“አማራን ማን ያደራጀው?” (አሳዬ ደርቤ ለቃሊቲ ፕሬስ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ብዙዎች የአማራ ህዝብ እያንጸባረቀው ያለው የብሔርተኝነት ስሜት እያሳከካቸው ነው፡፡
እኒህ ሰዎች ሁሌም እንዲህ ናቸው፡፡ የአማራ ህዝብ የሚያደርገው ነገር ሁሉ እከክ ይሆንባቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ የሚያስፎክታቸው
የአማራው ህዝብ አስተሳሰቡም ሆነ ልቡ ረቂቅና ድብቅ ስለሆነ አይደለም፡፡ ይልቅስ ለህዝቡና ለአስተሳሰቡ ያላቸው ትርጓሜ
ጠማማ በመሆኑ ነው፡፡

ስለ አገር ሲያወራ ‹ትምክህተኛ›….ዝም ሲል ‹ኩራተኛ›… ተራብኩ ቢል ‹ሆዳም› የሚል ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡
ስለ አባቶቹ ቢያወራ ‹የድሮ ስርዓት ናፋቂ›… አሰራርንና መመሪያን ተከትሎ ቢሰራ ‹ቢሮክራት›… ለእነሱ የማይመጥን ነገር ከአፉ
ቢያወጣ ‹ተራች› ይሉታል፡፡ አለፍ ሲልም ተረቱን ‹ከአፋር በጀት› ጋር እኩል አድርገው በስጋት መልክ ያስቀምጡታል፡፡
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱን አላልቶ ወደ ማንነቱ በመመለስ ከተጋረጠበት አደጋ ራሱን ለማዳን ሲሯሯጥ…. መኖሩን የካዱት ሰዎች
‹ፋሽስት› አድርገውታል፡፡

ይህ ሁሉ እንግዲህ ያለ ወኪል ያስቀሩትን የአማራ ህዝብ ማንነት በማቀጨጭ የመጥፊያ ጊዜውን ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
‹‹ሆ›› ብሎ ከተነሳ እራሱን ማዳን ቀርቶ ሌላውንም መታደግ ስለሚችል ተኝቶ እንዲቀር ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ሰዎች
መረጋጋትና ሰላም የሚያጎናጽፋቸው ማንቀላፋቱ ብቻ ነው፡፡ መንፈራገጥና መንቀሳቀስ ሲጀምር ግን እንደ ሰሞኑን መፎከት
ይጀምራሉ፡፡
.
ሆኖም ግን እነሱ ያሻቸውን ያህል ቃልና ሴራ ቢጎነጉኑም …. ባሁኑ ሰዓት የአማራ ህዝብ ላይ የተፈጠረው የብሄርተኝነት ስሜት
ራሱን የማቆያ ብቸኛ መንገድ ነውና… ያለውን ማንነት ማስታወስ ብቻ ሳይሆን የሌለውን አደረጃጀትም መቀየስ ግድ ይላል፡፡
ምክንያቱም የአገር አንድነት ቀርቶ የጋብቻ ዘላቂነትም በአንድ አካል ፍላጎት ብቻ ሊቀጥል አይችልም፡፡ እንደምታውቁት እስካሁን
ድረስ አገራችንን እንዲትሰነብት ያደረጋት የመንግስት ድርጊት ሳይሆን የህዝቦቿ አርቆ አሳቢነት ነው፡፡ ከዚህ ህዝብ ደግሞ ትልቁን
ድርሻ የሚወስደው በዝምታ ውስጥ ሲጨፈጨፍ የኖረው የአማራ ህዝብ ነው፡፡
ለባለፉት ዓመታት ‹‹የወዝ-አደርነት›› ትርጓሜው አማራነት ሲሆን ሰምቶ እንዳልሰማ ባያልፍ፣ በሄደበት ሁሉ እንደመጨፍጨፉና
እንደመገፋቱ ትከሻውን ባያደነድን፣ በስሙ ሲነገድበትና ሲንቋሸሽበት ካስቀመጡበት የበታችነት አሮንቃ ውስጥ ራሱን አላምዶ
ባይኖር ኖሮ….. ገና ድሮ ወይ ይጠራ ወይ ይደፈርስ ነበር፡፡

እርግጥ በዚህ ስርዓት ጥቃት የተፈጸመበት አማራው ብቻ አለመሆኑ ይገባኛል፡፡ በስርዓቱ ጠባቂዎች ያልተገደለና ያልቆሰለ ብሔር
የለም፡፡ የአማራው ጥቃት ግን ከሌሎች ጥቃቶች ለየት የሚያደርገው በታጣቂዎች ብቻ ሳይሆን በሲቪሎችም ሲጨፈጨፍ የኖረ
መሆኑ ነው፡፡ (እስኪ መለስ ብላችሁ በየክልሉ በሚነሳ ግጭት በማይመለከተው ምክንያት የሞተውን የአማራ ህዝብ ደምሩት፡፡
ብሄርተኛ ቀርቶ ደመኛ ለመሆን አያስችልም?)

ደግሞ እኮ የሚገርመው አማራው ላይ የተሰራው ‹ሴራ› ወደ ሌላ ክልል ሄዶ ለመኖር እንዳይችል መደረጉ ብቻ አይደለም፡፡
ለዘመናት በራሱ ክልል ውስጥ በትዳርና በፍቅር ተጎዳኝቶ ሲያኖራቸው የነበሩ ህዝቦችም እንዲነጠሉትና እንዲጠሉት ለማድረግ ብዙ
መሰራቱ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ካለፈ ህዝብ መሸምቀቅ እንጂ መንቦርቀቅ እንዴት ይጠበቃል? እስከ መቼስ የራሱን
ማንነት ዘንግቶ ስለ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ አላስፈላጊነት እየደሰኮረ ሊኖር ይችላል? ለሌሎች ምቾት የሆነው አንቀጽ ለእሱ ብቻ ስጋት
ሆኖ የሚገኝበት’ስ ምን አይነት ምክንያት ይኖራል?

የዚህ ህዝብ ስቃይ እንደሁ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡ ከቀን ወደ ቀን በክልሉ ውስጥ ያለው አማራ በድህነት፣ ከክልሉ
ውጭ ያለው ደግሞ በጥይት እየተጨፈጨፈ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሚያየውን የስርዓት ለውጥ ማምጣት ቀርቶ እንደ ሌሎች
ብሄሮች የአመራር ለውጥ እውን ማድረግ አቅቶት በእነ በረከትና አዲሱ ለገሰ ዱልዱም መጋዝ እየተገዘገዘ ነው፡፡
ሁሉም እንደሚያዉቀው…. ትናንት በዚህ ህዝብ ላይ በስውር ሲካሄድ የነበረው ግድያና ማፈናቀል ዛሬ እንደ ተራ ጨረታ በግልጽ
ማስታወቂያ የሚፈጸም ሁኗል፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ወንድ የሆነ ሰው በወንድ ላይ የማይፈጽመው ዘግናኝ ድርጊት በአንድ ወንድማችን
ላይ ተፈጽሟ ፎቶውን ላለማየት እየታገልን ነው፡፡

ስለዚህም ተወደደም ተጠላም የአማራ ህዝብ… ልክ እንደ ሌላው ብሔር ሁሉ በአማራነቱ መደራጀትና ራሱን ከጥቃት መጠበቅ
ይኖርበታል፡፡
ይህ ደግሞ ‹‹መክትና አንክት›› በሚል ፖስት እውን የሚሆን ሳይሆን መሬት የነካ አደረጃጀት በመስራት የሚመጣ ነው፡፡ ችግሩ
ግን ከእኛ መሃከል መረጃ ማሰራጨቱን እንጂ ማደራጀቱን የሚደፍር አልተገኘም፡፡ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹የለም›› ያሉትን
አማራዊነት ‹‹አለ›› ብሎ በገሃድ የሚያደራጀውና የሚያስከብረው አልተገኘም፡፡ በአማራው ብሔርተኝነትም ዙሪያ
የሚያቀነቅኑትም የተነሱበት ላይ እየረገጡ እንጂ ለውጥ እያመጡ አይደለም፡፡ እኛም ብንሆን የተሰጠንን አጀንዳ ይዘን… ትናንት
ወዲያ ስለተገደለውና ስለተፈናቀለው፣ ትናንት ስለማስታወቂያው፣ ዛሬ ደግሞ ስለተሰለበው….ከማውራት በዘለለ የራሳችንን አጀንዳ
መፍጠር አልቻልንም፡፡ ይህ መንጋነታችንም የእለቱን ጥቃት ለማናፈስ እንጂ የትናንቱን እንዳናስታውስ በሽታ ሁኖብናል፡፡ ለምሳሌ
ያህል ‹‹ከቀበሌው ለቃችሁ ውጡ›› ያለው ሊቀ-መንበር ምን እርምጃ ተወሰደበት? ቢባል ከመሃከላችን መረጃ ያለው ይኖር
አይመስለኝም፡፡

እናም ካለው ሁኔታ ተነስቼ የግሌን ሃሳብ ስሰጥ….. ከዚህ በኋላ ፌስቡክ ላይ የሚካሄድ ጩኸት ለአማራ ህዝብ የሚተክርለት
ነገር የለም፡፡ ፌስቡክ ማገልገል ያለበትን ያህል አገልግሏል፡፡ (ማለትም ሶሻል ሚዲያ የሚጠቀመውን የአማራ ወጣት ወደ ማንነቱ
እንዲመለስ ማንቃት ያለበትን ያህል አንቅቷል፡፡) አሁን ላይ ግን ፌስቡክ ይሄን አበርክቶውን ጨርሷል፡፡ በአማራ ጥቃትና
ብሔርተኝነት ዙሪያ ነፍ ግጥም ቢጻፍ፣ ነፍ ትረካ ቢተረክ፣ ነፍ ፎቶ ቢለጠፍ ዳውን-ሎድ ስናደርገው ወደ ሞባይላችን እንጂ ወደ
ምድር ሊወርድ አይችልም፡፡

ስለዚህም ጥቃት በደረሰ ቁጥር…. እርስ በእራሳችን እየተበላላን ‹አማራ ተደራጅ› ብንለው ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ
ያጣው ‹ተደራጅ› የሚለው ሳይሆን የሚያደራጀው ነው፡፡ ‹‹ብአዴን ገደለህ›› የሚለው ሳይሆን መንገድ ቀይሶ ከብአዴን
የሚታደገው ነው፡፡ ይሄን የማድረግ ድፍረትና ጽናት ያለው ‹ሰው› ደግሞ ‹ኦንላይን› የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም
ስለአማራ ብሔርተኝነት የሚዘምረው አብዛኛው የሶሻል-ሚዲያ ተጠቃሚ በፌክ አካውንት የተደበቀና ማንነቱ የማይታወቅ ነው፡፡
ጊዜው የሚጠይቀው ደግሞ በፌክ አካውንት ተሸሽጎ ‹ወደ ማንነትህ ተመለስ› እያለ የሚደሰኩር የአማራ ወጣት ሳይሆን ማንነቱን
ይፋ አድርጎ ከህዝብ ፊት በድፍረት የሚቆም ነው፡፡ አይመስላችሁም?

Share.

About Author

Leave A Reply