አብን 3ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንዲሰረዝ ጠየቀ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን) በ1999 ዓ.ም የተካሄደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እንዲሰረዝ ጠይቋል።

ንቅናቄው ዛሬ በሰጠው መግለጫ በቆጠራው የተሳተፉ ባለሙያዎችና ባለስልጣናት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም አቋሙን አሳውቋል።

በቆጠራው ለተፈጠረው ስህተትም መንግስት ካሳ መክፈል እንዳለበት ነው አብን የጠየቀው።

በአዲስ አበባ እና አካባቢው ስለታማ ነገሮችን በመያዝ ከህግ አግባብ ውጭ እተንቀሳቀሱ እና ህዝብን እያሸበሩ ባሉ አካላት ላይ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ዝምታ ተገቢ አለመሆኑንም አብን በመግለጫው አስታውቋል።

የንቅናቄው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሹምዬ እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ አቶ ክርስቲያን ታደለ በሰጡት መግለጫ መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ የዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተጣሰ ለእንግልትና ለስደት እየተዳረጉ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች በፍትሃዊነት ያሳተፈ እና ተጠቃሚ ያደረገ ባለመሆኑ እንዲቀየር አብን ጥረት እንደሚያደረግም አስታውቀዋል።

ፍትህ እንዲሰፍን እና የዜጎችን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች መንግስት እልባት እንዲሰጣቸው አብን ጠይቋል፡፡

ንቅናቄው በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ሆን ተብሎ በተፈፀመው ጥፋት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፈል፤ ቆጠራውም እንዲሰረዝ እና ጥፋተኞች በህግ እንዲጠየቁ መንግስትን ጠይቋል፡፡

ላልተወሰነ ጊዜ በተራዘመው 4ኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ተዓማኒነት የተሞላባቸው አሰራሮች እንዲካሄዱ እና ከአሁን በፊት የተፈፀሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ ትግል እንደሚያደርግ ንቅናቄው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply