አጼ ምንይልክ ተስፋፊ ወይስ ሰብሳቢ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አጼ ምንይልክ መባል ያለባቸው ሰብሳቢ እንጂ ተስፋፊ አይደለም። ምክንያቱም ተበትኖ የነበረውን ሀገር ሰበሰቡ እንጂ ለኢትዮጵያ አዲስ መሬት አላስገኙም። አብራራዋለሁ።

በጥንት ዘመን የኖሩ የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥታት እና ንግሥተነገሥታት ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ከዳር እስከዳር የማስተዳደር ፍጹም ስልጣን ነበራቸው።

ምንይልክ ከመወለዳቸው ከመቶ ዐመታት በፊት ኢትዮጵያ፣ አጼ ኢዮአስ በተባሉ ንጉሠነገሥት ትመራ ነበር። እሳቸው ከሞቱ በሁዋላ መጀመሪያ የትግራዩ ስሁል ሚካኤል፣ ቀጥሎ የ የጁ ኦሮሞ የነበሩት የሴሩ ጉዋንጉል ተወላጆች ከትልቁ ራስ አሊ እስከ ትንሹ ራስ ኡሊ በ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነት ጎንደር ላይ ሆነው ከፊል ኢትዮጵያን ለ60 ዐመት ያህል ገዙ። አቅም የሌላቸውን የሰለሞን ዘር ነን የሚሉትን የይስሙላ ንጉሠነገሥት አድርገው ዙፋን ላይ እያስቀመጡ።

አጼ እዮአስ ከሞተ በሁዋላ “ተፍጻሜ መንግሥት” ተባለ። የንጉሠነገስት ስልጣን መፈጸሙን ለመጠቆም ነው። በእዚህ አኩዋሀን ዘመነ መሳፍንት ተስፋፍቶ፣ ሁሉም መሳፍንት፣ ወህኒ አምባ ከተባለ ልዑላን እንንገሥ እያሉ አገር እንዳያተራምሱ ከሚታሰሩበት ስፍራ አንዳንድ ልዑል እየፈቱ ያለስልጣን እየጎለቱ ራሳቸው ለመፍለጥ ለመቁረጥ ይጣጣሩ ጀመር። ከእዚህ የተነሳ መሳፍንቱ እርስበርሳቸው እየተፋጁ ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ ከተዋት በትነዋት ነበር።

የተበተነችውን ሀገር አጼ ቴዎድሮስ ተነስተው ሀገር ከፋፋይዎቹን መሳፍንት ድል ነስተው የጥንቱን የንጉሠነገሥቱን ስልጣን በተወሰነ ደረጃ እጃቸው አግብተው ኢትዮጵያን እንደድሮው አንድ ለማድረግ ጣሩ። ከሳቸው ቀጥለው የላስታና የዋግ ገዢ የነበሩት ንጉሥ ጎበዜ ተክለጊዮርጊስ ተብለው ንጉሠነገሥት ሆነው አጼ ቴዎድሮስ የሰበሰቡትን ይዘው ያልተሰበሰበውን ራሳቸው መሰብሰብ ጀመሩ።

ከሳቸው ቀጥሎ የትግራዩ አጼ ዮሀንስ ሀገር በመሰብሰቡ ጉዳይ ከመሰማራታቸው በተጨማሪ ድንበር ሲያስከብሩ ህይወታቸው አለፈች። ከሳቸው ህልፈት በሁዋላ አጼ ምንይልክ ያልተሰበሰበ ሀገርን ከመሰብሰብ አልፈው ወራሪ ጣልያኖችን በመውጋት ትልቅ ተጋድሎ አደረጉ።

ስለ እዚህ አጼ ምንይልክ እንደ አጼዎቹ ቴዎድሮስ፣ ተክለጊዮርጊስ እና ዮሀንስ የተበተነ ግዛቶችን ሰብሳቢ ነበሩ እንጂ ተስፋፊ አልነበሩም። ተስፋፊ ማለት የባእዳን አዲስ ግዛትን የሚይዝ እንጂ ቀድሞ የነበረውን የራሱን የሚያስመልስ ወይም የሚሰበስብ አይደለምና። እንግዲህ ምንይልክ ሰብሳቢ እንጂ ተስፋፊ መባል የለባቸውም። ስለ እዚህ፣ ቃልን በአግባቡ እንጠቀምበት።

የጥንቶቹ የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥታት እና ንግሥተነገሥታት ግዛታቸው ከ ኢትዮጵያ የሚዘል ቢሆንም ምንይልክ የሰበሰቡት እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን ነው። ኤርትራን ሳንጨምር። ኤርትራ እንዴት ከኢትዮጵያ እጅ እንደወጣች ሌላ ታሪክ ስለሆነ በሌላ ቦታና ጊዜ የሚነገር ነው።

ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ

Share.

About Author

Leave A Reply