“አጣርተን ነው የምናስረው” ገደል ገብቶ የጅምላ እስርና መንግስታዊ ሽብር (በግርማ ካሳ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ብዙ ጊዜ “በዶ/ር አብይ ላይ እመነት አለኝ” ብዬ ጽፊያለሁ። ዶ/ር አብይም ያሻግረናል ፣ በርሱ አመራር ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተደረጎ አገር በዘላቂነት ትረጋጋለች ባይ ነበርኩ። አንዱ ዶ/ር አብይን ያስቸገሩት የሚመራው ድርጅት ውስጥና ከድርጅቱ ውጭ ያሉ የኦሮሞ ጽንፈኞች ናቸው የሚል እምነት ነበረኝ። ከዚህም የተነሳ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሌሎች ኦህዴዶች እንጂ ዶ/ር አብይ አይደለም በሚል የተለያዩ ምክንያቶች እስጥ ነበር። ዶ/ር አብይ ለምን ይሄን አደረገ ሳይሆን ለምን ይሄን የሚያደረጉት አንድ ነገር አያደርጋቸው የሚል አይነት ትችት ነበር የማቀርበው።

አሁን ግን አንድ ነገር ተረዳሁ። ሰኔ 15 በአዲስ አበባና በባህር ዳር በተፈጠሩት ግዳይ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎች የሉኝም፤ በገለልተኛ አካል እስኪታይ ብዙ መጻፍ አይመቸኝም። ሆኖም ግን “ሳናጣራ አናስርም” የሚለውን ቃል በማፍረስ፣ ልክ እነ ጌታቸው አሰፋ ያደረጉ እንደነበረው ፣ የዶ/ር አብይ አገዛዝ ዜጎችን በጅምላ ማሰሩ፣ (ያዉም ደግሞ በሽብርተኛ ክስ) ለአንድ አመት ሲነገረን የነበረው ሁሉ ድራማና ፉገራ እንደነበረ እየተሰማኝ ነው።

አሁንም እመክራለሁ፣ አስጠነቅቃለሁ። ዶር አብይና ድርጅታቸው ኦህዴድ፣ እየገደሉ፣ እያሰሩ እንቀጥላለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል። በአስቸኳይ ያሰሯቸውን በሙሉ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መልቀቅ አለባቸው። በማሰር፣ በማስፈራራት፣ በሃይል የሚሆን ነገር የለም። ምን አልባት “ዘመኑ የኛ ነው፣ ምን ያመጣሉ? ” በሚል ጥጋብና ዘረኝነት ተሞልተው ከሆነ፣ ከህወሃት እንዲማሩ እጠይቃቸዋከሁ።

በአዲስ አበባ የታሰሩ ወገኖች ናቸው ብዙዎቹ፣ የባላደራው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ስንታየሁ ቸኮል ጨምሮ፣ የባላደራው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ወገኖች ናቸው። ከባላደራው ውጭም የበረራ ጋዜጠኞችና ሌሎች እንደ ታጋይ አማኑኤል መንግስቱ ያሉም ታስረዋል።

በነገራችን ላይ እንደ ኢሳት ያሉ “ነጻ ሜዲያ” የሚባሉት፣ እንደ ኢዜማ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉ ፣ የኦዴፓ/ኦህዴድ አገዛዝ በጅምላ ዜጎችን ሲያስርና ህዝብን ሲያሸብር ዝም ማለታቸው በጣምና በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply