“አንድም ሰዉ አልተፈናቀለም፤ የሚያፈናቅልም አይኖርም፡፡” – የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሺን

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ሌሎችን የማቀፍ እንጂ የማፈናቀል ባህል የላቸዉም
/ ነገሪ ሌንጮ፤ የኦሮምያ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን / ቤት ሀላፊ
( ሙሉ መግለጫቸው እነሆ)

ሰሞኑን አንዳንድ ሚዲያዎችና የዉጭ ተቋማት ከኦሮሚያ ክልል፣ ከቄለም ወለጋ ዞን፣ ከሰዲ ጨንቃ እና ሰዮ ወረዳዎች፡ ሰዎች እንደተፈናቀሉ አድርገው እያስወሩ ናቸው። እዉነታዉ ግን፣ በ1977 በአገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መጥተው በቄለም ወለጋ ዞን በስድስት ወረዳዎች ማለትም፦ ዳሌ ሰዲ፡ ሃዋ ገላን፡ ሰዮ፡ ላሎ ቅሌ፡ ጅማ ሆሮ እና ሰዲ ጨንቃ ወረዳዎች እንዲሰፍሩ የተደረጉት ወገኖቻችን ላለፉት 33 ዓመታት ቤተሰብና ንብረት አፍርተዉ አስከሁን ድረስ በሰላም እየኖሩ መሆናቸው ነው።

በሰዲ ጨንቃ ወረዳ አምስት ቀበሌዎች ዉስጥ ቄጦ በመባል በሚጠራው አካባቢ የሰፈሩ ወገኖቻችን ሰሞኑን አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት ሳይሆን እንደሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች ሁሉ ከአካባቢዉ ህዝብ ጋር በሰላም መኖራቸውን የቀጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በእነዚህም ቀበሌዎች 1ኛ. በቄጦ 1 ቀበሌ 850 አባወራዎች (4935 ቤተሰብ)፤ 2ኛ. በቄጦ 5 ቀበሌ 810 አባወራዎች ( 5708 ቤተሰብ)፤ 3ኛ. በቄጦ 6 ቀበሌ 456 አባወራዎች (2302 ቤተሰብ)፤ 4ኛ. በቄጦ 7 ቀበሌ 623 አባወራዎች (3329 ቤተሰብ)፤ 5ኛ. በቄጦ 11 ቀበሌ 655 አባወራዎች (3072 በተሰብ) በድምሩ 3 ሺህ 394 አባወራዎች ወይም 19 ሺህ 346 ቤተሰቦች እየኖሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥም ሆነ ሰዮ ወረዳና ሌሎች ወረዳዎች ዉስጥ ከሚኖሩት አንድም ሰዉ አልተፈናቀለም፤ የሚያፈናቅላቸዉም አይኖርም፡፡

በዚሁ በሰዲ ጨንቃ ወረዳ ከላይ ከተጠቀሱት ቀበሌዎች ዉጭ ባለው እጉ ኮፈሌ በተባለው ቀበሌ ውስጥ ከአካባቢዉ ህዝብ ጋር በሰላም ሲኖሩ ከነበሩ መካከል 42 አባወራዎች ቀደም ሲል በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች ተከስቶ የነበረዉን የፀጥታ ችግር በዜና በሰሙበት ወቅት ስጋት ዉስጥ እንደገቡ በመግለፅ ለመሄድ ባሰቡበት ወቅት፣ የአካባቢዉ ህዝብና የወረዳዉ አመራር እንዳይሄዱ ሲለምናቸው የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም እንደሄዱ፣ ይህም ሆኖ ከነሱ መካከል 15 አባወራዎች ተመልሰዉ 10 አባወራዎች ንብረታቸዉን ሽጠዉ ሲመለሱ አምስት አባወራዎች ደግሞ ዉክልና ሰጥተዉ መሄዳቸዉ ታዉቋል፡፡

የአከባቢዉን ህዝብም ሆነ አመራሩን የማይወክሉ አንዳንድ ግለሰቦች ያልተለመደ ባህርይ አሳይቷቸዉ የነበረ ቢሆን እንኳን በህግ አግባብ ማስተካከል እየተቻለ እና ሌሎች ወገኖቻችን በአምስት ቀበሌዎች ዉስጥ እንዲሁም በዞኑ ልዩ ልዩ ወረዳዎች በሰላም እየኖሩ ባለበት ወቅት እነዚህ በቁጥር ጥቂት የሚሆኑ ወገኖቻችን መሄድ አልነበረባቸዉም፡፡ አሁንም ከወረዳዉ አመራርና ከአካባቢዉ ነዋሪዎች በተገኘው መረጃ መሰረት ንብረታቸዉ እንዳይጠፋ፤ መሬታቸዉንም ማንም ሰዉ እንዳያርስባቸዉ ህዝቡና አመራሩ ጠብቀው በማቆየት ላይ ናቸው። ሲመለሱም ተረክበው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ በመጠባበቅ ላይ ናቸዉ፡፡

ከአማራ ከልላዊ መንግሥት ለማጣራት በተደረገው ጥረት እነዚህ ከሰዲ ጫንቃ እጉ ኮፈሌ ቀበሌ በራሳቸዉ ፍላጎት የሄዱት ሰዎች የተወሰኑት ራያና ቆቦ አከባቢ እንዳሉ ብነገርም በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ዉስጥ እንዳልሆኑ ተገምቷል። የትም ቢሆኑ ግን እንደማንኛውም ዜጋ ያለምንም ስጋት ወደ ቄዬአቸዉ መመለስና መኖር እንደሚችሉ፣ ለዚህ ደግሞ የወረዳዉ አመራር አስፈላገዉን ድጋፍ እንደሚያደርገላቸዉ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

በቡኖ በደሌ ዞን ዴጋ፤ጮራና ድዴሳ ወረዳዎች ከወራት በፊት ተፈጥሮ በነበረዉና ወድያዉኑ አንዲስተካከል በተደረገዉ አለመግባባት ምክንያት መስተጓገል የደረሰባቸዉን እንዲሁም የአካባቢዉ ህዝብና አመራር እንዳይሄዱ እየለመናቸው ህብረተሰቡን የማይወክሉ የጥቂት ግለሰቦች ትነኮሳን ሰምተዉ በራሳቸዉ ፍላጎት ወደ አማራ ክልል የሄዱትን ሰዎች በተመለከተ ግን የሁለቱም ክልል አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሰዎቹ ተወካዮች የተሳተፉበት ዉይይት አንደተደረገና መፍትሄ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

በአጠቃላይ መሬት ላይ ያለዉ እዉነታ ከላይ የቀረበውን ይመስላል። ይህን ዕውነታ ወደ ጎን በመተዉ በተለይም በዚህ ሳምንት ነገሮችን እያጋነኑ በማቅረብ በህዝቦቻችን መካከል የኖረውንና በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጠናከረ የመጣዉን መልካም ግንኙነት ለማደናቀፍ በሚደረግ ሙከራ ህዝባችን እንዳይደናገር እናስገነዝባለን፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply