Thursday, January 17

አቶ በረከት ስምዖን – “በህዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ ገንብተናል” ሲሉ ሰማሁዎ! ድልድዩ ግን ምን በምን አስማት ወደ ባቢሎን ግንብነት ተቀየረ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ከአገናኝ ድልድይነት ወደከልካይ ግንብነት የተለወጠው….ይህም ዛሬ እንደሃገር ለገጠመን “የባቢሎን ቋንቋ ግንኙነት” ምክንያት የሆነው አቶ በረከት የኮሙኒኬሽን ልማት ዘርፉን ዲዛይን ሲያደርጉ በግልጽ የሚታይ ክፋት ወይም ጥፋት በመፈጸማቸው ነው። የማይግባባ ህዝብ ፈጥሮ እያናከሱ የመግዛት አንዱ ማስፈጸሚያ ስልትም ይኸው የተጣመመ የኮሙኒኬሽን ዲዛይን ነበር።

የዛሬ 8 ዓመት ግድም ኢህአዴግ “አዋቂ፣ አንባቢና አሰላሳይ አመራር ነው” ብሎ የሚኮራባቸው አቶ በረከት ስምዖን ለፓርቲያቸው እድሜ ርዝማኔ ሲሉ እንደኔ ያለ የአቦጊዳ ሽፍታ እንኳን የማይፈጽመውን አይነት ትልቅ ጥፋት ሰሩ። ደግነቱ ጥፋቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ በመሆኑ ይቅርታ አያሰጥም።

ምርጫ 97 ሊቃረብ ሰሞን አቶ በረከት እንዳዘጋጁት በምገምተው ‘የአብዮታዊ ዲሞክራሲያችን ጉዞና የህዝብ ግንኙነት ስራችን’ በሚል ርዕስ የተጻፈ አንድ ሰነድ ላይ ለሚዲያ ሃላፊዎችና ህዝብ ግንኙነት ሰራተኞች በሃገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ውስጥ ስልጠና ተሰጥቶ ነበር።

አሰልጣኙ አቶ ህላዊ ዮሴፍ ናቸው። (መቼም አቶ ህላዊን ከሰዓት በኋላ አለማየት ነው። ጸብ ጸብ ይላቸዋል።ስብሰባ እየመሩ በመቶ ዋት ፓውዛ አይናቸው ተሰብሳቢው ላይ ረጅም ያበራሉ። ጸሃይ ከረር ሲል የቀትሩ ጋኔን ይጣባቸዋል መሰል..ቂቂቂቂቂ)

እናም በዚህ ሰነድ ላይ ምን ሰፍሯል? ….

“ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና የፖሊሲና ስትራተጂዎቻችንን አፈጻጸም ለማፍጠን በህዝብ ግንኙነት ስራችን ላይ ከምንጊዜውም በላይ ማትኮር ይገባናል። የወደቀውን የህዝብ ግንኙነት ስራችንን ማጠናከር አለብን።

“በጊዜው ኢህአዴግ ስንትና ስንት ዓይነት ፖሊሲ፣ መመሪያ ወይም ስትራተጂ ሲያዘጋጅ የኮሙኒኬሽን ዘርፉን ግን ሙያዊ ቅርጽ በያዘ ሰነድ አላዋቀረውም። እናም እናጠናክረዋለን ያለውን የህዝብ ግንኙነት ስራ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፉን በሚያዘምን ዓይነት ሳይሆን ህዝቡን በሃሰት እየደለለ የስልጣን ዘመኑን በሚያራዝምበት መንገድ ብቻ መቀየድ ጀመረ። የህዝብ ግንኙነት ሙያ አንዱ መገለጫ የሆነውን ገመና ሸፋኝነት ብቻ ወስዶ “የጋራ መግባባት መፍጠር እና ለለውጥ ማነሳሳት” የሚሉትን ዋና ዋና ዓላማዎች አርቆ ቀበራቸው። ከዚያም ልማታዊ ኮሙኒኬሽን የሚባል የዲቨሎፕመንታል ስቴት (የሶሻሊዝም ዝርያ) አይዲዮሎጂ ቀለም ቀባው።

ከዚያም ተናገር ሲሉት “ሰማይ ሰማያዊ ነው፣ ወተት ነጭ ነው” የሚል እርባና ቢስ መረጃ አመንጪ ሆነ። ሲብስም በሬ መውለዱን ለማሳመን ሚዲያ ላይ ተጥዶ የሚውል የፕሮፓጋንዳ ማሽን ሆነ። አቶ በረከት በእጃቸው ጠፍጥፈው የሰሩት የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ይኸው ነው። አገራችንን ለማወቅ ብዙ ጊዜ ፈጀብን ።

ታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ ቻርለስ ጎይቴ Why governments lie “መንግስታት ለምን ይዋሻሉ” በሚለው መጽሃፉ “..በሚዋሽህ መንግሥት ስር ስትኖር ስለሕይወትህ ምንም ነገር በርግጠኝነት ማወቅ አትችልም። የምታውቀው ነገር ቢኖር ሲነገርህ የኖረውን ወሬ ብቻ ነው” እንዳለው እኛም የአቶ በረከት ማሽን ሲነግረን የኖረውን ብቻ ሰምተን ጉዳችንን ሳናውቅ ዘመን ባጅተናል።

ሙስናችን፣ የባለስልጣናቶቻችን ዝቅጠት፣ ከብሄር ብሄረሰብ መብት ጀርባ ያሉ ተንኮሎችን፣ ከፌዴራሊዝሙ ጉያ የተቀበሩ ቦምቦችን መልካምነታቸው ብቻ ሲነገረንና ስናምን ኖረናል። ዘቅጠን የተገኘነውም ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ያመረታቸውን ውሸቶች ስንሰማና ስለሃገራችን ያለን ዕውቀትም በዚያው ላይ ብቻ ተወስኖ በመኖራችን ነው። የተፈለገውም ይኸው ነው።

የሃገሪቱ የኮሙኒኬሽን መዋቅር መንግስት የሰራውን ብቻ ሳይሆን ያልሰራውንም አጋንኖ፣ ጨማምሮና ቀጣጥሎ የሚያወራ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ሆነ። በአይን የሚታየውን ችግር ‘ምንም ችግር የለም’ ብሎ የሚሸመጥጥ አይን አውጣ ዋሾ ሆነ። ኔትወርክ ይቆራረጣል ሰትለው “የከተማ ፎቆች ቁጥር መጨመር ያመጣው የልማታችን ውጤት ነው” የሚል አንድ አይና ዘርፍ ሆነ። ኢህአዴግ የማይሳሳት ብጹዕ ወቅዱስ ፓርቲ መሆኑን ለማሳመን የሚተጋ አቶስቷሽ መሳሪያ ሆነ። መንግስትን የተቸውን ሁሉ ‘በጸረ ሰላም ሃይል፣ ተላላኪ፣ አስፈጻሚ እና የዶላር እርጥባን ፈላጊነት’ የሚፈርጅ ተሳዳቢ አፍ ሆነ። መሬት ላይ የሌለ ርካሽ ገበያ፣ ማሳ ላይ የሌለ ሚሊዮን ኩንታል ምርት፣ ኢኮኖሚ ውስጥ የሌለ ፈጣን እድገት፣ ኪስ ውስጥ ያልገባ የኑሮ መሻሻል፣ መሶብ ውስጥ የማይታይ ዳቦ እየፈጠረ ኢትዮጵያን ባልሆነችበት የምኞት ገጽ ሲስላት ውሎ ያድር ጀመር። የመንግስት ሚዲያ ኮሙኒኬሽኑ ለሚያመርተው የውሸት ወሬ አፍ መጉመጥመጫ ተቋም እንዲሆን ተደርጎ ተበጀ። በአጠቃላይ አፍ እንጂ ጆሮ የሌለው ፣ የሚያወራ እንጂ የማይሰማ የኮሙኒኬሽን ስርዓት ከጫፍ ጫፍ ተዘረጋ።

ግዑዙ ስስዓት እንዲህ ከተዋቀረ በኋላ አንቀሳቃሹ የሰው ሃይል ተመለመለ።

እጅግ በጣም የሚያናድደኝና የሚያስቆጨኝ የሃገራዊ ውድቀት አንዱ መንስዔ ይኸው የኮሙኒኬሽን ዘርፉን እንዲመራ ታስቦ የተዋቀረው ‘ዜሮ ብቃት’ ያለው የሰው ሃይል አመላመል ሴራ ነው።

(መላኩ ብርሀኑ – ጋዜጠኛ)

Share.

About Author

Leave A Reply