ኢህአዴግ እና የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ የቁልቁለት ጉዞ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ፕሬስ የሚለው ቃል በአብዛኛው የህትመት መገናኛ ብዙሃንን ለመወከል ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም በኤሌክትሮኒክስ፣ በዲጂታልም ይሁን በህትመት መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች የወል ስም ሆኖ ሲያገለግል ግን ዘመናት ተቆጥረዋል። በዚህም ምክንያት ይመስላል “ፕሬስ” ሲባል ሁሉንም የመገናኛ ብዙሃን (Media) የሚወክል ቃል መሆኑ ተለምዷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክ ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃገርነትና ቀደምት ስልጣኔ አንጻር ሲታይ ጭብጥ የማይሞላ፣ ኢንዱስትሪውም እንደሌላው ዘርፍ ከማደግ ይልቅ በጊዜ ሂደት እየቆረቆዘ ሄዶ በማህበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ተዋስዖ ውስጥ የተጫወተው ሚና የጫጨ ቢሆንም፤ እንደአቅሙ ግን እየወጣና እየወረደም ቢሆን አራት መንግስታትን ተሻግሯል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ከዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመነ ኢህአዴግ ድረስ በመንግስታዊ ጭቆና ውስጥ የወደቀና በንስር ዓይን ሥር የኖረ ኢንዱስትሪ ነው። በኢትዮጵያ ከአወዳሽ ሚዲያው ውጭ ያለው ፕሬስ እንዳይወቅስ እና እንዳይከስስ፣ ህዝብን እንዳያነቃና ለመብት ጥያቄ እንዳያነሳሳ ፣ መረጃ እንዳያሰራጭና ለውጥ እንዳይፈጥር መንገዱን የእሾህ ጋሬጣ ሲያበጁበት በኖሩት ገዢ መንግስታት ሳቢያ ከዳዴ ጉዞ ፈቅ ሳይል አንድ ክፍለ ዘመን አብቷል።

በተለይም የኢህአዴግ መንግስት በሃገሪቱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ህገ-መንግስታዊ በሆነበት ማግስት ሊያብብ የጀመረውን ፕሬስ በክፉ ዱላ ከመታውና ጋዜጠኞችን ማዋከብ የህልውና ጥያቄ አድርጎ ከተነሳ ወዲህ፤ ዛሬ ይህ የፕሬስ በተለይም የነጻው ፕሬስ ዘርፍ “የደፈረ ብቻ” የሚገባበት “ቀይ ዞን” እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። በ 108 ዓመት 11 ጋዜጣ በዓፄ ምንሊክ ዘመን በ1902 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው “አዕምሮ” የአማርኛ ጋዜጣ መታተም ሲጀምር የኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክም አሃዱ አለ ። ኢትዮጵያዊ አንባቢ “ከአዕምሮ” ቀጥሎ በሃገሩ ሁለተኛ ጋዜጣ ለማየት 39 ዓመታት መጠበቅ ነበረበት።

“አዲስ ዘመን” በመንግስት የሚታተም ሁለተኛ ጋዜጣ ሆኖ ለአንባቢ የደረሰው በ1941 ዓ.ም ነው። የዓፄ ኃይለ ሥላሴንና የደርግን ዘመን ተሻግረው አሁን የኢህአዴግ ዘመን ድረስ የዘለቁትን እነአዲስ ዘመንን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጦችን ጨምሮ በ1902ዓ.ም. አሃዱ ተብሎ የተጀመረው ጋዜጣ በ2010 ዓ.ም (ከ108 ዓመት በኋላ ማለት ነው) መድረስ የቻለበት የብዛት ጣሪያ 11 ብቻ ነው። ከህትመት ዘርፉ ጋዜጣን እንደምሳሌ ካየን፤ እንግዲህ ይህ አሃዝ የሚያመለክተን በኢትዮጵያ በአማካይ በየ10 አመቱ አንድ ጋዜጣ ብቻ የህትመት ኢንደስትሪውን እንደተቀላቀለ ነው። ፕሬስ በዘመነ ኢህአዴግ ኢህአዴግ በግንቦት 1983 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ሲመጣ ካደረጋቸው መልካም ነገሮች አንዱ በሐምሌ ወር የሽግግር ቻርተር በማውጣት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ቢያንስ በህግ ደረጃ ማስፈሩ ነው። ይህንን ተከትሎ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ህግ በመነሳቱ የነጻ ፕሬስ መንፈስ እንዲቀሰቀስና ኢንደስትሪውም ብዛት ያላቸው ተዋናዮችን እንዲያሳትፍ መሰረት ጥሏል።

ወደ ገበያው ብቅ ያሉ እንደ ጋዜጣና መጽሄት ያሉት የፕሬስ ውጤቶች ምንም እንኳን በአብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ በባለሙያ የሚሰሩ ባይሆኑም፤ ለአንባቢው ግን በምርጫ ቀርበውለት ነበር። 1985 ዓ.ም የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/85 ሲደነገግ “ወርቃማ ዘመን” ተብሎ የሚጠራው የፕሬስ አብዮት በኢትየጵያ ፈነዳ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ወርቃማ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ቀደሞም ያልነበረ ኋላም ያልተደገመ የህትመት ውጤቶች ቁጥር የተመዘገበው በ1985 እና 86 ዓ.ም ነበር።

በ1985 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ 28 ጋዜጣና 65 መጽሄቶች የነበሩ ሲሆን፤ በ1986 ዓ.ም ደግሞ ይህ ቁጥር አሻቅቦ 79 ጋዜጣና 38 መጽሄቶች በድምሩ 117 የህትመት ውጤቶች ገበያውን አጥለቀለቁ። በጊዜው የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ የገነነበት፣ ህዝቡ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንግዜውም በላይ ያገባኛል ያለበት ወቅት ስለነበር፤ አዲስ ከነበረው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ጋር ተዳምሮ ዛሬ ላይ መልሶ የሚደገም የማይመስል ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተንሰራፋ። ይህን ተገን ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሬስ በተለይም የግሉ ፕሬስ በመንግስት አሰራሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበረ ኢኮኖሚ ተሳትፎውም የጎላ ድርሻ መያዝ ጀመረ። አሳታሚዎች በተለያየ አቀራረብ ይዘዋቸው ብቅ ከሚሉት የፕሬስ ውጤቶች ከሲሦ በላይ የሆኑት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ነበሩ። ጊዜው የጋዜጦች ብቻ ሳይሆን የመጽሄቶች አብዮትም የፈነዳበት ነበር።

በፍቅርና ጾታዊ ግንኙነቶች፤ እንዲሁም በፋሽን ጉዳይ ላይ በሚያተኩሩ መጽሄቶች ተጣቦ የነበረው ገበያ ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ ይዘት ወዳላቸው መጽሄቶች በመምጣቱ የሚቀርቡት መረጃዎች ለአንባቢውም የመወያያ አጀንዳ በመፍጠር ሃገራዊ ጉዳዮች ወደ ህዝባዊ የፖለቲካ ተዋስዖ መድረኮች እንዲመጡ እስከማድረግ የደረሰ አቅም ፈጥረዋል። በአንጻሩ በብዛት እና በስፋት የፖለቲካው ጉዳይ ላይ አትኩረው ይሰሩ የነበሩ የግል ፕሬሶች ማበብ በተቃራኒው የመንግስት የፕሬስ ውጤቶች የፕሮፓጋንዳ ማሽን ይዘት ያላቸው ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓል። ይህ በመጥፎ ጎኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ በሁለት ጽንፍ ተደራጅቶ ግንብ እንዲያበጅ ምክንያት ሆኗል። በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ነጻው ፕሬስ ኢ- ተዓማኒና በስሜት የሚነዳ፤ እንዲሁም በተዛባ መረጃ የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰራ ተደርጎ መወቀሱ፤ በነጻው ፕሬስም በኩል በመንግስት ይዞታ ሰር የሚገኙ የፕሬስ ውጤቶች ከፕሮፓጋንዳ ስራ እና ከውሸት ሪፖርቶች የዘለለ የህዝቡን ድምጽ የመስማት አቅም የሌላቸው ተደርገው መወሰዳቸው፤ በኢትዮጵያ የግልና የመንግስት ፕሬስ የሚባሉ ሁለት ፕሬሶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። “አወዳሽ” እና “ከሳሽ” ፕሬስ ጄኒፈር ፓርሜሌ የተባለች በ1990ዎቹ እ.ኤ.አ መጨረሻ አካባቢ ቪኦኤ የምስራቅ አፍሪካ ተጠሪ የነበረች ጋዜጠኛ “የኢትዮጵያ ፕሬስ ሁለት ጽንፍ፤ አንዱ አይኑን ጨፍኖ የሚያወድስ፤ አንዱም አይኑን ገልጦ የሚከስስ ተቋም አድርጎታል፣ ይህንን በሁለት ግንብ የተከፈለ “የመንግስት” እና “የግል ፕሬስ” ወደ አንድ የማምጣት ስራ ጊዜ ሊፈጅ ቢችልም የግድ መሆን ያለበት ነገር ነው ” ብላ ነበር። በርግጥም በሃገሪቱ እዚህም እዚያም የሚታዩ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርም ይሁን የሙስና እንዲሁም የፖሊሲ ችግሮችን አይቶ እንዳላየ በማለፍ ኗሪው ህዝብ ከሚያውቃት ኢትዮጵያ ውጪ የሆነች ኢትዮጵያን ለመሳል የሚለፋ የመንግስት ፕሬስ ባለበት ሃገር የግሉ ፕሬስ በልማት ጋዜጠኝነት ስም ተመሳሳይ ተግባር ውስጥ ቢሰማራ ተገቢም አይሆንም ፣ የመረጃ ብዝሃነትም አፈር ይግጥ ነበር።

የመንግስት ፕሬሶች ጭልጥ ወዳለ አፍቃሬ መንግስት ግብር ሲገቡና የህዝቡን ህይወት ረስተው የፓርቲ ፖለቲካ ማናፈሻ መድረኮች ሲሆኑ፤ በተቃራኒው የግሉ ፕሬስ የመንግስት ፕሬሶች በማይነኩት ችግሮችና ስህተቶች ላይ ብቻ አተኩሮ ሲሰራ፤ የፕሬስ ‘ተዓማኒነት’ ድንበር የቱ ጋ እንደሆነም ለማወቅ እስኪያስቸግር ድረስ ተደባለቀ። ህዝቡ የሰለቸውን የራዲዮ እና ቴሌቪዠን ፕሮፓጋንዳ ሽሽት በነጻው ፕሬስ መረጃ ጥላ ስር ራሱን መቅበሩ በአወንታዊ ጎኑ የማንበብ ባህልን አዳብሮ የጋዜጣና መጽሄት ህትመት እንዲሰፋ ቢያደርግም፤ በዚያው ልክ በነጻው ፕሬስ በተቃውሞ እና ክስ ላይ ካላተኮረ በቀር፣ በሚዛናዊነት የሚሰራውን ስራ የማግለል እና የመፈረጅ ባህል እንዲሰፍን ምከንያት ሆነ። ቲሞቲ ስፔንስ የሚባል በ1994 አስከ 1998 ድረስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ትምህርት ይሰጥ የነበረ የጋዜጠኝነት ባለሙያ እንደሚናገረውም የኢትዮጵያ ፕሬስ በሁለት ጫፍ ተይዞ በአንባቢ ምርጫ የሚጎተትና የራሱን አጀንዳ መቅረጽ እንዳይችል ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ ፕሬስ እንዲሆን ምክንያት ሆነ።

የፕሬስ የቁልቁለት ጉዞ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር አድጎ የነበረው የህትመት ውጤቶች ገበያ ማሽቆልቆል የጀመረው እንደሚባለው ከወረቀት ዋጋ መወደድ እና ከሶሻል ሚዲያው መስፋት፣ እንዲሁም ከአሳታሚዎች አቅም ማነስና ከማስታወቂያ እጦት ጋር በተያያዙ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ አለመሆኑን በተደጋጋሚ መድረኮች የፕሬስ ባለሙያዎቹም ይሁኑ ጉዳዩን የሚያጠኑ ምሁራን የሚገልጹት ሃቅ ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ህትመት ኢንደስትሪ ውስጥ የግልና የመንግስት ጋዜጣና መጽሄቶች ተደምረው ቁጥራቸው ወደ 24 ባሽቆለቆለበት ሁኔታ፣ በተግባር ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄራዊ ቋንቋ የሚታተሙ የግል ጋዜጦች ቁጥር ወደ 3 በወረዱበት ሁኔታ፣ ብዛት ያላቸው በሃገሪቱ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትና ጤናማ ማህበረ ፖለቲካ ለመገንባት አቅም የነበራቸው መጽሄቶች ከገበያው እንዲጠፉ ተደርገው የህትመት ዘርፉ በቀጨጨበት ሁኔታ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ተከብሯል ብሎ መናገር አባይነት ይሆናል። ዘንድሮ ሚያዝያ 25 ቀን በሃገር አቀፍ ደረጃ በተከበረው የፕሬስ ነጻነት ቀን ላይ ከተሳታፊዎች እንደተነገረው የኢትዮጵያ የፕሬስ ጉዞ በቁልቁለት መንገድ ላይ ነው።

መንግስት፤ የፕሬስ ነጻነትን የሚያረጋግጡ ህጎች ማውጣቱንና፣ እነዚህ ህጎች ለብቻቸው በሃገሪቱ የፕሬስ ነጻነት መከበሩን እንደሚያረጋግጡ ደጋግሞ ቢናገርም፤ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ፕሬስ አፋኝ ሃገር መሆኗ ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በተባለ ተቋም በ2018(እ.ኤ.አ) አለም አቀፉ የፕሬስ ፍሪደም ኢንዴክስ ላይ ከ180 ሃገራት ያገኘችው 150ኛ ያሽቆለቆለ ደረጃ ብቻ አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል። ሰነዱ ቃል በቃል “….Ethiopia at 150th place out of 180 countries, is one of the worst places for press freedom and journalists” ይላል። እዚህ ጋ በ1987 ዓ.ም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በህ-ገመንግስቱ ተደንግጎ፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ በ2000 ዓ.ም ታውጆ በአንጻራዊነትም ፕሬስ የህግ ማዕቀፍ ተቀምጦለት ባለበት ሁኔታ፣ ፕሬሱን ወደ ቁልቁለት መንገድ የነዳው ምንድነው የሚለውን መጠየቅ ግድ ይሆናል። የኢኮኖሚና ፖለቲካ ግፎች የኢትዮጵያ ፕሬስ እንዲያሽቆለቁል የኢህአዴግ መንግስት ለአመታት ሆን ብሎ ብዙ ለፍቷል።

በተለይ የ1997ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በሃገሪቱ የተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ ኢህአዴግ ከየትኛውም ነገር በላይ ፕሬስንና ብዕርን እንዲፈራ ስላደረገውና ለዚህ ህዝባዊ ተቃውሞ መሰረታዊ አነሳሽ ፕሬሱ ነው የሚል ጭፍን ድምዳሜ ላይ ስለደረሰ የተለያዩ አፋኝ ህጎች በማውጣት የፕሬሱን አቅም ለመሰባበር ሙከራ አድርጓል፣ ተሳክቶለታልም። ተከትሎም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዊችንና አመራሮችን በማሰር፣ ጋዜጠኞችን በሃገር መክዳት ወንጀል ወህኒ በማጎር፣ ያንን ተከትሎም እንደ ጸረ ሽብር ህግ እና የመሳሰሉትን አፋኝ መመሪያዎች በማውጣት ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሚታትሩና በሃገራቸው ፖለቲካ ውስጥ የህዝብ መደመጥንና ጥቅምን ለማረጋገጥ መረጃን በማዳረስ ሙያዊ ግዴታቸውን የሚወጡ ጋዜጠኞችን በሽብር ህግ እየከሰሰ ወደ ወህኒ አውርዷል። እንደነእስክንድር ፣ ተመስገን፣ ርዕዮት፣ውብሸት እና ሌሎችንም በዚህ የመንግስት የፕሬስ እቀባና ፍራቻ ጦስ የተለያዩ ክሶች ተመስትሮባቸው ወደ ወህኒ ተወርውረው የነበሩ ጋዜጠኞችን መጥቀስ ይቻላል። ይህ አልበቃ ብሎም በርዝራዥ የተረፉ የነጻ ፕሬስ ውጤቶችን “የግንቦት ሰባት እና አሸባሪ ድርጅቶች ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፣ ሃገሪቱን ለማፈራረስና ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድ ይሰራሉ፣ በመረጃ ነጻነት ሰበብ ጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል” ወዘተ በማለት የህትመት ውጤቶቹ እንዲዘጉ እና አሳታሚዎችም እንዲከሰሱ በማድረግ ብዛት ያላቸው መጽሄቶች ከገበያ እንዲወጡ አድርጓል። በተካሄደው የታቀደ የማዋከብና የማስፈራራት ሥራ በኢንደስትሪው ውስጥ አወንታዊ ሚና መጫወት የሚችሉ ብዛት ያላቸው ባለሙያዎች ስደት ገብተዋል ። ኢህአዴግ እነዚህን ሁሉ የተቀነባበሩ ጥቃቶች በፕሬሱ ላይ ሲፈጽም፤ በአንድ በኩል ጋዜጠኛን አልከሰስኩም እያለ መግለጫ በመስጠት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛው የሚሰራበትን ሚዲያ እንዳይተርፍ አድርጎ እያጠፋ ተግባሩን በማይታረቅ ተቃርኖ ውስጥ ከትቶ ነው። ይህ መንግስት በፕሬሱ ላይ ከሰነዘረው ቀጥተኛ ጥቃት ባሻገር ፕሬሱን በኢኮኖሚ እንዳይዳብርና በኪሳራ እንዲከስም ማስታወቂያ የሚሰጡ ድርጅቶችን በማስፈራራት፣ ማተሚያ ቤቶችን እንዳያትሙ በመከልከል፣ የህትመት እና ወረቀት ዋጋን በማናር እና የመጽሄት እና ጋዜጦችን ስርጭት ለመግታት የህትመት ውጤቶችን ሰብስቦ እስከማሰር የደረሱ ከአንድ መንግስት የማይጠበቁ የወረዱ ተግባራትን አከናውኗል።

ይህንን ተከትሎ አቅማቸው የሳሳ እና ገበያውን የመቋቋም አቅም አጥተው የከሰሙ የፕሬስ ውጤቶችን “በኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት በገበያው መዝለቅ ባለመቻላቸው የተበተኑ” የሚል ስም አውጥቶ ራሱን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሞክሯል። አጥፊ ስነ-ልቡና “ስነልቡናው በማጥፋት የተለከፈ የማልማት በር የቀዳዳ ያህል አይታየውም፡፡ ” እንደሚባለው ኢህአዴግ ፕሬሱ ላይ ካለው ቂም እና መሰረተ ቢስ ውንጀላ የተነሳ ነጻው ፕሬስ እንዲያብብ አይፈልግም። በአንጻሩ በነጻ ሚዲያ ስም በገበያው ውስጥ ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚሰገስጋቸውን የህትመት ውጤቶች የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እየነሰዙ የኢትዮጵያ ፕሬስ ሃላፊነት የጎደለው እንደሆነ እንዲሰብኩ ሲያተጋ ኖሯል። በዚህም ወጣ በዚያም ወረደ መንግስት ኢትዮጵያን ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኝነትን ለመተግበር የሲዖል ያህል ከከፉ ሃገራት አንዷ ተደርጋ ከመታየት ግን አላገዳትም። የአለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎችም ተቋማት ኢትዮጵያን በብዙ ሲከስሱና መንግስት ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ሲጠይቁ ኖረዋል። በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ “እስክንድር ነጋን እጃችንን ጠምዝዘው ያስፈቱት እንደሁ እናያለን” እስከማለት የደረሰ እልህ የተጋባችው ይህች ሃገር ፕሬስን በተመለከተ አስካሁንም የቆሸሸ ገጽታ ይዛ የተቀመጠችው መንግስት በተከተለው አጥፊ ስነልቡና ነው። “ለፕሬስ አጥፊ ፌስቡክን ያዝለታል” ዛሬ መንግስት በተደጋጋሚ “በሶሻል ሚዲያው ሃላፊነት የጎደለው እና የሃሰት ዘገባ ይሰራጫል፣ ህዝብና ህዝብን የሚያቃቅሩ መረጃዎች ይወጣሉ፣ ጠባብነት ሰፍኗል የተቃውሞ ባህል ብቻ ዳብሯል” ወዘተ እያለ እሮሮ ያሰማል ፣ ይወተውታል።

በህግ ተመዝግቦና አድራሻው ታውቆ ተገቢ ግብር ከፍሎና ህጋዊ ሆኖ የሚሰራ፣ የህትመት ይዘቶቹ ተገምግመው ሲያጠፋም እየታረመ መልካም ሲሰራም አይዞህ እየተባለ መቀጠል ይችል የነበረውን ነጻ ፕሬስ አውድሞ አንድ ድምጽ ብቻ እየሰማ በሰላም ለመቀመጥ ያሰበ መንግስት የእጅህን አግኝ ሲለው የቴክኖሎጂ ትሩፋት የሆነው፣ ማንም የማያዘውና የሚለቀቀውን መረጃ ምንጭ ለማወቅ የሚከብደውን ፌስ ቡክን አዘዘለት። እነሆም በዚህች ሃገር ዛሬ የመጣው ለውጥ በዋናነት የተዘጋውን የመረጃ አማራጭ ወለል አድርጎ በከፈተው ነገር ግን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ አደጋም ያለው ፌስቡክ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው። “ ሁሉም በር ሲዘጋ ግድግዳም በር ነው” እንደሚባለው መንግስት የመተንፈሻ በሮችን ሁሉ ዘጋግቶ የተቃውሞ ድምጽ ግድግዳውን እንዲያፈርሰው አድርጎታል። የኢትዮጵያ ፖለቲካም ዛሬ ይሆናል ተብሎ ባልተጠበቀ መስመር እየተጓዘ ያለው በዚሁ የታፈነ ድምጽ በፈጠረው ማዕበል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። መንግስት መረጃን እያረጋጋ እና ሚዛናዊነትን እያሰፋ በህግ የሚመራውን ፕሬስ ምህዳር እንደጀመረው እያጠበበ ከሄደ ዛሬ የተረጋጋ የሚመስለው የፖለቲካ መስመር ዳግም እዚህም እዚያም በሚበታተኑ መረጃዎችና ባልተጠኑ ውሳኔዎች በማንኛውም ጊዜ ስላለመናወጡ ዋስትና የለም።

(ምንጭ፤ ግዮን)

Share.

About Author

Leave A Reply