አጤ ሚኒሊክንና እቴጌ ጣይቱን ለመጥራት የፈራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአድዋ በአል መግለጫ (ያሬድ ጥበቡ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የዶክተር አቢይ የአድዋ ድል መልእክት ረጅምና ብዙ ቁምነገሮችን ያዘለና ትምህርታዊ ነው። ሆኖም በነዚህ አራት ገፆች በወሰደ መልእክት ውስጥ ተሳስቶም አንዴም እንኳ ምንሊክንና ጣይቱን በስማቸው ማንሳት አልደፈረም። ያለምንሊክና ጣይቱ አመራር አድዋ ምንም ነው። በእኔ ግምት ዶክተር አቢይ ምንሊክን በስሙ አንስቶ ማመስገን ጠልቶ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ያልተቀበለውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፈርቶ ነው። ግን እስከመቼ? እስከመቼ የኦሮሞን ብሄርተኝነት እሹሩሩ ብለህ ትችለዋለህ?

ዶር አቢይ ስለኦሮሞ ብሄርተኝነት ማወቅ ያለበት ነገር፣ ሁለት ስለት ያለው ካራ መሆኑን ነው። በአንዱ ስለት ኢትዮጵያን የሚገዘግዘውን ያህል፣ በሌላ ስለቱ መንግስትንም የሚገዘግዝ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ዛሬ የምንሊክን ስም መጥራት ከፈራህ ነገ ደግሞ “አድዋ የትግሬዎች እዳ ነው አንተን ምን አገባህ” ይመጣል ። ውሎ ሲያድር ደግሞ “የነፍጠኞች ንጉስ ሃውልት ከፊንፊኔ መነሳት አለበት” ይሉሃል። ዛሬ ላይ በመተክል ላይ ቆመህ ካላስቆምካቸው፣ እኔ የበለጥኩ ኦሮሞ ነኝ በሚለው የቁንጅና ውድድር አትችላቸውም። ያ ውድድር ሁሌም እጅግ ያከረረው ብቻ የሚያሸንፍበት ውድድር ነው። ዘረኝነትን ተፀየፈው፣ አትንበርከክለት።

ጀምረኸው የነበረውን ኢትዮጵያዊነት የሙጥኝ ብለህ፣ እንዳሰብከው ኢህአዴግን አንድወጥ ፓርቲ አድርገህ፣ ምርጫው ፕሬዚዳንታዊ እንዲሆን ህገመንግስታዊ ማስተካከያ አስደርገህ፣ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ መሪ ሁን። በዚህ አካሄድ የኦሮሚያ ክልልን 1/3ኛ ድጋፍ እንኳ ብታገኝ ማሸነፍ ትችላለህ። ይህን ለማድረግ አመንትተህ ፣ ሰሞኑን ሲደረግ እንደከረመው ግን አንተ በተሰየምክበት ጉባኤ አዲስአበባን በኦሮሞ ተፈናቃዮች ለመክበብ ሲዘከር ዝም እያልክ፣ በአድዋ 123ኛ የድል በአል መልእክትህ ላይ የምንሊክንና ጣይቱን ስም አንስተህ ለማመስገን እየፈራህ የዘር ፖለቲካን መቋቋም አትችልም። ተወዳድረህም አታሸንፋቸውም።

ደረስኩባቸው ስትል መመዘኛውን ከፍ ያደርጉብሃል። ነገ፣ ግማሽ አማራነትህ ጥያቄ ይሆናል። ኢትዮጵያዊ ስሜትህ ወንጀል ይሆናል። ኦህዴድ/ኢህአዴግ ውስጥ የነበረህ ስልጣንና የተሰራ ስህተት መክሰሻ ይሆናል። ስለሆነም በማታሸንፍበት የቁንጅና ውድድር ውስጥ አትግባ ። ያንን ለነዳውድና ጃዋር ተወው፣ አይመጥንህም፣ ደግሞም ያጠፋሃል! ከዓመት በፊት ልባችንን ያማለልክባትን ኢትዪጵያን ይዘህ ግን መንገድህ ቀና ነው፣ አታመንታ! ፈጣሪ ቀናውን ያሳይህ!

Share.

About Author

Leave A Reply