አጭር ቆይታ ከዶ/ር አዲስአለም ባሌማ ጋር

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(ሲሳይ መንግስቴ)

አላማጣ ከተማ ውስጥ የተገነባውን ራያ ግራንድ ሪዞርት ሆቴል ለማስመረቅ ባለፈው ሳምንት ወደ ራያ ጎራ ብየ ነበር፡፡ ቅዳሜ ሚያዚያ 6/2010 ዓ.ም ከቀኑ 5፡30 ላይ የሪዞርት ሆቴሉ በይፋ ሲመረቅ የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የትግራይ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ ነበሩ፡፡

በእርግጥ በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ ሌሎች የክልል ባለስልጣናትና የሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን አመራሮችም በተጋባዥነት ተገኝተዋል፣ በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የሆቴሉ ባለቤት የተሳታፊውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በአማርኛ ንግግር ቢያደርጉም የከተማው ከንቲባና የክብር እንግዳው ግን በትግርኛ ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡

የኋላ ኋለ የምረቃ ስነስርአቱ ተጠናቆ ምሳ ከበላን በኋላ ለትንሽ ጊዜ ያህልም ቢሆን ዶ/ር አዲስ አለምና የትግራይ ክልል አመራር በራያ ህዝብ ጥያቄ ዙሪያ ያላቸውን እይታ ለማወቅ ስለፈለግሁ ላናግራቸው በማሰብ ራሴን አስተዋውቄ ከጎናቸው ተቀመጥሁ፡፡ እሳቸውም በአካል ባላውቅህም ስምህ አዲስ አልሆነብኝም በማለት ወሬያችንን አንድ ብለን ጀመርን፡፡

ጊዜ ሳላጠፋም ለመሆኑ የራያን ህዝብ ጥያቄና ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ነው የምትመለከቱት ስል በቀጥታ ወደ ገደለው ገባሁ፡፡ ትንሽ ቆፍጠን በማለት ጭምር ምን ማለት ነው ይኸ ሲሉ ጥያቄየን በጥያቄ መለሱልኝ፡፡ እኔም ጥያቄውን ፈታ አድርጌ ለማቅረብ ያህል ባለፉት 26 አመታት የራያ ህዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ አይደለም፣ ልጆቹም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አይማሩም፣ የልማት ተጠቃሚም አይደለም ወዘተ ብየ ሳልጨረስ ይኸ ጥያቄ የአንተና የመሰሎችህ ነው ወይስ የራ ህዝብ በማለት አሁንም ከሀይል ቃል ጋር መልሰው አፈጠጡብኝ፡፡

ይህን ጊዜ የእኔም ትግስት አለቀና እናንተ ሰዎች ዋነኛ ችግራችሁ ይኸው ይመስለኛል፣ መጀመሪያ እያልሁ ያለሁትን በአግባቡ አዳምጡ ከዛም ትክክለኛውን ነገር ለመረዳት ሞክሩ፣ ሌላው ነገር ከዛ በኋላ ይደርሳል ስል እኔ በተራየ በስጨት ብየ ተናገርሁ፡፡ ከዛም ብስጭታቸውን መደበቅ ስላልቻሉ አንተ ሰው ዝም በል እንዴት እንደዚህ ትላለህ በማለት የፖለቲካ ስልጣናቸውን በመጠቀም ጭምር ጸጥ ለማሰኘት ትንሽ ፈንጠር በማለት ተቀምጠው በንቃት የሚከታተሉንን አጃቢዎች በአይናቸው መቃኘት ጀመሩ፡፡

የአባ ቢላዋ ልጅ እንደሚባለው እኔም የእሳቸው ቁጣ ብዙም የሚያስጨንቀኝ ስላልነበር ይልቅስ የሚሻለው መሬት ላይ ያለውን እውነት በጸጋ ተቀብሎ በስርአቱ ለማስተናገድ መሞከር ነው በማለት ቀደም ሲል ያነሳሁትን ጥያቄ በአስተያየት መልክ አጠናክሬ አቀረብሁት፡፡

ይኸኔ የአይጥ ምስክሯ ድንቢት ሆነና ነገሩ እኔ ተወልጄ ያደግሁበት፣ ኋላም ላይ ለተወሰ ጊዜ ያህል የሰራሁበት፣ በመጨረሻም ከጓደኛየ አለሙ ካሳ ጋር በመሆን ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር አድርገን መጽሀፍ ጭምር የጻፍሁበት ሰው እውነታውን በግልጽ እየነገርኋቸው ሁለት አመት እንኳ በአካባቢው ያልቆየውንና ከፊት ለፊታቸው ተቀምጦ የነበረውን የደቡባዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ ይኸ ሰውየ የሚለው ነገር እውነት ነው እንዴ ሲሉ ጥያቄ አይሉት ማስፈራሪያ አቀረቡለት፡፡

እሱም አይኔን ግንባር ያደርገው ብሎ የዚህ አይነት ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም፣ በራያ ውስጥም ሲሳይ እንደሚለው አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪ ህዝብ የለም፣ ምናልባት አንዳንድ ጎጦች ውስጥ የተወሰኑ አማርኛ ተናጋሪዎች ሊገኙ ካልሆነ በስተቀር ሲል የተለመደ የክህደት ምላሹን ሰጠ፡፡

እኔም በማስከተል አይ ሌላው ቀርቶ አላማጣ ከተማ ውስጥ እኮ በአማርኛ የሚያስተምር ት/ቤት እንዲከፈትላቸው ነዋሪዎቹ ሰሚ አላገኙም እንጂ በስብሰባ ላይ ጭምር ጥያቄ እቅርበው ነበር ብየ ምሳሌ ሳነሳለት፣ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ይኼ ጥያቄ እዛ አዲስ አበባ የምትኖሩ ሰዎች ጥያቄ ነው እንጂ የአላማጣ ህዝብ ጥያቄ አይደለም በማለት እውቅና የመንፈግ አካሄዳቸውን አረጋገጠ፡፡

በመጨረሻም ዶ/ሩ በስልክ አሳበው ከእኔ ተለዩና የዞኑን አስተዳዳሪ ጠርተው ረዥም ወሬ ስለጀመሩ እኔም ትቻቸው ወደ ስፍራየ ተመልስሁ እላችኋለሁ፡፡ እናም የትግራይ ክልል አመራር ራይኛ ተናጋሪውን የህብረተሰብ ክፍል እንደ ትግሬ ቢቆጥረው እንኳ ራያ ውስጥ ቢያንስ በመቶ ሽዎች የሚቆጠር አማራ፣ በአስር ሽዎች የሚቆጠር ኦሮሞ፣ አፋርና አገው እንዳለ እውቅና መስጠት አይፈልግም፣ በተቃራኒው ሶስት ሽህ ለማይሞሉ ኩናማዎች በክልሉ ህገ-መንግስት ሳይቀር እውቅና ሰጥቶ ቋንቋቸውና ባህላቸው እንዳይጠፋ መስራት ጀምሯል፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply