“አብዲ ኢሌ” መሸኘቱ መልካም ነው “ማን ይተካው?” የሚለው ግን ራስ ምታት ነው (መላኩ ብርሀኑ – ጋዜጠኛ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አቶ አብዲ ኢሌ (አብዲ መሃመድ ዑመር) እንደነፍሱ የሚወደውን ስልጣኑን አጥቷል። የጅግጅጋው አላሙዲ ዛሬ እዚያ አካባቢ የለም። በምትኩ መሃመድ አብዲ ተተክቷል። አብዲ የስልጣን ማምሻው ሲቃረብ ጋዜጠኞችን ሰብስቦ በክልሉ ለተፈጸሙ ጥፋቶች በሙሉ እሱና ባለስልጣናቱ እንዲሁም ፓርቲው ሶህዴፓ ሃላፊነት እንደሚወስዱ ይቅርታ ጠይቆ ነበር። ለዚህ የዳረገን ደህንነቱ ነው በማለት ሙሉ ጥፋቱን ጌታቸው ላይም ደፍድፏል። አብዲ ብቻውን የዚያ ክልል መንግስት ነበር። የተጻፈውን አስቀምጦ የራሱን ህግ ያወጣል፣ ህግ ይተረጉማል፣ህግ ያስፈጽማል። የዚያ ክልል ህግ አብዲ ብቻ ነው።

“አብዲ ለፍርድ ይቅረብ ፣ ለክልሉ ፌዴራል መንግስት ፕሬዚዳንት ይሹምለት፣ ወዘተ” የሚሉ አንዳንድ አስተያየቶችን በፌስ ቡክ ሳይ ግን ነገሩ እንደምናወራው ቀላል አለመሆኑ ይሰማኛል። አብዲ ለዓመታት ሶማሌ ላይ ከተከለው ሰፊ የጸጥታ ሃይል መዋቅር እና ካለው የአብላጫ ጎሳ ድጋፍ፣ በገንዘብም በሃይልም ከያዘው ተለዋዋጭ የክልሉ ባህሪ አንጻር ሲታይ የአብዲ መነሳት ብቻውን ለሶማሌ ክልል ሰላም ዋስትና ነው ብዬ አላምንም።
ስለሶማሌ ክልል የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ቅን ቢሆኑም የክልሉን ሁኔታ፣ የሶማሌን ህዝብ ባህሪና ባህል እንዲሁም የስልጣን ክፍፍሉን ዘዬ ካለማወቅ የሚመነጩ እንደሆኑ ይሰማኛል። የፌዴራል መንግስቱ እርምጃዎች መዘግየት በራሱ ብዙዎችን ቢያስቆጣም ለምን ዘገየ የሚለውን ማወቅ ግን አስፈላጊም ነው።

ሶማሌ ክልል በቀላሉ ዘው ተብሎ ጣልቃ የሚገባበት የፖለቲካ አውድ የለውም። ከገበየሁ አየለ “ጣምራ ጦር” የልጅነት ንባቤ በዘለለ ሶማሌ ክልልን ጠለቅ ብዬ ባላውቀውም ወደክልሉ ለዘገባ በሄድኩበት የጥቂት ሳምንታት ክራሞቴ ግን በቁንጽል ሁኔታውን ለማየት እድል ነበረኝ። በዚያ ቆይታዬ የተረዳሁት ነገር ቢኖር የሶማሌ ክልል ጉዳይ ቁጭ ብለን እንደምናስበው የፌዴራል መንግስቱ በቀላሉ ጣልቃ የሚገባበትና የፈለገውን አውርዶ የፈለገውን የሚሾምበት ቦታ አለመሆኑን ነው።

አብዲ እንደአጋር ፓርቲ መሪነቱ ለኢህአዴግ በጣም ታማኝ ሰው ነው። ኢህአዴግ አብዲ ኢሌ የሶማሌን ክልል እንደግል ቤቱ ነው ሲያስተዳድረው ዝም ያለው ከርሱ በፊት እጅግ አስቸጋሪ የነበረውን የጸጥታ ችግር በማርገብ ሰላሙን ወጥሮ ስለያዘለትና በተለይ ኦብነግን ለሁለት ለያይቶ ስለሰነጠቀለት ነው። ፕሬዚዳንት ከመሆኑ በፊት ለዓመታት ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ስለነበር የክልሉን እያንዳንዱን የጸጥታ ችግር አብጠርጥሮ ያውቀዋል። መጥፎው ነገር ግን አብዲ በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ መንታ ገጽ ያለው ሰው ነው። በዚህ ሶማሌ ክልልን እንዳያፈነግጥ ይዞ የቆየ ጠቃሚ ሰው ሲሆን በዚያ ደግሞ ማፈንገጥን የክፉ ቀን መጫወቻ ካርታ ለማድረግ ጊዜ የሚጠብቅ አደገኛም ሰው ነው። ክልሉን የግል ቤቱ አርጎ እንደልቡ ቀጥቅጦ ሲመራው ይህ ካርታ ጠቅሞታል።

ከአብዲ በኋላ ይህንን ክልል ለመምራት የተቀመጠው ሰው በመከራ የተሰባሰበውን የክልሉን አንድነት ጠብቆ የነበረውን ጸጥታ ማስቀጠል ፣ ህዝቡንም ወደሃርጌሳ ወይም ሞቃዲሾ ከማማተር መመለስ ይችላል ወይ የሚለውም ራሱን የቻለ አንድ ጥያቄ ነው። አብዲ ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች አሉት። የማይደግፉት ደግሞ እንዲፈሩት አስፈሪ የጸጥታ መዋቅር ዘርግቶ አርበድብዷቸዋል። ራሱም የፌዴራል መንግስቱ ኮሽ ባለበት ቁጥር የሚያስፈራራበት “መገንጠል” የምትል ቀይ ካርድ ኪሱ ይዞ ኖሯል።በስልጣን ዘመኑ ስሩን አርዝሞ ተክሏል። ሙሉ በሙሉ ሲነቀል አፈሩን ቦድሶ ጉድጓድ ለመፍጠር የሚያስችል አቅምም አለው። አ

ብዲ ብልጥ ነው። ራሱን ችግር ውስጥ የሚከትት ነገር ከመጣ ማርከሻ አዘጋጅቷል።አሁን ታስሯል ይባል እንጂ ሁኔታውን አናውቅም። ፌስቡክ ላይ ሆነን የውጊያ ካርታ ስናወጣለት የቆየነው መከላከያ አብዲን በቀላሉ መያዝና ማሰር አቅቶት አይምሰላችሁ የዘገየው። አብዲን በአንድ ጊዜ ከመስመር ማራቅ የሚያስነሳቸው ቀውሶች ታሳቢ ሆነዋል። ተጽዕኖው በጊዜ ሂደት መምከን አለበት። ከዚህ ውጪ ግብታዊ እርምጃ መውሰድ ጦስ አለው።

*****************
በ2004 ዓ.ም ክረምት አካባቢ በአብዲ ብልጠት እንደተሳካ የሚነገርለትን ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር በተገነጠለ በአንድ ጄኔራል የሚመራ ክንፍ የሰላም ስምምነት ፈርሞ ወደሃገሩ መግባቱን በማስመልከት የክልሉን ጸጥታ እና የልማት እንቅስቃሴ ለመጎብኘት ወደስፍራው ሁለት የጋዜጠኞች ቡድን ተላከ። አንዱን የመራሁት እኔ ነኝ። በዚያ ሳቢያ በሶማሌ ክልል ከፊቅ እስከሃርትሼክ እና አፋምቦ በደረሰ ስፋት አካባቢውን ለማየት ዕድሉ ነበረኝ።

ሙሉ በሙሉ ሰላም ሰፍኗል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር በማይቻልበት በዚያ ጊዜ ፣ ጋዜጠኛ ገብቶበት በማያውቅበት ስፍራ ፣ አደጋ ጣዮች በበዙበት ዘመን እስከአፍንጫው የታጠቀው ኦብነግ ቤዝ የነበሩትን ስፍራዎች በፊልም ቀርጾ ዘገባ ለመስራት መገኘት ራስን ለአደጋ የማጋለጥ ያህል በጣም ከባድ ነበር።

ድሬዳዋ ከአውሮፕላን ስንወርድ የተቀበሉን የክልሉ ጸጥታ ሃይሎች በመኪና ይዘውን የሄዱት ሃረርን አለፍ ብሎ ወደሚገኘው የምስራቅ እዝ መምሪያ ነው። መጀመሪያ ስለክልሉ ጸጥታ አጠቃላይ ኦሬንቴሽን መቀበል ነበረብን። ያነጋገሩን የምስራቅ እዝ አዛዠ ጄኔራል አብረሃ (ኳርተር) ናቸው። መቼም የእኚህ ጄኔራል ስም ሲጠራ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ምን እንደሚያንቀጠቅጣቸው አላውቅም። በጣም ይፈሯቸዋል። ጄኔራሉ በአጠቃላይ በሶማሌ ክልል ሰዎች ዘንድ ለምን እንደሚፈሩ አላውቅም። እኛም ተቀባዮቻችን እያስፈሩን ጄኔራሉን ቢሯቸው ገብተን እየተሳቀቅን አናገርናቸው። ፊታቸው ካለመፈታቱና ቢሮው አቅራቢያ ካሉት ሁለት አንበሶች ግሳት በቀር የመምሪያው ግቢ ብዙም የሚያስጨንቅ ድባብ አልነበረውም።

ጅግጅጋ ስንደርስ ሶህዴፓ ቢሮ ሄደን አቶ አብዲ መሃመድን አገኘነው። አቶ አብዲ በጊዜው የክልሉን ጸጥታ ምክትሉ ለነበረውና አሁን እንደተባረረ ለሰማሁት አብዱላሂ ኢትዮጵያ እያስመራ እሱ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ይዞ ነበር። ጥቂት አናግሮን ጉዳያችንን በወቅቱ ለዚሁ የጸጥታ ዘርፍ ም/ ሃላፊ አሳለፈው። ዝግጅት ተጀመረ።

(ይቀጥላል)

 

Share.

About Author

Leave A Reply