አመስጋኞቹ እስረኞች – (ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዛሬም ጉዳያችን በእስረኞች ስንክሳር ላይ ያተኩራል ። በአፋን ኦሮሞ “Abjuun bara beelaa bidden bidden jetti” እንደሚባለው  ነው። ሃሳቡን ወደ አማርኛ ስንመልሰው የረሃብ ዘመን ህልም ስለምግብ ብቻ ነው የሚል ዕሳቤ ይሰጠናል። እስርና እስረኛ የበዛበት ዘመን ወግም የእስርና የአሳር ከመሆን አያመልጥም ። ተንጦ ተንጦ “ፍቺ” ብስራት የሚሰማበት ጊዜም አለ። ይኸውም ወይ ዘግይቶ ወይ መጠኑ አንሶ ያለበለዚያም “ሁለት ሚዛን” ሆኖ ብስራቱን በሃዘኔታ  የተሸበበ ያደርገዋል ።

ባለፉት ሁለት ቀናት በዝዋይ እስር ቤት የሚገኙ የክፉው ቀን ወንድሞቼን ጠይቄ፣ የእስልምና ዕምነት ተከታዮቹን “ረመዳን ከሪም” ብዬ (አንዳንዶቹ ቤተሰብ ካዩ እስከ 17 ዓመት የቆዩ ናቸው) ወደቤት እየተመለስኩ ነው። እነዚያን በየራሳቸው መንገድ አገር፣ ወገን፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ እንዳሉ የወጣትነት እድሜያቸውን በአሳሩ ውስጥ እየፈጁ ያሉ የእናት ኢትዮጵያን ልጆች ወደሁዋላዬ ትቼ! እናም በጣም ከፍቶኛል።

የአሳሩ ባለዕዳዎቻችን አመስጋኞች ናቸው። ካፕቴን በሃይሉ ገብሬ ሲቃ እየተናነቀው ስለሱ የሚጨነቁትን ሁሉ አመስግንልኝ ሲል ሲታሠር  የ25 ዓመት ወጣት የነበረ አሁን የ40 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን እያሰብኩ…

ነጅብ ጠሃ ሐሰን በሐረር ወግ ምስጋናና ምርቃቱን  “ይፈቱ” ላሉ ሁሉ አድርስ ሲለኝ ከ11 ዓመት በፊት የ33 ዓመት ወጣት እንደነበር እያሰብኩ…

ዳውድ አባተማም የዛሬ 17 ዓመት የስንት ዓመት ቀንበጥ ነበር!

ፍቅረማርያም አስማማው አባሪዎቹ ዶ/ር ፍቅሬና አቶ አግባው ትናንት መፈታታቸውን ሳበስረው እሱ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ እያመሰገነ ነበር።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!

Share.

About Author

Leave A Reply