አዋሽ ባንክ ለዳያስፖራዎች እጥፍ ወለድ የሚያስገኝ አገልግሎት ጀመረ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አዋሽ ባንክ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግዥን ጨምሮ ለሌሎች ቢዝነስ እንቅስቃሴዎቻቸው ሊውል የሚችል የተለያዩ የብድር አማራጮችን ሊያገኙ የሚችሉበትን የባንክ አገልግሎቶችን ማመቻቸቱን አስታወቀ፡፡ ከመደበኛ የወሊድ ምጣኔ በእጥፍ ወለድ የሚከፈልበት አገልግሎትም አለኝ ብሏል፡፡

በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ታሳቢ ያደረገው የአዋሽ ባንክ የዳያስፖራ ልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶች በርካታ ስለመሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለመኖሪያ ቤትና ለቤት ግዥ ሊያውለው የሚችለውን ብድር ማመቻቸቱ አንዱ ነው፡፡ የዳያስፖራ ማኅበረሰቡን ራዕይ ይሳካ ዘንድ የተለያዩ የብድር አማራጮችን ማዘጋጀቱን ባንኩ ገልጿል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ የቤት ባለቤት ለማድረግ ባዘጋጀው የመኖሪያ ቤት ወይም ለንግድ ቤት ግዢና ግንባታ የሚውልና አነስተኛ የወለድ ተመን ያለው አገልግሎቱ ተጠቅሷል፡፡ ብድሩ በረዥም የክፍያ ዘመን የሚጠናቀቅ እንደሆነ የሚገልጸው ይህ የባንኩ መረጃ፣ እንዲህ ያለውን አገልግሎት እውን ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የቤት አልሚዎች /ሪል እስቴት/ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ መሆኑን ባንኩ ገልጿል፡፡ ለአውቶሞቢል ግዥና ለግል ፍጆታ ይኸውም ለትምህርት ቤት፣ ለሕክምና፣ ለቤት መገልገያ ዕቃዎችና ሌሎችም የብድር አማራጮችን በዝቅተኛ የወለድ መጠን ለዳያፖራው ማኅበረሰብ እንደተዘጋጀም ታውቋል፡፡

ከዚህም ሌላ ዳያስፖራው በሚኖርበት አገር በውጭ የምንዛሪ ተቀማጭ ሒሳብ አማካይነት የተለያዩ አገልግሎቶችን ማዘጋጀቱም ተጠቅሷል፡፡ ይህም ደንበኞች በጊዜ ገደብ የተቀመጠውን ዝቅተኛውንና 5,000 ዶላር በሚያስቀምጡበት ጊዜ፣ የዓለም አቀፍን የወለድ ምጣኔ ጣሪያ ግምት ውስጥ በማስገባት በባንኩና በደንበኛው የጋራ ስምምነት ላይ የተመሠረተ ጠቀም ያለ ወለድ የሚያገኝ አሠራር ነው ተብሏል፡፡ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ አገልግሎት ወይም ተንቀሳቃሽ ሆኖ ወለድ የማይከፈልበት የአገልግሎት ዓይነትም ለዳያስፖራው የተሰናዳ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች ገንዘባቸውን በማንኛውም ወቅት ቼክ በመጻፍ ወጪ ማድረግ የሚያስችላቸው አሠራር ነው፡፡ ይህ የቁጠባ ሒሳብ አስቀማጮች የገቢ ንግድ አገልግሎትን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን ሊረዳቸው የሚችል መሆኑንም መረጃው ያስረዳል፡፡

በአዋሽ ባንክ፣ ለዳያስፖራው የተመቻቸው ሌላው አዲስ አገልግሎት የባንኩ አካውንት የሚከፍቱ ዳያስፖራ ደንበኞች በውጭ ምንዛሪ የሚያስገቡት ገንዘብ በብር ተመንዝሮ ሲቀመጥላቸው፣ በብር የተቀመጠው ገንዘባቸው ከመደበኛው ወለድ የበለጠና በተለየ ወለድ የሚታሰብላቸው መሆኑ ነው፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመውም በዚህ ዓይነት መንገድ የሚቀመጥ ገንዘብ ባንኩ ከመደበኛው የወለድ ምጣኔ በእጥፍ ወለድ የሚከፍልበት ይሆናል፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት መደበኛ የቁጠባ ወለድ ምጣኔ ሰባት በመቶ ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ለመክፈል የተዘጋጀው 14 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ውጭ አገር ሒሳብ ወይም ገንዘብ መዘዋወር በማይችለው በብር የሚቀመጠው ገንዘብ ላይ የሚሠራበት ይሆናል፡፡ ይህም ባንኩ ዜጐች ከውጭ አገር በሚልኩት ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ ተቀይሮ በብር የሚቀመጥበትንና በአገር ውሰጥ የተለያዩ ክፍያዎችን ለመፈጸም የሚያገለግል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ታሳቢ ያደረገ የሙራሀባ የብድር አገልግሎት አማራጭን ያዘጋጀ መሆኑንም ገልጿል፡፡ በዚህ አገልግሎት ደንበኞች የመኖሪያ ቤት ወይም የንግድ ቤት መግዥያና መሥሪያ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መጀመሪያና ማስፋፊያ እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን የያዘ አገልግሎት ነው፡፡

አዋሽ ባንክ ለመላው የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በዚህ አገልግሎት እንዲጠቀሙ በማድረግ ባንኩ ከዳያስፖራው ጋር በጋራ ለመሥራት የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያው የግል ባንክ ነው፡፡ ከ375 በላይ ቅርንጫፎች ያሉትና ባለፈው የሒሳብ ዓመት መዝጊያ በትርፍ፣ በብድር፣ በተቀማጭ ሒሳብ፣ በሀብትና በሌሎችም መሥፈርቶች ከግል ባንኮች መሪነቱን መያዙ ተጠቅሷል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 1.9 ቢሊዮን ብር ማትረፉ አይዘነጋም፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply