“አንዳርጋቸው የሚያደርገውን በትክክል ያውቃል” አቶ ጽጌ ሃብተማርያም የአንዳርጋቸው አባት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግዮን፡- እንኳን ደስ አለዎት! ለዓመታት እስር ቤት እየተመላለሱ ልጅዎን አንዳርጋቸውን ይጠይቁ ነበርና ምን ተሰማዎት?

አቶ ፅጌ፡- እኔ ከልጅነቴ ጀምሬ ብዙ ነገር ስላየሁ የእሱ መታሰር ቢያሳዝነኝም ያን ያህል የሚያስጨንቀኝ ግን አልነበረም

ግዮን፡- እንዲያው ለመንደርደሪያ ያህል ትንሽ ስለራስዎ ቢነግሩኝ… አቶ ፅጌ፡- ደስ ይለኛል… የእናቴና የአባቴ ወገን ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ጃንሆይ ዘመናዊ የወታደር ሥርዓት እስከሚያመጡ ድረስ የአገራችንን ዳር ድንበር ሲጠብቁ ነበር፤ መጨረሻ ላይም ቢሆን በውጊያው ሰዓት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የያዘውን የጠላት ጣልያንን ጦር መቋቋም ቢያቅታቸውም ዝም ብለን ቁጭ ብለንማ አንበላም ብለው ትንንሽ ሕፃናት ልጆችን ይዘው ነው ጫካ የገቡት:: በጊዜው አባቴ ሞተ፣ አራት ታናናሽ ወንድሞቼ ታርደው ተገደሉ፤ በኋላ እኔም ከቀሩት ዘመዶቼ ተለየሁ፤ ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር ሆኜ በተለያዩ አገሮች እየተዋጋን ስንሄድ ቡታጅራ የሚባለው ቦታ ላይ ጠላት ተዘጋጅቶ ጠበቀን:: ራስ ደስታ፣ ደጃዝማች ገ/ማርያም፣ ፈታውራሪ ሽመልስና ሌሎችም የታወቁ መሪዎች በዚህ ውጊያ ላይ ነው የተሠውት:: ከእነርሱ ጋር የነበሩ ብዙ አርበኞችም በውጊያው ላይ ተሠውተዋል:: የእኔ ዘመዶችም በብዛት እዚህ ውጊያ ላይ ሞተዋል:: ጥቂት የተረፉ ሰዎች ወደ ኬንያ ለመሄድ ፈልገው ሰው ገንዘብ ሲረዳቸው ያኔ እኔ ልጅ ስለነበርኩና እድሜዬ ገና ሠባት በመሆኑ በአደራ ሰጥተውኝ ከሰዎች ጋር እዚያው አምስት ዓመት ተቀመጥኩ:: ጃንሆይ ሲመጡ ታሪኬን የሚያውቁ ሰዎች ለጃንሆይ ነግረዋቸው ስለነበር በዚያ መሰረት ጃንሆይ ቤተ መንግሥት ተቀምጬ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት እንድማር ቢፈቅዱልኝም ቤተ መንግሥት ቦታ ባለመኖሩ የአርበኞች ልጆች የሚማሩበት ት/ ቤት ደጃዝማች ገ/ማርያም ተጽፎልኝ ገባሁ:: በዚህ ት/ቤት ሁለት ዓመት እንደተማርኩ ወደተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተዛወርኩ፤ በመጨረሻም መምህራን ማሠልጠኛ ገብቼ ሁለት ዓመት ከተማርኩ በኋላ በአስተማሪነት ሠራሁ:: በፍጥነት ወደ ዳይሬክተርነት አድጌ በትምህርት አስተዳደር ዘርፍ ስሠራ ቆይቻለሁ:: እንዲህ እንዲህ እያለ ብዙ ቦታዎች የመሥራት እድሉ ገጥሞኛል:: ግዮን፡- መቼ ነበር ትዳር የመሠረቱት? አቶ ፅጌ፡- ወደ ትዳር ስገባ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበርኩ:: አጠቃላይ ዘጠኝ ልጆች ነው የወለድኩት በሕይወት የሌሉ አሉ::

ግዮን፡- አንዳርጋቸው ፅጌ በታሰረ ጊዜ እርስዎ ተይዘው ታስረው ነበር፤ ለምን ለነበር የታያዙት?

አቶ ፅጌ፡- ግብረ አበር ነህ በሚል ነው፤ እኔ ደግሞ አባቱ እንጂ ግብረ አበሩ አይደለሁም አልኩኝ፤ ሰሚ ባይኖርም::

ግዮን፡- ምን ያህል ጊዜ ነው የታሰሩት?

አቶ ፅጌ፡- ሁለት ዓመት ተኩል ታስሬ ነው የተፈታሁት::

ግዮን፡- በሽምግልና እድሜዎ ከሁለት ዓመት በላይ ያስለፉት የእስር ሕይወት ምን ይመስላል? አቶ ፅጌ፡- እስር ቤት እስር ቤት ነው፤ ብዙ ነፃነት ባይኖረውም የሚበላ፣ የሚጠጣ እንዲሁም መኝታ አለው፤ ያው ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት በጊዜው ይቀርብልን ነበር::

ግዮን፡- መጨረሻ ላይ ምን ብለው ፈቱዎት? አቶ ፅጌ፡- በጊዜው የእስረኞችን ሁኔታ የሚከታተል፣ የታሰሩ እስረኞችን በተለያዩ መንገዶች ይቅርታ የሚያስደርግና የሚያስፈታ አንድ ኮሚቴ ነበር:: በእነርሱ በኩል የእኔ ጉዳይ ታይቶ ምንም ጥፋት አልተገኘበትም፣ ወንጀለኛ አይደለም በሚል እድሜዬም ከግምት ውስጥ ገብቶ ጠይቀውልኝ ነው የተፈታሁት::

ግዮን፡- ያኔ ሲታሰሩ እድሜዎ ምን ያህል ነበር?

አቶ ፅጌ፡- እነሱ ሲያስሩኝ 78 ዓመቴ ነበር፤ አሁን 87 ዓመት ሞልቶኛል:: በእርጅና እድሜዬ አስገብተው ሰማኒያኛ እድሜዬን ከደፈንኩ በኋላ ነው ያስወጡኝ::

ግዮን፡- አንዳርጋቸው ተይዞ ወደ አገር ቤት ገብቷል የሚለውን ዜና መጀመሪያ ሲሰሙና በኋላም እስር ላይ ሲጠይቁትስ ምን ተሰማዎ?

አቶ ፅጌ፡- አንዳርጋቸው በሚያደርገው ነገር ሁሉ ምክንያታዊ መንገዱ የማይዋጥላቸው ሰዎች ሲይዙት ቢያስገርመኝም የተያዘው ባመነበትና በሚሠራው ሥራ በመሆኑ በፍርድ የሚሰጠውን ውሳኔ ከመጠበቅ ውጪ ከፍተኛ ድንጋጤ አልተሰማኝም:: አንዳርጋቸው ልዩ የሆነ ሰው ነው፤ እንዲህ አድርግ አታድርግ ብዬ የምመክረው አይደለም፤ በጣም ጠንካራና በእኔ ቤተሰቦች ላይ የደረሰውንም መከራ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የሚጠበቅበትን መሥዋእትነት ከፍሎ ፍትሕን እንደሚያገኝ የታገለለትንም ሕዝብ እንደሚያከብር እርግጠኛ ነበርኩ:: እሱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ልጆቼ የቀደመ ታሪካቸውን የሚያውቁ ቤተሰቡ ያሳለፈውን እንግልት የሚረዱ ስለሆነ ከእኔ ብዙም ምክር የሚያስፈልጋቸው አይደሉም::

ግዮን፡- አንዳርጋቸው ከሌሎች ልጆችዎ ለእርስዎ በምን መልኩ ይለያል?

አቶ ፅጌ፡- እርሱ ያለው አዕምሮ ትልቅ ነው፤ በጣም አስተዋይ ሰው ነው:: ልጅም ሆኖ ይህ እውቀትና ንቁነቱ አብሮት ነበር:: ገና በለጋ እድሜው በደርግ ሥርዓት ብዙ መከራ አይቷል፤ ያኔ አለመሞቱ በራሱ ይገርመኛል:: አንድ ወንድሙ በጊዜው ተገድሏል:: አንዳርጋቸው የሚታገለው ለሕዝቡ ነው:: ባወቀውና በተረዳው መጠን አገሩ ሰላምና ሕዝቦች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባት እንድትሆን ይፈልጋል:: ጥቃትን፣ በደልን አይወድም:: ሁሌም የሚታገለው ለሀገሩና ለወገኑ መብት ነው እንጂ ሥልጣን ወይም ሌላ ነገር አጓጉቶት አይደለም::

ግዮን፡- እስር ቤት በነበረ ጊዜ ልጄን አንድ ነገር ያደርጉብኛል ብለው ሠግተው ነበር?

አቶ ፅጌ፡- የሚደረገውን ነገር ሁሉ ስለማውቀው ያን ያህል አልጨነቅም ነበር፤ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ የታሰረው በወገንና በአገር ጉዳይ ስለሆነ ምንም ነገር ቢገጥመው ለአገሩ የከፈለው መሥዋእትነት ነው ብዬ ነው የወሰንኩት:: እግዚአብሔር ራሱ ጊዜውን ጠብቆ ፍርድ ይሰጣልና::

ግዮን፡- ሌላ ጊዜ አንዳርጋቸውን ሊጠይቁ ሲሄዱ ቁጭ ብለው ነበር የሚጠብቁት፤ ቅዳሜ ዕለት ሊጠይቁት በሄዱ ሰዓት ግን እሱን እንዳዩ ነው ብድግ ያሉት፤ የመፈታቱ ዜና የፈጠረብዎት ስሜት ይሆን?

አቶ ፅጌ፡- ይህችን ደግሞ ከየት አገኘሃት:: ያው የፈነጠቀው ፀሃይ ነው እንደዚያ ያደረገኝ:: መፈታቱን መስማቴ በውስጤ የሚያሳድረው ነገር እንዳለ መዘንጋት የለብህም:: እንደዚያ በፍጥነት ያስነሣኝ በቀጣይ የሚኖረው ተስፋ ነው:: ያ ለእሱ ልዩ የሆነ ነገር ስለነበር በጊዜው አንዳርጋቸው በጣም ተገርሟል:: ደስታው ውስጤ ስለገባና እሱን ተፈትቶ ማየት እመኝ ስለነበር ነው ብድግ ያልሁትና እርጅናዬን የረሣሁት::

ግዮን፡- በመኖሪያ ቤትዎና በአካባቢው ሕዝቡ ያደረገውን አቀባበል እንዴት አዩት?

አቶ ፅጌ፡- አንድ ሰው ብቻውን አይደለም የሚኖረው፤ ሕይወቱ ከአገሩና ከሕዝቡ ጋር ነው:: አንዳርጋቸውም የታገለው ለዚህ ሕዝብ ነው፤ እድሜውን በሙሉ የደከመላት ለአገሩ ነው:: እንስሳትም በጋራ ይሄዳሉ፣ በጋራ ይፋለማሉ፤ ሰው ከእንስሳ በላይ ስለሆነ የጋራ ሕብረትና ስሜት ያስፈልገዋል:: አንዳርጋቸው በዚህ መንገድ የትግል ዘመኑን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጓል:: ራሱን ለመሥዋእትነት ያቀረበለት ይህ ሕዝብ በይፋ እንዳያችሁት ውለታውን በይፋ ከፍሎታል:: በጣም ደስ በሚልና እንኳንም ታገልኩ በሚያስብል ሁኔታ ነው ህዝቡ የተቀበለው:: አንዳርጋቸው የሚያደርገውን በትክክል ያውቅ ስለነበር የታገለለት ሕዝብ በክብር ተቀብሎታል::

ግዮን፡- በመጨረሻ በዚህ አጋጣሚ የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድነው?

አቶ ፅጌ፡- ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ነው:: ልዩነታችንን በሰላማዊ መንገድ ፈትተን ሕዝቡ በምግብ፣ በጤና፣ በኢኮኖሚና በነፃነት ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት:: ይህ ነገር ለኢትዮጵያችን ያስፈልጋል::

ግዮን፡- አመሰግናለሁ::

Share.

About Author

Leave A Reply