‹‹አገር በማንም ፈቃድ ተሠርታ የምትፈርስ የእጅ ሥራ አይደለችም!›› – የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ቱት ኮት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

269 ባለሃብቶች ጋምቤላን ብቻ ሳይሆን አገር እና ሕዝብን ዘርፈዋል
• ትዕቢት ለውርደት እንጂ ለክብር ቅርብ አይደለም!

በ1968 ዓ.ም. ጋትሉዋክ ቱት ኮት በጋምቤላ ክልል ጄካዎ በምትባል ወረዳ ተወለዱ፡፡ ኑዌር፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡

በ2010 ዓ.ም. እኤአ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሐምሌ 2015 እኤአ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በወንጀል ፍትሕ እና በሰበአዊ መብቶች (CRIMINAL JUSTICE & HUMAN RIGHTS) የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በለንደን ኮመን ዌልዝ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት በሕዝብ አስተዳደር (PUBLIC ADMINISTRATION) የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል፡፡ በትርፍ ሰዓቴ መጽሐፍ ማንበብ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች መሳተፍ እንዲሁም የብዙሃን መገናኛዎችን በመከታተል አዘወትራለሁ ይላሉ፡፡

የተከበሩ ጋትሉዋክ ቱት ኮት ባንኮክ ሕክምና አድርገው፤ አገግመው ከተመለሱ በኋላ አነጋግረናቸዋል፡፡

ጥያቄ ፡ የበረሃዋ ገነት፤ ጋምቤላ እንዴት ይገልጧታል?

ጋትሉዋክ ፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች አንዱ ነው። ዋና ከተማው ጋምቤላ ነው። የሕዝብ ብዛቱ 306,916 ነበር። ኑዌር ፤ ማጃንግ ፤ ኦፖ እና ኮሞ ብሄርሰቦች ይኖራሉ።

ጋምቤላ የተመሰረተችበት በ1904 ተቆረቆረች፡፡ 100 ኛ የልደት በዓሏን የበረሃዋ ገነት፤ ጋምቤላ ከተማ አክብራለች፡፡ በባሮ ወንዝ ላይ ባላት አቀማመጥ የበረሃዋ ገነትን ልዕልና ይዛለች፡፡

በሦስት ብሔረሰብ ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ ሥር በሚገኙ 13 ወረዳዎች፣ በ649 ቀበሌዎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረችው ጋምቤላ ጠቅላላ የቆዳ ስፋቷ 30,065 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ሃያ በመቶው የክልሉ መሬት በደን የተሸፈነ ነው፡፡

የበረሃዋ ገነት፤ ጋምቤላ ክልሉ በኢትዮጵያ ምእራባዊ ጫፍ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በምእራብ ደቡብና ሰሜን ሱዳንን ሲያዋስን፣ በደቡብና በምስራቅ ደግሞ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትን ያዋስናል፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜንና ምስራቅ ያዋስኑታል፡፡

ከአዲስ አበባ በ776 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

አብዛኛው የክልሉ ህዝብ አብዛኛውአርሶ አደር እና በከፊል አርብቶ አደር ነው፡፡ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በቆሎ፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎችን፣ ማንጐ፣ ሙዝና ወዘተ በማምረት ይተዳደራሉ፡፡

አማርኛ የክልሉ የሥራ ቋንቋ ነው፡፡ አምስቱ የብሔረሰቦቹ የራሳቸው ቋንቋ አላቸው፡፡

የተለያዩ እምነት ተከታዬች የሚኖሩበት ክልል ነው፡፡ ኘሮቴስታንት፣ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የሰባታኛው ቀን አድቨንቲስት፣ ሁለቱ የመካነ ኢየሱስ ሲኖዶች፣ የሙሉ ወንጌል፣ እስልምና፣ ካቶሊክ ፣ ባህላዊ ሀይማኖት እንዲሁም የሌሎች ሀይማኖት ተከታዮች ይኖሩበታል፡፡

ባሮ ወንዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው ለመጓጓዣ የሚያገለግለው ወንዝ በዚሁ ክልል ይገኛል፡፡ ወንዙ ክልሉን ከሱዳን ካርቱም ሶባት ጋር ያገናኛል፡፡

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ የሚገኝ የቱሪስት መሰህብ ነው፡፡ 4ሺህ 575 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በውስጡም 69 ዓይነት የአጥቢ እንስሳት፣ 327 የተለያዩ አዕዋፋትና 492 የእጽዋት ዝርያዎችን ይዟል፡፡ በተጨማሪም እንደ ዝሆን፣ ጐሽ፣ ዝንጀሮና በቀቀን የመሳሰሉ የዱር እንሰሳት ይገኙበታል፡፡

በብቸኝነት በጋምቤላ ውስጥ የሚገኝ ብርቅዬ እንስሳ ሌቹዌ እንዳለ እንዳትረሱ፡፡ እንቁላል በመጣል የሚራባ እንስሳን ለማየት እባክዎ ጋምቤላ ይምጡ፡፡

ጥያቄ ፡ በበረሃዋ ገነት፤ ጋምቤላ የነበርዎት የሥራ ኃላፊነት፤ (ከየት ተነስተው የት ደረሱ?)

ጋትሉዋክ ፡ በ1997ዓ.ም. በኑዌር ብሔረሰብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ፣ የክልልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ የክልልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮምሽን ኮምሽነር፣ ከየካቲት 2004ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2005ዓ.ም. ድረስ የክልሉ ምክትል መስተዳድር እና የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊና የጋምቤላ ሕዝቦች ኅብረት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር፣ ከሚያዚያ ወር 2005ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ ፐሬዚዳንት እና የጋምቤላ ሕዝቦች ኅብረት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር በመሆን ለአገር እና ሕዝብን ሰርቻለሁ፡፡ ስልጣን የህዝብ ነው፡፡ ባለስልጣንም የህዝብ ባለአደራ ነው፡፡ ስለሆነም ህዳር 1 ቀን 2011ዓ.ም. ለስልጣን ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ሥልጣኔን በገዛ ፈቃድ በመልቀቅ ለሕዝብ በክብር አስረክቢያለሁ፡፡ በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እፎይታም ይሰማኛል፡፡

ጥያቄ ፡ ካሩቱሪ፣ ሳውዲ ስታር እና ኢትዮጵያውያን ‹‹ባለሃብቶች›› ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የሰበአዊ መብት ጠበቃ ኦቦንግ ሜቶ ‹‹ጋምቤላ ዘረፋ እንጂ ልማት አልነበረም!›› ይላሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ጋትሉዋክ ፡ ኢትዮጵያውያን የግል ባለሀብቶች፣ በቢሊዮን ብር ካፒታል በክልሉ ውስጥ በእርሻ፣ በግንባታና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የኢንቨስትመነት ፕሮጀክቶች ለክልሉ ነዋሪዎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ይሁንና ቁጥራቸው ከ49 አልዘለሉም፡፡ ይህ አኀዝ አስደሳች አይደለም፡፡ እንዲሁም 27 ባለሃብቶችን በከባድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናቸዋል፡፡

ጋምቤላ በጥጥና የቅባት እህል ምርቶች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች እምቅ ሀብት ይዛለች፡፡ በአሳ ምርት፣ በወርቅ ማውጣት፣ በነዳጃ ፍለጋ፣ የማዕድን ውሀና የግንባታ ሥራ ላይም ለሚሰማሩ ሰፊ የሆነ የኢንቨስትመንት እድል አለ፡፡

ይሁንና 269 ባለሃብቶች መሬት ወስደው፣ ከባንክ በቢሊየን ብር (አላግባብ፤ የብድር መስፈርቱን ያልተከተለ) ብድር ወስደው ምንም ያልሰሩ፤ ያላለሙ፤ ያልሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አገር እና ሕዝብን ረስተው፤ ንቀው ራሳቸውን ለማበልፀግ ፤ ለመመዝበር የተሰለፉ ናቸው፡፡ እነዚህ ጋምቤላን ብቻ ሳይሆን አገር እና ሕዝብን ዘርፈዋል፡፡ ድህነት ካጎበጣት፤ ከድሃ እናታቸው መቀነት ፈተው ከተማ እና ባህር ማዶ ተጉዘው ተሸቀርቅረዋል፡፡ ይህ በጣም ያሳፍራል! አገር እና ሕዝብን አሳዝኗል፡፡

ጥያቄ ፡ በጋምቤላ ተተኪ የሌለው የተፈጥሮ ሃብት በተለይ የጉማሬ ደን ተጨፍጭፏል – ብለው ይከሳሉ

ጋትሉዋክ ፡ የጉማሬ ደን በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ ጉማሬ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ የጉማሬ ደን ከ1,800 እስከ 2,200 ሜትር ከፍታ ላይ ደልዳላ ቦታ ይዞ ከተራራው ወደታች ሲወርድ ቁልቁለታማ ሸለቆዎች በብዛት ያሉበት ነው፡፡

ከዚህ ተራራማና በጥቅጥቅ ተፈጥሯዊ ደን የተሸፈነ ምድር በርካታ ወንዞችና ወንዞችን የሚፈጥሩ ምንጮች ይነሳሉ፡፡ በአጠቃላይ 40 የሚደርሱ ምንጮችና ወንዞች ከአባቢው ይነሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሻይ፣ ጋጃ፣ ካጃዲ፣ ፋኒና ቢታሽ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከአካባቢው የሚነሱ የውኃ ምንጮች በኢትዮጵያ ከሚገኙ 12 ተፋሰሶች አንዱ የሆነው የባሮ አኮቦ ተፋሰስ አካል ናቸው፡፡ የጋምቤላ ክልል እስትንፋስ የሆነው ባሮ አኮቦ ወንዝ የነጭ ዓባይ ትልቅ ገባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ለውኃ አካላቱ መሠረት የሆነው የአካባቢ ተፈጥሯዊ ደን በርካታ አገር በቀል ዛፎችን ያካተተ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቀረሮና ገተማ ዛፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የገተማ ዛፍ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ኢንቨስተሮችና የአካባቢው ንብ አናቢዎች ማር እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

ከማር ምርት በተጨማሪ ተፈጥሯዊው የጉማሬ ደን በርካታ ቅመማ ቅመሞች ይገኝበታል፡፡ ነገር ግን የህንዱ ኩባንያ ቬርዳንታ ሐርቨስትስ ያለ በቂ ጥናት ቦታውን መረከቡ የአካባቢውን ብዝሃ ሕይወት መጉዳቱን መካድ አይቻልም፡፡

ጥያቄ ፡ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በኢትዮጵያ ለብሔረሰብ ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች የማያዳግም የፖሊሲና የአፈጻጸም መፍትሄ ይሰጥ! – ብሎ ጠይቋል፡፡ ጋምቤላ ስሟ ተነስቷል፡፡ በሰበአዊ መብት አያያዝ ላይ ምን አስተያየት አልዎት ?

ጋትሉዋክ ፡ የሰበአዊ መብት አያያዝ እንዲሁም በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ፍትሕ ላይ አልሰራንም፡፡ ብዙ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

የሰበአዊ መብቶች መስፈን ያለበት በሕግ የበላይነት ነው፡፡ ‹‹ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል›› የሚባል አባባል ቢኖርም፣ ኃይል ሲቀላቀል ሕገወጥነት ሊያጋጥም ስለሚችል በተቻለ መጠን ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡ ፍትሕ የማያስገኝ ኃይል ለሰላም ጠንቅ ስለሚሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕግ የበላይነት ክብደት መስጠት አለባቸው፡፡

በጋምቤላ በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩ የሰበአዊ መብቶች እና በደሎች የጋሕዴን አመራር በሕዝብ ፊት ግለ ሂስ አወራርደን በይፋ ይቅርታ ጠይቀናል፡፡ የአገር እና የሕዝብን ይቅርታ አግኝተናል ብለን መቀመጥ አንፈልግም፤ አገር እና ሕዝብን መካስ እንፈልጋለን፡፡

ጥያቄ ፡ በኢትዮጵያ ምድር ፍትሕ እንዲሰፍን ምን መደረግ አለበት?

ጋትሉዋክ ፡ ፍትህ ለተገፉ እንድትቆም ለማድረግ ሌት ተቀን መልፋት፤ መሰራት አለበት፡፡ የማታ ማታ በዳይ የእጁን ማግኘት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ጫንቃ ኢ-ዲሞክራሲያዊነትን፣ ሐሳዊ – ፍትሕን፣ ምዝበራንና ኢ-ሰብአዊነትን ለመሸከም ከእንግዲህ ምንም ቦታ ሊኖረው አይችልም፡፡ የሰው ልጅን ዘቅዝቆ ከመስቀል፣ ለወራት አንጠልጥሎ ከማቆየት እስከ ከፎቅ መወርወር ድረስ ምን አሰየጠነን? ኢትዮጵያ – (ሃይማኖታዊ አገር) ላይ ይህን መሳይ ግፍ ሲፈፀም ልናወግዘው ይገባል፡፡

የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ በብሔርና በእምነት እየተከፋፈሉ ከመወዛገብ ይልቅ፣ በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ለማኅበራዊ ፍትሕና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን እጅ ለእጅ መያያዝ ይበጃል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሥልጣንና ከጥቅም በላይ ምንም የማይታያቸው ራስ ወዳዶችና በስሜት የሚነዱ አገር እየበጠበጡ ነው፡፡ እነዚህ ዕድሜና ጊዜ የማያስተምራቸውን እኩያንና ተላሎች በሕግ አደብ አስገዝቶ፣ ሕዝብን ከጨለማው ወደ ብርሃን ማሸጋገር አገራቸውን የሚወዱ ወገኖች ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ይገባል፡፡ አገር ከሌለ ምንም የለም፡፡

ጥያቄ ፡ በኢትዮጵያ ምድር በሕዝቦቿ ተስፋና ስጋት አይሏል፡፡

ጋትሉዋክ ፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩል ከፍተኛ ተስፋ የሚያሰንቁ በርካታ ጅምሮችን ሲያዩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥጋቶች አሉ፡፡ እነዚህ የተደበላለቁ ስሜቶች ገፊ ምክንያቶች አሉዋቸው፡፡ ተስፋን በሚመለከት ሕዝቡ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት ላለመመለስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ዕርምጃዎችን ከልቡ መደገፉ አንደኛው ነው፡፡

በሕዝብ ላይ ለዘመናት ሲያናጥር የኖረው ድህነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ የሚረዱ አዋጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲነደፉለት የጋለ ፍላጎት ማሳየቱ ሌላው ጠቃሚ ነው፡፡

በተጨማሪም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የምታስተናግድ አገር እንድትኖረውና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በተደጋጋሚ መሻቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ከተቻለ የዘመናት ቁስሎች ሽረው የምታስጎመጅ አገር መፍጠር አይከብድም፡፡

በሌላ በኩል እንደ ሥጋት የሚጠቀሱት ሥርዓተ አልበኝነትን ማበረታታት፣ ልዩነትን በማጦዝ የጋራ ጉዳዮችን ማደፋፋት፣ ከመጠን ባለፈ ራስ ወዳድነትና የሥልጣን ጥም በመስከር ሕዝብና አገርን መናቅ፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ለተወሰነ ጊዜ ቀውስ ቢፈጥሩም፣ በአገር ወዳድና በቅን ዜጎች ከፍተኛ ጥረት አይሳካላቸውም፡፡ አገር ሁሌም የሚጠብቋት ጀግኖች ልጆች ይኖሯታልና፡፡ ስለዚህ ስለመፍረስና መበተን ማውራት ተገቢ አይሆንም፡፡

ጥያቄ ፡ ለጋምቤላ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይመክራሉ?

ጋትሉዋክ ፡ በሀገሪቱ የተፈጠረው ሁለንተናዊ ለውጥ ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሰለማዊ ፖለቲካ የተሻለ አመራጭ በመሆኑ የጋምቤላ ክልል ንቅናቄ አመራሮችና አባላት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ወደ ክልላቸው ገብተዋል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ጋህነን እና ጋምቤላ ክልል ንቅናቄ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሆን የሕግ የበላይነትና የዜጎች ሰብዓዊ መብት የተከበረበት ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ።

የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚቀረፉትና ሕዝብ ነፃነቱን የሚያጣጥምበት ሥርዓት መገንባት የሚቻለው፣ የሰላማዊ ፖለቲካ የጨዋታ ሕግ ሲከበርና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል ጥብቅ ዲሲፕሊን ሲኖር ነው፡፡

በአንድ በኩል ሥልጣናችንና ጥቅማችን ለምን ተነካብን የሚሉ ወገኖች፣ በሌላ በኩል መያዣና መጨበጫ የሌለው አቋም ይዘው ትርምስ የሚፈጥሩ ኃይሎች እርስ በርስ እየተመጋገቡ የአገር ተስፋን ለማጨለም እየጣሩ ነው፡፡ የአገር ተስፋ መጨለም ስለሌለበት እነዚህ ከታሪክ የማይማሩ ለሕዝብና ለአገር ደንታ የሌላቸው ኃይሎች በተባበረ ጥረት በሕግ አደብ እንዲገዙ መደረግ አለበት፡፡

ወቅቱ የሐሳብ ልዕልና ያላቸው የሚፎካከሩበት እንጂ ‹እርስዎም ይሞክሩት› እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሰንቆ ተነስቷል፡፡ ይህ ተስፋ ደግሞ በማንም እንዳይጨናገፍ ይፈልጋል፡፡ የአገር ተስፋ በእኩያን አይጨናገፍም እያለ ነው!

በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች በሙሉ ከእነ ልዩነቶቻቸውም ቢሆን በጋራ ለመሥራት መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡

‹መጀመርያ የመቀመጫዬን› እንዳለችው እንስሳ፣ የአገርን ጉዳይ ከምንም ነገር በፊት ማስቀደም ይገባል፡፡ በተለይ በሕዝብ መስዋዕትነት በተገኘው ለውጥ ምክንያት፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ጥያቄ ፡ የጠቅላይ ምንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሀመድ ጉብኝት እና የሕዝቡ አቀባበል እንዴት ነበር?

ጋትሉዋክ ፡ ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደምቢ ዶሎ ከተማ ቆይታቸውን አጠናቀው ከሰዓት በኋላ ጋምቤላ ኤርፖርት የደረሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋምቤላ ከተማ ሲገቡም ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ‹‹እንኳን ወደ በረሃዋ ገነት፤ ጋምቤላ ምድር በሰላም መጡ!›› ብልን ሁለት እጆቻችንን ዘርግተን በክብር አቀባበል አድርገንላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋምቤላ ክልል ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ ስታዲየም በመገኘት ለከተማዋ እና ለክልሉ ህዝብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሕዝቡም አዲሱ መሪውን በአዎንታዊ እንደተቀበላቸው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር እንደተሰለፈ ፊት ለፊት አረጋግጦላቸዋል፡፡

ጥያቄ ፡ከጠቅላይ ምንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ለይፋዊ ጉብኝት ኬንያ አምርተዋል ልበል?

ጋትሉዋክ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት ሀገራት ጂቡቲ እና ሱዳን ስኬታማ ጉብኝቶችን አድርገው ተመልሰው ነበር። ልጆቻችንን ከእስር መማቀቅ ሕይወት አውጥተዋቸዋል፡፡ ይህ በሰውም፤ በፈጣሪም ዘንድ ክብር የሚያሰጣቸው ታላቅ ተግባር ነው፡፡

ነሐሴ 24 ቀን 2010ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት እኔን ጋብዘውኝ ከእርሳቸው ጋር ሄጃለሁ፡፡

ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ምሥራቅ አፍሪካን ከእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭቶች አላቀን ሰላማዊ ደሴት መስረተን ጠንካራ ኢኮኖሚ እንመስርት ሲሉ አህጉራዊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ምሥራቅ አፍሪካን በተለይ ሞያሌን እንደ ዱባይ – የንግድ ማዕከል እናድርጋት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና በሙሉ በጎ አመለካከት አላቸው፡፡ በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋትን በማምጣት እየሰራ ላለ የኢትዮጵያ መንግስት ኬንያ ከጎኑ ትቆማለች። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ደስተኞች ነን ፡፡ ከኤርትራ ጋር በተደረሰው ስምምነትም ተደስቻለሁ›› ብለዋል።

ጥያቄ ፡ የእርስዎ የስልጣን መንበር ተተኪዎች፤ ለአዲሶቹ የጋምቤላ ፕሬዚዳንትና ምክትሉ መልዕክትዎ ምንድነው?

ጋትሉዋክ ፡ የተከበሩ አቶ ኡሞድ ኡጅሉ ኡቡፕ እና የተከበሩ አቶ ቴኩዌይ ጆክ ሮም የአሁኑ አመራር የጋሕዴን ፤ (የጋምቤላ ሕዝቦች ደሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ታጋዮች ናቸው፡፡ ሕዝቡም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሊደግፏቸው፤ ሊያግዘቸው ይገባል፡፡

በተለይ በተለይ ጠባብ ብሔርተኝነት፣ ጎሰኝነት፣ ቡድንተኝነት፣ የእርስ በእርስ የስልጣን ሹኩቻ – መጠላለፍን ሕዝብ እና ክልላዊ መንግስት በጋራ ሊመክቱት ይገባል፡፡ ክልሉ ወደፊት እንዳይራመድ አስሯት ይገኛል፡፡ ይህንን የእድገት ማነቆ ሰንሰለት በጣጥሶ መጣል ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ ፡ ጋምቤላ 400 ልጆቿን ያጣችበትን ቀን እየዘከረች ነው?

ጋትሉዋክ ፡ ብሔር ተኮር በሆነ ጥቃት ከ400 በላይ ንጹሃን የአኝዋክ የሞቱበትና ከ7 ሺህ በላይ የተፈናቅሉበት የጋምቤላ እልቂት 15 ዓመት ሞልቶታል ፡፡

በአኝዋክና በደገኛ መከካል የተነሳን ግጭት መነሻ ያደረገው የወቅቱ ዕልቂት በርካቶችን ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲፈልሱም ምክንያት ሁኗል ፡፡

ይህ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ዓለም ያዘነበት ድርጊት ነበር፡፡

አሁን ብሔረሰቦቹ ባህላዊ እርቅ ፈጽመው ይህ ድርጊት አይፈፀምም – ‹‹አይደገምም!›› ብለው ተማምለው፤ ተከባበብረው እየኖሩ ናቸው፡፡ ይቅር ባይነት ለዘላለም ይኑር! … ይህ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡

በ2005 ከፌደረል መንግስት ጋር በመሆን ተሰደው የነበሩ ዜጎቻችንን በሁለት ዙር ከደቡብ ሱዳን ተመልሰዋል፡፡

ጥያቄ ፡ እርስዎ ለአገር እና ለሕዝብ ምን ይመክራሉ ?…

ጋትሉዋክ ፡ ሰላም – ሰዎች ከፍርኃት፣ ከጥላቻ፣ ከግጭትና ከውድመት ተጠብቀው በነፃነት የሚኖሩበት ድባብ መገለጫ ጽንሰ ሐሳብ ከመሆኑም በላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ደግሞ አገርን ለማሳደግ የሚረዳ መሣሪያ ነው፡፡

‹‹በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች አሉባልታ ይፈጥራሉ፣ ሞኞች ደግሞ እየተቀባበሉ ያሠራጫሉ፣ ነፈዞች ደግሞ አሉባልታውን የራሳቸው ያደርጉታል፤›› ይባላል፡፡ በዚህ ዘመን በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች የሕዝብ ደም የሚያፈሱት በማር የተለወሰ የአሉባልታ መርዝ በመንዛት ነው፡፡ ይህንን መርዝ የሚያስተጋቡ ደግሞ ሳያውቁ መሣሪያ እየሆኑ ነው፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ከስሜታዊነት ይልቅ፣ ለምክንያታዊነት ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደዋዛ ያመለጠ መልካም አጋጣሚ ተመልሶ የመገኘቱ ዕድል እጅግ በጣም የመነመነ በመሆኑ፣ የአገር የጋራ ጉዳይን በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ ኃላፊነት መወጣት ይገባል፡፡

ምሁራንና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ደግሞ በተቻለ መጠን ስለሰላም ቢያስተምሩና ራሳቸውም ከአላስፈላጊ ድርጊቶች ቢታቀቡ መልካም ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማራገብ ቢቆጠቡ ይመከራሉ፡፡

ሥልጣንን ከሕዝብ ድምፅ ሳይሆን በአቋራጭ ለማግኘት ያስፈሰፉ ኃይሎችም ከማያዋጣው ድርጊታቸው ተቆጥበው፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካ ቢያራምዱ ይሻላቸዋል፡፡ በተለይ ሕዝብ መስዋዕትነት ከፍሎ ለዚህ እንዳበቃቸው እያወቁ የሚታበዩ ከታሪክ ቢማሩ ጥሩ ነው፡፡

ትዕቢት ለውርደት እንጂ ለክብር ቅርብ አይደለም፡፡ ሰላም ሳይኖር ዓላማውን ማሳካት የሚችል የለምና ሰላም ከቃል በላይ ተግባር እንደሚሻ መተማመን ያስፈልጋል!

ሥልጣን የሚገኘው ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን የሚገነዘብ ማንኛውም ጤነኛ ሰው፣ በሕዝብና በአገር ላይ የሚቆምሩ ቁማርተኞችን በይሉኝታ ማለፍ የለበትም፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ አገር በማንም ፈቃድ ተሠርታ የምትፈርስ የእጅ ሥራ አይደለችም፡፡

ጥያቄ ፡ ፈጣሪ ጨርሶ ምህረቱን ይላክልዎ፡፡
ጋትሉዋክ ፡ አሜን! አሜን – እናንተንም አመሰግናለሁ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply