አዲሱ “የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ” ( ክፍል አንድ) ከኤርሚያስ ለገሰ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መንደርደሪያ፣

የዛሬ አስር አመት ( 2001ዓ•ም•) ወጥቶ በተግባር ላይ ከዋለው የበጐ አድራጐት እና ማህበራት አዋጅ ጋር ከጥንስሱ እስከ ህግ ሆኖ መፅደቁ ሂደቱ ላይ የነበረኝ ትስስር ከፍተኛ ነበር። ከምርጫ 97 በኃላ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችን ለማጥላላት በመንግስት እና በኢህአዴግ ቢሮ ደረጃ የፓለቲካ ዘመቻ ለመክፈት የፕሮፐጋንዳ እቅድ ሲነደፍ እምብርቱ ላይ ነበርኩ። ከእኛ አልፍ በዘመቻው ላይ ትላልቅ የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮችን አውቀውም ሆነ ሳያውቁት እንዲሳተፉበት ሲደረግ የዳር ተመልካች አልነበርኩም። ለምሳሌ አቶ ልደቱ አያሌው ( እስከ አሁንም ሳያውቅ እንደተሳተፈ ነው የማምነው!) መያዶች ላይ በማስረጃ ላይ እየተደገፈ ሲያብጠለጥላቸው ኢንፎርሜሽኑ ወደ ዳታ የተቀየረው ኢህአዴግ ቢሮ ነበር። ወደ ሚዲያ ለክርክር ከመግባቱ በፊት ዶክመንቱ በእጅ አዙር (ሳያውቀው) እንዲደርሰው ሲደረግም በቅርብ ርቀት ተመልክቻለሁ።

ከዚህ በተጨማሪም የ2001ዓ•ም• የበጐ አድራጐት እና ማህበራት አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በማብራሪያው እና ረቂቅ ህጉ ላይ ከ50ሺህ በላይ ለሚጠጉ የመዋቅራችን አባላቶች በፕላዝማ ቀጥታ ስርጭት ያሰለጠነው እኔ እና ወይዘሪት ፍሬህይወት አያሌው ነበርን። በቅርብ ለማታውቋት የዚህ መጣጥፍ አንባቢያን ተጋዳሊት ፍሬህይወት የቀድሞ ብአዴን አመራር እና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስት ዲኤታ የነበረች ሲሆን አሁን ጡረታዋ ደርሶ የፓርላማ አባል ሆናለች። እዚህ ላይ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው እኔ እና ፍርዬ ለአባላት የማሰረፅ(ኢንዶክትሪኔሽን) የሰራነው ሜክሲኮ ጀርባ የሚገኘውን መንግስታዊ የሆነው ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ማሰራጫ ተቋምን በመጠቀም ነበር። በሌላ አነጋገር ለፓርቲ ፕሮፐጋንዳ ስራ የተጠቀምነው የመንግስት ንብረትና ተቋምን ነበር።

አዋጁ ከፀደቀም በኃላ ዝርዝር ይዘቱን ለአለምና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ የተደረገው በኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የበላይ ኃላፊዎች ነበር። የጽህፈት ቤቱ ሃላፊዎች አዋጁን ለጋዜጠኞች ስናብራራ በአንድ በኩል በነበረን የተሳሳተ የፓለቲካ አመለካከት፣ በሌላ በኩል ለመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያዳበርነው መረን የለቀቀ ጥላቻ ምክንያት እርስ በራሱ የሚቃረን ነበር። በመድረኮቹ እና መግለጫዎቻችን አይደለም ጋዜጠኞች መዋቅራችን እንኳን የምናቀርበው አመክንዬ ብዙም እንደማይዋጥላቸው ገፅታቸው ያሳብቃል።

እርግጥም የፓለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ ህግ እያወጣን ዲሞክራሲው እየሰፋ ሄዷል ብሎ መናገር በሃፍረት እስከ መቅላት የሚያደርስ ነው።… እርግጥም እየወጡ ያሉት አዋጆች መሰረታዊ መነሻቸው ለአፈና የተዘጋጁ ፀረ ዲሞክራሲ መሆናቸው እየታወቀ ይዘታቸው ዲሞክራሲያዊና ተራማጅ ነው ብሎ እንደ የገደል ማሚቴ ማስተጋባት አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ነው።… እርግጥም አዋጁ ወደ ተግባር ሲለወጥ በርካታ ድርጅቶች እንደሚከስሙ እየታወቀ አገሪቷን መያድ ሊያጥለቀልቃት እንደሆነ መስበክ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነበር።

#ሁለት: – የቀድሞ የበጐ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ “ ትሩፋት”

2•1• “ የትሮይ ፈረሶች”

በተደጋጋሚ እንደተገለጠው ህውሓት/ ኢህአዴግ በጠላትነት ከፈረጃቸው የፓለቲካ አስተሳሰቦች ዋነኛው የግለሰብ ነፃነትንና ነፃ ገበያ መሪ መፈክሩ ያደረገውን የሊብራሊዝም አመለካከት ነው። ፓርቲው የሊብራሊዝም አቀንቃኝ የሆኑ አገሮች በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት በማስነሳት ከስልጣን ሊያባርሩኝ ይችላሉ የሚል የቀን ቅዠት አለበት። በሌላ በኩል ህውሓት/ኢህአዴግ የቀለም አብዮት እንዲካሄድብኝ ለዚህ ስራ ተብለው የተቃኙት ወይም እዚያው በዚያው የሚፈጠሩት መያዶች ናቸው ብሎ ያምናል። ለእነዚህ ድረረጅቶች “ የትሮይ ፈረሶች” የሚል ስያሜ ሰጥአቸዋል። በወቅቱ የመያዶችን አዋጅ ለማብራራት በኢህአዴግ ልሳን በሆነው አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ እነሱን አስመልክቶ ሰፊ መጣጥፍ ወጥቶ ነበር።በዚህ ጽሑፍ ላይ እንደ የአሜሪካው የአለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ•ኤአይ• ዲ) አይነት አለም አቀፍ መያዶች በቀለም አብዮቶች ላይ የሚሳተፉ ብቻ ሳይሆን ከሮኬቶችና ሚሳይሎች በላይ ግምት የሚሰጣቸው የመንግስት መገልበጫ መሳሪያዎች እስከመሆን እንደሚደርሱ ተገልጦ ነበር። የፅሑፉም ማጠንጠኛ ይሄ ነበር።

በአጠቃላይ መልኩ ገዥው ፓርቲ ህውሓት መያዶችን የሚመለከትበት መነፅር በጠላት መስመር ውስጥ የሚሰለፍ ነው። በዚህ ምክንያት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስቀድመው መጥፋት አለባቸው ብሎ ያምናል። አለበለዚያ የቀለም አብዮት መሃንዲስ በመሆን ከጨዋታ ውጭ እንደሚያወጡት የፀና እምነት አለው። እርግጥም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስለ ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት ፣ የግለሰብ ነፃነት፣ ነፃ ገበያ ማስተማር ከጀመሩ የህውሓት/ኢህአዴግ የስልጣን መቆያ ምሰሶ ስለሚገረሰስ እድሜው ያጥር ነበር።

2•2• የድርጅቶቹ አመሰራረትና ምዝገባ

ለአስር አመታት በስራ ላይ የዋለው የበጎ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ የአገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅት የሚለውን ለመከፋፈል በዋናነት የተጠቀመው የፋይናንስ ምንጭን ነበር። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሆነው ከአስር በመቶ በላይ የሆነውን ፋይናንስ ከውጭ ድርጅቶች የሚያገኙ ከሆነ የሚመዘገቡት እንደ ውጪ ድርጅት ይሆናል። በአንፃሩ ከአስር በመቶ በታች የፋይናንስ ምንጫቸውን ከውጪ የሚያገኙ ከሆነ “ አገር በቀል ድርጅቶች” የሚል ስያሜ ያገኛሉ። ቃል በቃል ለመግለፅ ያህል በዚህ አዋጅ ቁጥር 621/4521 አንቀጽ 2 ቁጥር 3 መሰረት “ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ማኀበር” ማለት ሁሉም አባላቱ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ፣ ከአስር ከመቶ በላይ ገቢ ከውጭ ምንጭ የሚያገኝና በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት የተቋቋመ ድርጅት ነው ይላል።

እዚህ ላይ በቀድሞው ህግ መያዶችን በዚህ መልኩ መከፋፈል ችግሩ ምንድነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በዚህ መልኩ ክፍፍል መደረጉን ኢትዮጵያውያን፣ ሲቪክ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በጋራ ድምፅ ለምን አጥብቀው ተቃወሙት። ተገቢ ጥያቄ ነው።

ነገሩ እንዲህ ነው፣

በመጀመሪያ ለማንም ግልፅ እንደሆነው የአብዛኛው የኢትዮጵያ ዜጐች የፋይናንስ አቅም ከእለት ኑሮ ተርፎ ለበጐ ፍቃደኝነት በስጦታ የሚሰጥ አይደለም። በጣት የሚቆጠሩ የናጠጡ ሃብታሞች በአገሪቱ ቢኖሩም በባህላችን ውስጥ በበጐ ፍቃድ መለገስ ዝቅተኛ በመሆኑ መያዶች ከቱጃሮቻችን ገንዘብ የማግኘታቸው እድል ወደ ዜሮ የተጠጋ ነው። የሜሪጆይ መስራችና ዴሬክተር ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ እኔ በማዘጋጀው የኢሳት “ ሁለንተናዊ እይታ” ፕሮግራም ላይ እንደገለጠችው ኢትዮጵያዊ ቱጃርች ለበጐ አድራጐት ስራ መቶ ብር ከሚለግሱ ይልቅ በአስር ሺዎች አውጥተው የሸራተን ሺቫስ እና ማርቲኒ ቢጋብዙ ይመርጣሉ። የኢትዮጵያ ሃብታሞች ለበጐ አድራጐት ስራ እጃቸው ከሚፈታ ይልቅ ቆማሪ ቤት ገብተው ከበር መልስ ሂሳብ ቢዘጉ የበለጠ ይደሰታሉ። እንደ ፈረንጅ ዶሮ ደረታቸውን ይነፋሉ።

የሆነው ሆኖ አገር በቀል ድርጅቶች የፋይናንስ አቅማቸውን ከዜጐች የማግኘት እድላቸው ጠባብ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ከስራ ውጪ እንደሚሆኑ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የሚታወቅ ነበር። በተግባርም ህጉ በስራ ላይ በዋለ በጥቂት አመታት ውስጥ ከ400 በላይ መያዶች የመዘጋት እጣ ፈንታ ገጠማቸው። ከ3ሺህ የማያንሱ መያዶች የህልውና አደጋ ተጋረጠባቸው። ለምሳሌ ያህል ከ1•5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን እየረዳ የሚገኘው ሜሪ ጆይ በአዋጁ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አገር በቀል ድርጅቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ሲስተር ዘቢደር በቁጭት ውስጥ ሆና ገልጣለች።

2•3• የስራ ስምሪት

ላለፉት አስር አመታት በስራ ላይ ያለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ክፍፍል በሁለተኛ ደረጃ ተፅእኖ ያሳደረው በመያዶቹ የስራ ስምሪት ላይ ነው። ገቢያቸውን ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ የሚያገኙ መያዶች የውጭ ድርጅት ሆነው የሚመዘገቡ በመሆኑ በፓለቲካዊ እና ሲቪል መብቶች ላይ መሰማራት አይችሉም። በዚህ ምክንያት ከአስር በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጭ የሚያገኙ ድርጅቶች በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች …ወዘተ መብቶች ላይ ፕሮግራም ቀርፀው መንቀሳቀስ አይችሉም። ዛሬ ላይ ተቆሞ ሲታሰብ ካገኘኸው መቶ ብር ውስጥ 11 ብሩን ከውጭ በእርዳታ ስላገኘህ በሴቶች መብት ላይ አትሰራም ማለት ያሳፍራል። የህፃናት መብት እንዲጠበቅ ማስተማር አትችልም ማለት ያሸማቅቃል። አካል ጉዳተኞችን ለማብቃት እድል ሊሰጣቸው አይገባም ማለት ጥፍር ውስጥ ተደበቅ ያሰኛል። እውነትም የአዋጁ ዋነኛ ባለቤቶች መደበቅ የነበረባቸው መቀሌ ሳይሆን ጥፍራቸው ውስጥ መሆን ነበረበት።

2•4• የአስተዳደር ወጪዎች

ለአስር አመታት በስራ ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በርካታ አሳሪ አንቀጾችን ያካተተ ነበር። ከእነዚህም በቅድሚያ የሚይዘው “ የአስተዳደር ወጪ” በሚለው ውስጥ የተካተቱት ተግባራት በዚህ ማእቀፍ ውስጥ መግባት ያልነበረባቸው ነበሩ። ከትርጉሙ ለመነሳት የአስተዳደር ወጪ ማለት በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከሚያከናውነው የፕሮጀክት ሥራ ጋር ተያያዥነት የሌለው ነገር ግን ለድርጅቱ ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነ ከአስተዳደር ስራዎች ጋር የተያያዘ ወጪ ማለት ነው። ይሁን እንጂ እንደ ስልጠና የመሳሰሉ ቁልፍ ስራዎች በዚህ ክፍል ሆን ተብሎ እንዲሸፈኑ የተደረገበት ነበር። ይህም ድርጅቶቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደ አስተዳደር ወጪ ስለሚወሰድባቸው ተልእኮአቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ነበር።

በአጠቃላይ መልኩ ላለፉት አስር አመታት በስራ ላይ የዋለው የበጐ አድራጎት ድርጅትና የማህበራት አዋጅ ነፃነታቸውን የጠበቁ ሲቪል ማህበረሰቦች እንዳይኖሩ አድርጓል። ዜጐች በፓለቲካው እና በሲቪል መብቶች መስክ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ገድቦ ነበር። በሌላ በኩል መያዶችና ማህበራት በፓርቲው ቁጥጥር ስር የዋሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

( በክፍል ሁለት በአዲሱ “ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ” ላይ እመለሳለሁ። እስከዛው የሃሳብ ደሃ ከሆኑ ሰዎች ” ፀረ – ምናምንቴ” ስድብ ይሰውራችሁ። እርግጥ ሃውልታችሁ የሚያብረቀርቀው እነሱ በሚወረውሩት ባልጩት ድንጋይ መሆኑን አትርሱ። የሳምንት ሰው ይበለን።)

Share.

About Author

Leave A Reply