‹‹አክቲቪስቶች›› ኳስ በመሬት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሀገራችንን ወደ ብጥብጥና ሁከት ለመዝፈቅ ታጥቀው የተነሱ በዘመኑ ቋንቋ በ‹‹አክቲቪስት›› (የሚከተሉትን የፖለቲካ አቋም ለማራመድ የተለያየ መንገድ የሚጠቀሙ አካላት) ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በከፋ ጥላቻ ወሰን በሌለው ስሜታዊነትና እብደት ታውረው አታሞና ከበሮ እየደለቁ ይገኛል፡፡ አሁን አሁን በተለይ አክቲቪስቶች በየጎራው ከትመው በአማራው፣ በኦሮሞው፣ በትግራይ፣ በሶማሌው፣ በደቡቡ ስም የጎጥ ሰልፋቸውን አሳምረው ስለታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ማሰብና በእርጋታ መመልከት ትተው ዘረኝነትን መስበክ ሥራችን ብለው ይዘውታል፡፡

ሀገራዊ ጥፋት ውድመት እልቂት እንዲከሰት ሁሉም በየጎራው እየደለቀ ይገኛል፡፡ ሁኔታው አይ አንቺ ሀገር መጨረሻሽ ምን ይሆን? ለማለትም ያስደፍራል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም በመጠቀ የስልጣኔ ማማ ላይ ሆኖ እያለ እኛ ዘንድ ይሄንን የዝቅጠት አስተሳሰብ ሲያራምዱ መመልከት በእጅጉ ይዘገንናል፡፡ አለመታደልም ነው – በአስተሳሰብ እልፍ ፈቀቅ አለማለት፡፡ ‹‹ያልታደልሽ እንደምን አደርሽ›› ይል ነበር የድሮ ሰው፡፡ የእኛም ነገር መገለጫው ይኸው መሆኑ ነው፡፡

‹‹ትላልቆቹ አለፉና …›› እንደሚባለው አይነት ኢትዮጵያዊነትን ያከበሩ ያነገሱ ያወደሱትን በአየንበት አይናችን ‹‹ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ›› የሚባለው ዘመን ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ የአክቲቪስቶቹን መፍላትና በጸረ ሀገርና ሕዝብ ማባላት ስምሪት ላይ መገኘታቸውን ላየና ላስተዋለ ዘመኑ የግርምቢጥ ነው ብሎ ቢያስብ አልተሳሳተም፡፡

ይህችን ሀገር ለማፈራረስ በየበኩሉ እየተጋ ያለው የአክቲቪስቶቹ ሠራዊት በዘመናት አብሮነት ሕብርነት ፍቅርና አንድነት ጸንቶና ተገምዶ ከሕይወት እስከ መቃብር ድረስ ተሳስቦ ተዋዶ ተላቅሶ በሰርጉም በሀዘኑም አብሮነቱን አጽንቶ የኖረውን ሕዝብ እነሆ ሊያባሉት ሊያናክሱት ሊያፋጁት ደፋ ቀና ማለቱን መያያዛቸውን መታዘቡ አይቀርም፡፡ ይሁንና አይሳካም፡፡

በአክቲቪስትነት ስም በተለያየ አካውንትና ማንነት ብእራቸውንና መርዛማ ጥርሳቸውን አግጥጠው አፍጥጠው ዘመቻ የከፈቱ በርካታ ናቸው፡፡ ይህን በቅጥ ላስተዋለ አሳፋሪ የታሪክ ወቅትና ምእራፍ ላይ መድረሳችንን ይመሰክራል፡፡ የእነርሱ ደስታ፣ ሆታና ጭፈራ ሀገር በእሳት ነዳ ሕዝቦቿም ተላልቀው ባዶና ምድረበዳ መሬት ማየት ነው፡፡ ያላወቁት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ የተሰኘችው ምድር አጥፊዎቿን ሁሉ እያጠፋች፤ወደቀች ሲሉ እየተነሳች፤ጠፋች ሲሉ ዳግም እያንሰራራች የኖረች የምትኖርም ታላቅ ምስጢራዊ ሀገር መሆኗን ነው፡፡

በሀዘንና በደስታ በትውልድ ፈረቃ ውስጥ ተሳስሮ ረዥም ዘመናትን በአብሮነት የኖረን ሕዝብ ለመከፋፈል ለመበታተን ማሴር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በቅጡ ካለማጤን የመነጨ መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከደምና አጥንት ጋር ተለስኖ የተጋገረ በማይበጠስ ክር የተገመደ በምንም መልኩ ሊበጠስ የማይችል ጠንካራ የብረት ሰንሰለት መሆኑን አክቲቪስቶቹ አልተረዱም፤ አላስተዋሉትም፡፡

በእነርሱ ሴራና የጥላቻ መርዝ መርጨት የሚናቆር የሚጠፋፋ የሚበላላ የሚጫረስ ሕዝብ የለም፡፡ አይኖርምም፡፡ የአክቲቪስቶቹ ደስታ የሕዝብ እልቂት የሀገር ውድመትና ጥፋት ተፈጥሮ ተከስቶ ማየት ነው፡፡ የሠላም የፍቅር የመቻቻል የአንድነት የይቅርታና የምሕረት መልዕክተኞች አይደሉም፡፡

አክቲቪስቶች ዘመኑ በፈጠረላቸው ማሕበራዊ ድረገጽ በመጠቀም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያናቁር መልዕክትን በማስተላለፍ ከድርጊቱ ጋር የማይገናኝ ፎቶ ከሌላ ሀገር በማምጣትና በፎቶ ሾፕ አቀናብረው በመለጠፍ ሕዝብ ለዘመናት የገነባውን አብሮነት ለመናድ እርስ በእርሱ እንዲባላ ለማድረግ ሰፊ ሰልፍ ይዘዋል፡፡ የማይሳካ ከንቱ ድካም መሆኑን ግን ሊረዱ ይገባል፡፡

በየጎራው አሰላለፍ ለይተው የቆሙ ዘረኞች የፖለቲካ ጥላቻ አራማጆች በአክቲቪስትነት ተሰልፈው የሚረጩት መርዝ ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት መከላከል ይገባል፡፡ የዓለም ሁሉ የሰው ዘር የመጀመሪያ መፍለቂያ መገኛ በሆነችው ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ ተወልዶና አድጎ ዘረኛ፣ ጎጠኛና መንደርተኛ መሆን በእጅጉ ያማል፡፡ ያሳፍራልም፡፡ ሀገርን የመነሻ ታሪክን በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የነበረንንና ያለንን ታላቅ ክብርና ስፍራ ያዋርዳል፡፡ የተዘራው እርሻ እምቧጮ አፈራ የሚባለው የአባቶች አባባል የሚገልጸው ይሄንኑ ነው፡፡ ከትልቅነት ወደ ትንሽነት ለመፍገምግም መሮጥ፡፡

ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፋ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገች በኩር ሀገር ነች፡፡ የደቡብ አፍሪካውን የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን በሀገርዋ መሬት ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ወታደራዊ ትምህርት ያስተማረች በዓላት አቅም እስከ ነጻነት የረዳች ነጻ ሲወጡም አብራ የቆመች ታላቅ ሀገር፡፡ የዚምባብዌን የነጻነት ትግል ደግፋ እስከ ነጻነታቸውም አብራ የቆመች ሀገር ኢትዮጵያ፡፡

ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፎ ለአፍሪካውያን ነጻነት ያደረገችው ታላቅ የትግል አስተዋጽኦ በምንም መልኩ የሚረሳ የሚዘነጋም አይደለም፡፡ እኛ ደልቶን ሕዝባችን ተመችቶት አልነበረም የአፍሪካን ነጻነት ፋና ወጊ ሁነን ስንደግፍ የኖርነው፡፡ ዘረኝነት ባርነትን በደልንና መጠቃትን ነጻነትን ማጣትን አምርረን ስለምንጠላ ነው፡፡ የኢጣሊያን ፋሽስት ወረራን የመከትን የመጀመሪያውን የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ዓለም አቀፋዊ ድል በአፍሪካ መሬት ላይ ያረጋገጥን ዘረኝነትን አምርረን የተዋጋን ነን እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡

ኢትዮጵያ የአትንኩኝ ባዮች ሀገር ነች፡፡ ጥቃትን ወረራን የባእዳንን የበላይነት የማይቀበሉ ለባርነት የማይንበረከኩ ለነጻነታቸው ለክብራቸው መሞትን ታላቅ ክብር አድርገው የሚቆጥሩ ጀግኖች ሕዝቦች ያሉባት ሀገርና ምድር ነች፡፡ በዚህ ሁሉ ለሀገር ክብር በተደረገ የአባቶቻችን ታላቅ ትንቅንቅና ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ዘርና ጎሳ ሳይለዩ በአንድ ቆመው በአንድ ተሰልፈው በአንድነት ጸንተው ወራሪ ጠላቶቻቸውን ሁሉ አሳፍረው መልሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እንደዛሬው አይነት ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ የሚጥሩ አክቲቪስት ነን የሚሉ ዘረኞችና ጎጠኞች ተፈጥረውም ታይተውም አይታወቁም፡፡ ከአንድነትና ከሕብረት ይልቅ መበታተንን መከፋፈልን የሚሰብኩ አንዳንድ አክቲቪስቶች ለታሪካችንና ለእኛነታችን እንግዳ ናቸው፡፡ ዛሬም ወደፊትም አይበጁንም፤ አይጠቅሙንም፡፡

አክቲቪስቶች ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባላ የሚያናክስ መርዝ እየረጩ ወገንን እርስ በእርሱ ለማጫረስ ብሎም ሀገራችንን ለማጥፋትና ለመበታተን የማይነዙት የፈጠራ አሉባልታና ወሬ የለም፡፡ ይልቁንም ለአንድነት ለፍቅር ለሕብረት ለሰላም ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቢተጉ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡

አባቶቻችን ፈጣሪን ከማመን ውጭ ዛሬ በቀለም ትምሕርት ተስፈንጥሬአለሁ እንደሚለው አይነት ትውልድ ዘመናዊ እውቀት አልነበራቸውም፡፡ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ስሜት የማያስቡ ስለሀገር ትልቅነት የሚጨነቁ ነበሩ፡፡

የዛሬው በገዛ ሀገሩና ወገኑ ላይ መአት ለማውረድና መተላለቅን ለማስፈን እልቂትና ደም መፋሰስ ተከስቶ ምድረበዳ እንድትሆን ሌት ተቀን እየሰራ የሚገኝ የአክቲቪስቶች ሠራዊት የሀገሪቱን ታሪካዊ ጠላቶች ዓላማ እያሳካ መሆኑን በውል ያስተዋለው አይመስልም፡፡ ዘረኝነት የዓለማችን የመጨረሻው የዘቀጠ፣ የወረደ፣ የከፋና የከረፋ አስተሳሰብና እምነት ነው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በመጽሀፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርአን አንድና እኩል ነው፡፡

የዘመኑ አክቲቪስቶች የተነከሩበት የዘረኝነት አስተሳሰብና ጥላቻ ሀገርን ከማጥፋት ሕዝብን ችግርና አደጋ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡ ከየትኛውም ብሔርም ሆነ ብሔረሰብ የወጡ ግለሰቦች ጨካኝ አረመኔ ክፉ ዘራፊ ቀማኛ ወንበዴ ነፍሰ ገዳይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በምንም ተአምር ግን ሕዝብን ሊወክሉ አይችሉም፡፡ ወክለውም አያውቁም፡፡

በግለሰቦች የቆሸሸ አስተሳሰብና ነውረኛ ድርጊት መጠየቅ ያለባቸው ግለሰቦች እንጂ እነሱ የተፈጠሩበት ማሕበረሰብ ወይንም ሕዝብ አይደለም፡፡ አክቲቪስቶች መሰረታዊ ስህተታቸውም ይህ ነው፡፡ ሕሊናቸው በጥላቻ በመጋረዱ ሀቁን ለማየት ስለተሳናቸው ጭፍንነት ስለሸፈናቸው ከመንገድ እየወጡ በመጋለብ ላይ የሚገኙትም ለዚህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፡፡ በዘመኑ እውቀት ባይገፉም ታላላቅ ልበ ብርሀን አባቶች የተፈጠሩባት የመሩዋት ያስተዳደሯት ሀገር ነች፡፡ ባርነትን ሳይቀበሉ ለውጭ ኃይላትም ሳያጎበድዱ ሳይንበረከኩ ነጻነታቸውን አሳልፈው ሳይሰጡ ጠብቀው አስጠብቀው የኖሩባት ለትውልድ ነጻነትን በክብር ያወረሱባት የደመቀ ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡

ወቅቱ የፈለፈላቸው አንዳንድ አክቲቪስቶች ግልብ በሆነ መልዕክታቸው የማንነታቸውን መሰረት ድርና ማግ ካለማወቅ ሊያፈራርሱ የሚሮጡት ኢትዮጵያንና ለፍቶ አዳሪ ልጆቿን ነው፡፡ በስራቸው እንደሚያፍሩ በትውልድ ውስጥ እንደሚሸማቀቁ ግን በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል፡፡ ጎይቶምም ሆነ ክንደያ የትግራይን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ አየለም ሆነ አበበ ወይንም ጎንጤ የአማራውን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ ዱፌራም ሆነ ወልቀባ ወይንም ጫላ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ ግለሰቦች መጠየቅ ያለባቸው በግለሰብነታቸው በሰሩት የየራሳቸው የግል ሥራ ብቻ ነው፡፡

በግለሰቦችና በድርጅቶች መነሻነት እያስታከኩ ጸንቶ የኖረውን የሕዝብ ፍቅር አንድነት ሕብርነት የመቻቻልና የመከባበር ባሕል ለመናድ በአክቲቪስትነት ስም መንቀሳቀስ እሳት ለመጫር መሞከር በእጅጉ አሳፋሪና ወራዳ የሆነ ተግባር ነው፡፡ አክቲቪስቶች ከዚህ እብደታቸው ታቅበው ስለ ሕዝብ አብሮነት ወዳጅነት መቻቻል ይቅርታና ፍቅር በአብሮነት በመደመር ችግሮቻችንን እየፈታን ታላቅ ሀገርን ስለ መገንባት ማሰብና መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ጥንትም ታላቅ ሀገር ነበረች፡፡ አሁንም ታላቅ ሀገር ትሆናለች፡፡

‹‹አክቲቪስቶች›› ሆይ ለዛሬ የዘመኑ ለጆች ነገሩን አረጋጉት ለማለት የሚጠቀሙበትን ‹‹ኳስ በመሬት›› የምትል አባባል ለመጠቀም ወድጃለሁ፡፡ ጥላቻንና ክፉ ክፉውን መዝራት ትታችሁ መረጋጋትና ሠላም በሚያሰፍኑ መልዕክቶቻችሁ እንገናኝ፡፡

 

መሐመድ አማን

Share.

About Author

Leave A Reply