን 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ የምታስተናግደው ጅማም እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗንም ተነግሮዋል፡፡

በ9ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የኦህዴድ ኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ እና የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ አደረጃጀት ሀላፊና የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በጅማ ከተማ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ጉባኤው ‘‘የላቀ ሃሳብ ለተሻለ ድል’’ በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።

በጉባኤው ላይ በድምጽ የሚሳተፉ 1ሺህ66፣ በታዛቢነት የሚሳተፉ 250 ሰዎች ጂማ ከተማ ተጠቃለው መግባታቸውንም አመላክተዋል።

በጉባኤው ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው በዚሁ ጉባዔም ያለፉት ሶስት ዓመታት የውስጠ ድርጅት አፈጻጸም ይገመገማል፤ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትም ቀርቦ ውውይት የሚካሄድበት መሆኑን አስረድተዋል።

በጉባኤው ቆይታ የድርጅቱን ስያሜ፣ አርማ እና መዝሙር ለመቀየር የሚያስችል ረቂቅ ቀርቦም ውይይት እንደሚካሄድበት ነው አቶ አዲሱ የተናገሩት።

በነገው ዕለት ከሰዓት በኋላም 6 ሺህ ታሳታፊዎች በላ የሚታደሙበት ድርጅታዊ ጉባዔ ለሦስት ቀናትም እንደሚቆይ ይጠበቃል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply