አክራሪዎቹ ከህወሓት ጋር በትብብር እየሰሩ ነው!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከጎንደር እስከ ከነቀምት፣ ከሐዋሳ እስከ አሶሳ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ባህር ዳር፣… በአጠቃላይ በየትኛውም የኢትዮጵያ አከባቢ የሚገኙ አክራሪ ብሔርተኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጥምረት ፈጥረው ለጋራ ዓላማ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በዶ/ር አብይ አመራር ከስልጣን የተወገዱት የህወሓት እና ኢህአዴግ ባለስልጣናት ህልውናቸውን ለመታደግ በሚያደርጉት ጥረት ጥምረት ፈጥረዋል። ባለፉት አመታት በሀገር ላይ በፈፀሙት ዘረፋ እና የመብት ጥሰት ተጠያቂ እንዳይሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማደፍረስ እና የፀጥታና ፍትህ ተቋማትን አቅም በማዳከም የመንግስት እና ህዝብን ትኩረት በማስቀየስ እድሜያቸውን ለማራዘም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህን አፍራሽ ተግባር በመፈፀም እና ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት ረገድ፣ እንዲሁም ሁኔታዎችን ይበልጥ በማጋነን በህዝብና መንግስት ላይ ከፍተኛ ውጥረት እና ጫና የሚፈጥሩት አክራሪ ብሔርተኛ ቡድኖች ናቸው።

ብሔርተኛ የፖለቲካ ቡድኖች በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ፣ ብሎም እንዲባባስ በማድረግ በሚፈጠረው ግርግርና አለመረጋጋት አማካኝነት የፖለቲካ ስልጣን የመያዝ ዓላማና ግብ ያላቸው ናቸው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም ብሔርተኛ ቡድኖች ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚወተውቱት ይህን ግርግርና አለመረጋጋት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የፖለቲካ ስልጣን የመያዝ ዓላማና ግብ ስላላቸው ነው። በአጠቃላይ በወንጀል የሚፈለጉ የህወሓት እና ኢህአዴግ ባለስልጣናት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ችግር በመፍጠርና በማባባስ ራሳቸውን ከህግ ተጠያቂነት ለመታደግ እየታገሉ ሲሆን አክራሪ ብሔርተኛ ቡድኖች ደግሞ በዚህ አማካኝነት የሚፈጠረውን ግርግርና አለመረጋጋት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የፖለቲካ ስልጣን መቆናጠጥ የሚሹ ናቸው። ስለዚህ ህወሓትን ጨምሮ ሁሉም ብሔርተኛ ቡድኖች ተመሳሳይ ፍላጎትና ዓላማ አላቸው።

በዚህ መሰረት የብሔርተኝነት አጀንዳ የሚያቀነቅኑት የፖለቲካ ቡድኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከህወሓት ጋር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ከህወሓት የገንዘብና ማቴሪያል ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በተለይ አክራሪ ብሔርተኝነት የሚያቀነቅኑት ነባርና አዳዲስ የፖለቲካ ቡድኖች ከፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍና ትብብር በዘለለ ከህወሓት ጋር ተመሳሳይ ዓላማና ግብ አላቸው። እሱም ኢትዮጵያዊነትን በማጥፋት ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። በእርግጥ እነዚህ አክራሪ ብሔርተኛ ቡድኖች የፖለቲካ ስልጣን በያዙ ማግስት የአንድነት ስሜትን በመሸርሸር ኢትዮጵያን ያደርሷታል። ምክንያቱም እነዚህ ብሔርተኛ ቡድኖች ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በዘለለ እንኳን በጋራ ተነጋግሮ ለመስራት እርስ በእርስ የመነጋገር ባህልና ልማድ የላቸውም። በመሆኑም የፖለቲካ ስልጣን በያዙ ማግስት የራሳቸውን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ግብግብ ሀገሪቷን ለውድቀት፣ ህዝቡን ለዕልቂት ይዳርጋሉ፡፡

(ስዩም ተሾመ)

Share.

About Author

Leave A Reply