አንዳንዶች ባይደመሩስ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መንግስታዊ አርቲስቶች (ልማታዊ አርቲስቶች) ዛሬ ራሳችሁን ቻሉ! የሰው ጥላ ስር እየተንሿከካችሁ መኖር ይብቃችሁ ተብለዋል! ሰምተዋል፣ ሰምተናል!

እንግዲህ ምንም ሰበብ የለም! ወደ ስራ!!

የተሸፋፈነውን ግለጡ!

ያልተነገሩ ታሪኮቻችንን እንግዲህ የዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ በተስፋ ተሞልታለች። ከውስጥም ከውጭም አንድ ዓይነት ስሜት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ይፍለቀለቃል። የሚታየው የለውጥ ጅምር እውነተኛና ዘላቂ ወደሆነ ለውጥ ያመራል የሚለው ተስፋም እንደብረት ጠንክሯል። በዋሽንግተን ዲሲ ትላንት ያየነው የኢትዮጵያውያን ትዕይንት እንደከዚህ ቀደሙ ‘ሰልፍ’ ተብሎ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሳይሆን በድጋፍ፡ በተበላሸ እንቁላል ቀርቶ በዘንባባ ዝንጣፊ፡ በእርግማን ምትክ በምርቃትና ምስጋና የሚቀበሉት መሪ(ዶ/ር አብይ) እንደሚሆን ቃል የገቡትበት ሰልፍ ነው። ታዲያ በደረቁ አመስግነው ብቻ አልተዉም። ”የተጀመረው ለውጥ ወደ ሽግግር ስርዓት እንዲያመራ በእርሶ ላይ ተስፋ ጥለናል።” የምትል በአደራ የተቋጠረች የቤት ስራም ለዶ/ር አብይ ሰደዋል።

በየዕለቱ የሚሰሙ አስገራሚ ነገሮች ቀጥለዋል። ባድመን መልቀቅ እንደቅድመ ሁኔታ ሳያሰቀምጡ፡ ሶስተኛ ወገን ይዳኘን የሚል አቋም ሳይዙ የልዑካን ቡድናቸውን ወደ አዲሰበባ እንደሚልኩ የገለጹት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትላንት ቱባ ባለስልጣናቶቻቸውን ሰደው ተአምር ሲያስብሉኝ ነው የዋሉት። በጉዳዩ ላይ የምርና ቁርጠኛ ውሳኔ ለመድረሳቸው የላኳቸው ባለስልጣናት ስብስብ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ዶ/ር አብይም ለእኚህ ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት ያደረጉት አቀባበልና በቤተመንግስት ያዘጋጁት ስነስርዓት አፍን በአግራሞት የሚያሲይዝ ነው። እንደዛ የጠበቀ ካለ አላውቅም። ታምራት ገለታ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቆላው ተሰምቶ ከሆነ እኛ ዘንድ አልደረሰም። ያልተጠበቀ፡ በቅርብ ዘመን ይሆናል ተብሎ ያልታሰበ ነው የሆነው።

ለእኔ በመሀሙድ አህመድ ”ሰላም” ዜማ እጅ ለእጅ የተያያዙት የአንድ አፈር ልጆች ሁኔታ የደስታ እምባ ወደውስጥ እንድለቀው አድርጎኛል። መጪው ቅዱስ ዮሀንስ አስመራና አዲስ አበባ እንደሚከበር ዶ/ር አብይ ሲናገሩ ደግሞ ጆሮዬን ተጠራጠርኩ። ፈጣሪ ሊታረቀን ይሆን? አስመራ በአበባይሆሽ ዘፈን ስትቀልጥ ታየኝ። የካዛንቺስ መሽታ ቤቶች በሄለን መለስ ‘ፍርፍር’ ዘፈን ሊደምቁ ነው ማለት ነው? በእርግጥ አስመራ ለኢትዮጵያ ሙዚቃዎች እንግዳ እንዳልሆነች አውቃለሁ። በኢትዮጵያ ጭፈራ ቤቶች የኤርትራ ዜማዎችን ማድመጥ አዲስ ነገር አይደለም። አሁን የሚለየው ሰላም፡ ፍቅርና አንድነት በሁለቱ ሀገራት መሀል መደመራቸው ነው። አሁን ሙዚቃዎቹ ትርጉም አላቸው። የጥላቻው ግድግዳ ተደርምሶ የሚደመጡ መሆናቸው ጣዕማቸው የሙዚቃ ብቻ ሆኖ ከጆሮ አይገቡም። ከልብ ዘልቀው ስለሁለቱ ሀገራት የአንድነት ማህተም ያኖራሉ። የ2011 አዲስ አመት ዋዜማውን ከአስመራ ኩምቢሽታቶ፡ ሰምበል ማይተመናይ፡ ገጀረት አሳልፎ በማግስቱ የእንቁጣጣሽ ዕለት ወደ ሸገር ብርርር….

በእርግጥ የዶ/ር አብይ የይቅርታና መደመር አዲስ መንፈስ አወንታዊ ለውጦችን በያቅጣጫው እያስመዘገበ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። ”መደመር” የሚለው አሮጌ ቃል፡ አዲስ የመንፈስ ስጋ ለብሶ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ደምቆ ይሰማ ከጀመረ ሳምንታት ተቆጠረዋል። ግን ‘መደመር’ ምንድን ነው? በዚህን ወቅት በኢትዮጵያውያን ዘንድ አብዝቶ ከአፍ የማይጠፋ ሆኗል። ሀሳቡም በተስፋ ተለብጦ በኢትዮጵያ ምድር ከጫፍ እስከጫፍ ጎሎቶ የሚሰማ የጊዜው ‘ንጉስ’ ቃል ለመሆን በቅቷል። ”ተደመረ” ማለት በዶ/ር አብይ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ተማርኮ፡ እጅ ሰጥቶ፡ ለለውጥ ተነሳ ማለት ነው የሚል ትርጉም ይዞ እዚህም እዚያም፡ የጨዋታ ማጣፈጫ በመሆን እያገለገለ ነው። ይህ ጥሩ ነገር ነው። የሚሊዮኖችን ቀልብ የሳበ፡ ተስፋንም የሰነቀ ነውና። ግን ደግሞ ወረት ሆኖ እንዳይቀር ስጋት አለ። ከዚያም ባለፈ ‘መደመር’ የሚለው ቃል ከሚገባው በላይ ተለጥጦ የተዛባና ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ውጤት እንዳያመጣም የታሰበበት አይመስለኝም።

አዎን! መደመር ሲባል ድንበር የለውም? ስነስርዓት የለውም? ህግና ደንብ ሳይኖረው: መልክና ቅርፅ ስይበጅለት: ዝም ብሎ መደመር ነውን? ስንዴ ከእንክርዳዱ: ፍሬ ከገለባው: ጥሩውና መጥፎው: ፉንጋውና ሰልካካው: አደርባዩና ሃቀኛው ሳይለዩ: ወሰን ሳያበጁ መደባለቅም ማለት ነው? እንዴት ነገሩ? በመደመር ሂሳብ ንጹህ ከቆሻሻው የማይለይበት፡ ጻድቃን ከሃጥአን የተዋሃዱበት፡ ገራፊውና ተገራፊው የተቃየጡበት፡ ሰነፍና ጎበዝ አንድ የሆኑበት፡ ዘራፊው ደረቱን ገልብጦ የሚፈነጭበት፡ ሞራል አልባው አይኑን በጨው አጥቦ የሚፎልልበት፡ የህሊና ደሀው ፊት መስመር ተሰልፎ የሚፎክርበት …..ከሆነ ምኑ ነው ለውጡ? ቁልቁል መደመር፡ በዜሮ መባዛት፡ ለምን ተፈለገ?

የዶ/ር አብይና የኤርትራ ባልስጣናት የቤተመንግስት ትዕይንትን ከተመለከትኩ በኋላ ይህን ጽሁፍ እንዳዘጋጅ ውስጤን ገፋፋው። እውነት ለመናገር የዶ/ር አብይ የ’መደመር’ አብዮት ፈሩን እየሳተ፡ በሆይ ሆይታና ግርግር የታጀበ፡ በማይደመሩ ሰዎች በዜሮ እየተባዛ፡ በሂደትም ትርፉ ሀገራዊ ወደ ሆነ ኪሳራ እንዳያመራ በጽኑ እሰጋለሁ። ሟርተኛም ካሰኘኝ..ግድየለም ልሁን። ፖለቲካ ብዙ ቅንነት፡ ትንሽ ተጠራጣሪነት ያስፈልገዋል። ፖለቲካ የፍቅር ቲያትር አይደለም። በይቅርታ ጀምሮ በይቅርታ የሚጠናቀቅ፡ ፍቅር ብቻ የሞላበት፡ የዋህነት፡ ደግነት፡ መልካምነት እንጂ ሌላ ነገር የማይነካካው አይደለም። ቅዱስ መጽሀፉም እንደእርግብ የዋህ፡ እንደእባብ ልባም ሁን ይላል። እሾህ በሞላባት፡ አሜኬላው በየሜትሩ በወደቀባት፡ የሞራል ኮምፓሷ በጠፋባት በዚህች ዓለም፡ አልፋና ኦሜጋው ፍቅር ብቻ የሆነበት የፖለቲካ ስትራቴጂ የጠዋት ጤዛ ነው። እድሜ አይኖረውም። ትንሽ ቆፍጠን ማለት ያስፈልጋል። ኮስተር።

ስንቱን የኪነጥበብ ሰው ያፈራች፡ አንጋፋና ስብዕናቸው የገዘፉ፡ በአርያነታቸው ከፍ ብለው የሚነሱ፡ ስማቸውን ጠርተን የማንጠግባቸው ስንት ዕንቁ የጥበብ ሰዎች እያሉ ሰራዊት ፍቅሬ የተባለ፡ ሞራል የደረቀበት፡ ነውር የማይፈራ፡ ሰውነቱን አራግፎ የጨረሰ፡ የመጥፎ ስብዕና መገለጫ የሆነ ግለሰብ በመደመር ሂሳብ ዘንድሮም ከፊት ተሰልፎ ስመለከተው እውነት ለመናገር አቃረኝ። ከመንደር አስተሳሰብ ያልወጣን፡ ኢትዮጵያውያንን በዘርና በጎሳ ሸንሽኖ ሲያባላ ኖሮ ኢትዮጵያዊ መሆን አቅቶት፡ ቁልል መከራ አሸክሞን፡ በጭካኔ በትር ሲቀጠቅጠን ኖሮ ዘላለማዊ ሞቱን የጨለጠውን መለስ ዜናዊን ”የሙሴ በትር” እያለ ያዜመን ነዋይ ደበበ የተባለን ዘፋኝ የአዲሲቷን፡ የተደመረች ኢትዮጵያን ወክሎ መድረክ ላይ ሲንጎማለል እንደማየት ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን ነገር አለ?

እንደሰማነው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ የተባለ በቀደመው የህወሀት አገዛዝ መሬት የጠበበው ሰው ከዶ/ር አብይ ጋር አፈር ፈጭቶ ያደገ ወዳጅ ነው። በአብሮ አደግነት ስሌት በዶ/ር አብይ ተመርጦ ወደፊት እንዲመጣና የአርቲስቶችን ጉዳይ እንዲመራው የተመረጠ እንደሆነም ይነገራል። ዶ/ር አብይ በዚህ አንጻር ትልቅ ፋውል ሰርተዋል። የህዝብ አመኔታን ያጡ፡ ባትሪያቸውን የጨረሱ፡ ህሊና የሚባል ትንሹ እግዚያብሄር ያልፈጠረባቸው፡ አክሮባት መስራት፡ መገለባበጥን የህይወታቸው መርህ ያደረጉ፡ በአጭሩ ህዝብ የሚጠየፋቸውን ሰዎች ከአጠገቡ መሰብሰብ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። አርቲስት ቴዎድሮስ በሰፈር ልጅነት ያገኘውን መድረክ ብጤዎቹን መሰብሰቢያ አድርጎት አርፏል። የኢትዮጵያ ህዝብ በጸሎቱ ፈጣሪ እስከወዲያኛው ያለያየውን መለስ ዜናዊን ጥቁር አዘቅዝቀው፡ ማቅ ለብሰው ”ምነው ተለየሀን፡ መስከረም ሳይጠባ” የተሰኘውን ታላቅ ዜማ አርክሰው በህብረት እያዜሙ፡ እንባ እየተራጩ የሸኙ አርቲስቶችን ለዶ/ር አብይ ተስፋ ሰጪ የመደመር አብዮት አድማቂ አድርጎ ከፊት ሲያመጣቸው ውስጤ በቁጭትና ንዴት በግኗል። ከዚህ ዓይነቱስ መደመር አንደኛውን ተቀንሶ የዳር ተመልካች መሆኑ ሳይሻል አይቀርም።

ገና በጠዋቱ፡ በመለስ ጉትጎታ ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ ከመለየቷ በፊት አስመራ ድረስ ሄደው በአማራው ህዝብ ስም ”በድለናችኋል፡ ይቅር በሉን” የሚል የውርደት ታሪክ ፈጽመው በዚህ አሳፋሪ ተግባራቸው ማፈርና መደበቅ ሲገባቸው እንደጀግና እየተንጎራደዱ የሚፎልሉ፡ ሰው ዘንድሮም የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ዋና ተንታኝ ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት ሳያቸው አሁንስ ይሄ ‘መደመር’ ሃዲዱን ስቶ ከገደል እንዳይወስደን አስባለኝ። አቶ ታደለ ይመር በአደርባይ ባህሪያቸው የሚስተካከላቸው የለም። አስመራ ድረስ ሄደው በአንድ ህዝብ ስም ይቅርታ የጠየቁበት አስቀያሚ መልካቸውን ሳይቀይሩት፡ በሁለቱ ቀደምት ምርጫዎች የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ማህበር ወንበር ላይ ፊጢጥ ብለው ተቀምጠው የአደርባይነት ታሪካቸውን ደገሙት። ህወሀት በዓለም ዓቀፍ መድረክ ጨፍጫፊነቱ የተጋለጠበትን የ1997 ምርጫ ”ሰላማዊ” ሲሉ በታዛቢዎች ስም መግለጫ ሲሰጡ ሳይ አንድ ሰው በአደርባይነት እስከየት ጥግ ሊሄድ ይችላል ስል ራሴን ጠየኩ።አሁንም ህወሀት በተዋረደበት የ2002ቱ ምርጫ 100 ፐርሰንት አሸነፍኩ ብሎ ፓርላማውን ሲቆጣጠር እኚሁ ሰዉ ዳግም ብቅ ብለው ተመሳሳይ ቆብ አጥልቀው ምርጫው ”ፍጹም ዲሞክራሲያዊ ነው” ሲሉ ተናገሩ። ሰውዬው ሀፍረት አልፈጠረባቸውም። ለልጆቻቸው አዘንኩ። ምን ዓይነት አባት አለን ብለው እንደሚናገሩ አላውቅም። እኚሁ የአደርባይነት ተምሳሌት የሆኑ ግለሰብ ዘንድሮም በመደመር ሂሳብ ከፊት መጥተው እየደሰኮሩ ነው።

በመደመር አብዮት ተንገዋለው ወደ ኋላ ይቀራሉ ያልናቸው ግለሰቦች በተቃራኒው ከፊት ተሰልፈው ስናያቸው የዶ/ር አብይ ተስፋ ሰጪ አካሄድ ላይ መጥፎ አሻራ እንዳያኖሩ ስጋት ገብቶኛል። ዶ/ር አብይ ስራ ስለሚበዛባቸው ይሄን ሁሉ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ውሳኔ እንዲሰጡ አይጠበቅም። ግን ደግሞ በመደመር ሂሳብ አጨብርባሪዎች መድረኩን ሲቆጣጠሩት ማየት የሚታገሱት ነገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ክብር የሌላቸው ናቸው። ለዚህ ዓይነቱ ሀገራዊ አብዮት የሚመጥን ስብዕና የላቸውም። ህዝብ ላይ ላደረሱት የሞራል ኪሳራ ይቅርታ ሳይጠይቁ ከመንጋው ጋር ተቅላቅለው፡ ብሎም ፊት መሪ ሆነው ሲመጡ ማየት በእጅጉን ያሳፍራል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ባይደመሩስ?

ልቤ በተስፋ በርቶ እነዚህን ሰዎች ስመለከት ቅጭም ይልብኛል። ደስታዬ እንደጉም በኖ ይለየኛል። የዶ/ር አብይ ራዕይ በእነዚህ የሰውነት ባህሪያቸውን ባጡ ሰዎች የተነሳ ይጨናገፋል የሚል እምነት የለኝም። ግን ከመድረኩ ዞር እንዲሉ እፈልጋለሁ። በጽኑ እሻለሁ። ልጆቻችን ከዚህ ምን እየተማሩ ያድጋሉ? ለነገው ትውልድ የምናስብ ከሆነ የሞራል ክስረት የገጠማቸውን ሰዎች እያመጡ መሸልምና ማወደስ ትልቅ ስህተት ነው። ልጆቻችን በሀቀኝነት ሀገራቸውን ከሚያገለግሉ እንጂ ‘በእንብላውና’ እንጋጠው ማህበር ከተሰበሰቡ የቀን ጅቦች የሚቀስሙት አንዳችም መልካም ነገር የለም። መገለባበጥን እንጂ እውነትን አይማሩም፣፡ አደርባይነት እንጂ ለመርህ መቆምን አይመርጡም። በመጥፎ አርዓያነት ልጆቻችንን የሚያበላሹ የትውልድ ጸር መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።

ዶ/ር አብይ የመደመር አብዮትዎን በሚገባ ይፈትሹ። እነዚህን ሰዎች ከፊት እያሰለፉ መደመር አይኖርም። መቀነስ እንጂ። የእርስዎ ቅጥር በእነዚህ ሞራል አልባ ሰዎች አይወረር። እውነት ለመናገር እንዲህ ዓይነት መደመር የትም አያደርስም። በየቤቱ አንገቱን የደፋ ስንት ድንቅ የጥበብ ባለሙያ አለና እነሱን ይፈልጉ። አዲስ ፊት ለአዲስ ራዕይ።

(መሳይ መኮንን – ጋዜጠኛ)

 

Share.

About Author

Leave A Reply