“ኢህአዴግ እንደለመደው ተቋማቱን ለራሱ ሰዎች በፍፁም መሸጥ የለበትም” ረ/ፕ መረራ ጉዲና

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግዮን፡- በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተሰብስበው ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፤ ይህንን እንዴት ተመለከቱት?

ዶ/ር መረራ፡- የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ወደብሔራዊ እርቅና መግባባት ቢሄዱ ይመረጣል:: ምንም ጥያቄ የማያስፈልገው ነገር ነው:: በተቻለ መጠን የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር የሆነው የአሰብ ወደብ ጉዳይም በውይይቱ ውስጥ ቢጨመርበት በጣም ጥሩ ነው የሚል ግምት ነው ያለኝ:: የአሰብ ጉዳይ ተጨምሮበት እርቁ ሁለቱም ህዝቦች በተሻለ መንገድ የሚጠቀሙበትና መልካም ግንኙነታቸው የበለጠ ተጠናክሮ ሰላማዊ ሕይወት ሊመሩ የሚችሉበት መንገድ ቢሠራ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ::

ግዮን፡- ኢህአዴግ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሳይነጋገር በራሱ ያሳለፈውን የባድመ ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ይቀበለዋል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር መረራ፡- በደስታ ነዋ! ኤርትራ እኮ እየጠየቀች ያለችው እሱን ነው:: ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከአሁን ድረስ በድርድር እንጂ ዝም ብዬ አልለቅም በሚል ምክንያት ነው የቆየው:: ውሳኔው እኮ ከተላለፈ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል:: የኢትዮጵያ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ይህንን ሐሳብ ከመቀበል ባሻገር ወደተግባር ለመለወጥ ፍላጎት ካሳየ የኤርትራ መንግሥት እምቢ የሚልበት ጉዳይ አይኖርም:: ሐሳቡን ይቀበላሉ እንጂ ወደኋላ ያፈገፍጋሉ ብዬ አላስብም::

ግዮን፡- እንደዚህ ዓይነት የውሳኔ ሐሳብ በሥራ አስፈፃሚው ብቻ ከመወሰኑ በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አልነበረበትም?

ዶ/ር መረራ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እኮ የኢህአዴግ ነው:: ምንም ለውጥ የለውም:: የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባላትም ሆኑ በህዝብ ተወካዮች ውስጥ ያሉት ሰዎች አንድ ናቸው:: ስለዚህ ራሳቸው ተሰብስብው ወሰኑት፣ ምክር ቤት አደረሱት ለእኔ ምንም ለውጥ የለውም:: ግን ዋናውና ትልቁ ጉዳይ በሁለቱ ህዝቦች መካከል በድጋሚ ሌላ ጦርነት እንዳይካሄድ ሰላማዊ ጉርብትና ቢፈጠር እኔ እደግፈዋለሁ:: መሆን ያለበትም ይሄ ነው::

ግዮን፡- ጉዳዩ ከሚመለከታት ኤርትራ ጋር ውይይት ሳታደርግ ኢትዮጵያ በራሷ ፍላጎት ብቻ ይህንን ውሳኔ ማሳለፏ ምንን ያሳያል?

ዶ/ር መረራ፡- ሰዎች በተለያየ መንገድ ሊደራደሩ ይችላሉ:: ሊነጋገሩ ይችላሉ:: እሱን እኛ አናውቅም:: አንዱ ለሌላው ቃል የሚገባው ነገር ሊኖር ይችላል:: በዲፕሎማሲና በሌሎች መስመሮች ሊከናወን ይችላል:: እነሱን ሁሉ ስለማናውቅ በዚያ ላይ አስተያየት መስጠቱ ያስቸግረኛል:: ዞሮ ዞሮ ግን ሁለቱ ህዝቦች ዘለቄታዊ ሰላም ማግኘታቸው ለወታደራዊ ወጪ፣ ለወሰን ጥበቃ እየተባለ የሚወጣው ወጪ ወደልማት ሊዞር በሚችልበት መንገድ፤ በተለይ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ተጠቃሚ በምትሆንበት መንገድ ላይ ትኩረት ቢደረግ ጥሩ ይመስለኛል:: የኢትዮጵያ ህዝብም የሚፈልገው ይህንን ነው::

ግዮን፡- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚዎች በውሳኔያቸው ላይ እስከዛሬ ድረስ ሳይነኩ የቆዩትን ትልልቅ የመንግሥትና የህዝብ መሠረተ ልማት ተቋማት ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል:: በዚህስ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር መረራ፡- በዚህ ላይ ሁለት ስሜቶች አሉኝ:: አንደኛው መንግሥት ተሸክሞት መሄድ ያቃተው፤ ለምሳሌ፡- የመብራት ኃይልን ተቋም ብንመለከት፤ ብዙ ቦታዎች እኔን ጨምሮ በጨለማ ውስጥ ነው ብዙ ጊዜ የምናሳልፈው:: ስለዚህ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት፣ ተጨማሪ ገንዘብ ተገኝቶ በዚህ ተቋም ውስጥ ያሉ ችግሮች ቢሻሻሉ የግል ባለሐብቶች በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ገብተው አገልግሎቱን ቢያሻሽሉ ተቃውሞ የለኝም:: ሁለተኛውና በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ ትልቅ ሥጋቴና ጥርጣሬዬ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት እንደለመደው የሚሸጡትንና ወደግል የሚዞሩትን ተቋማት ቅርበት ላላቸው ተጠቃሚዎችና ለራሳቸው ወገን ካደረገና፤ ብሎም ተጠያቂነት በጎደለው፣ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ዝም ብሎ ከዚህ በፊት እንደፈፀመው ወደተሳሳተውና የጥፋት አሰራሩው ከገባ ትልቅ ጉዳት ያመጣል:: የህዝቡን ሐብት የግል ባለሐብቶች ሲገዙት፣ መንግሥትም ለእነሱ ሲሸጥ ቀጥተኛና ተጠቃሚነቱን ባማከለ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል:: ስለዚህ ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በሚያደርጉበት መንገድ እንደገና እንዲደራጁ ቢደረግ ተቃውሞ የለኝም::

ግዮን፡- በተለይ ኢህአዴግ ሊከተላቸው የሚገቡ የሽያጭ ዝርዝር መንገዶች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር መረራ፡- ከዚህ በፊት የመንግሥት ልማት ተቋማት የሚባሉት ዝም ብሎ በቀላል ዋጋ፣ ምንም ቀዳዳ በማይሸፍን ገንዘብ፣ ግለሰቦችና የራሳቸው ሰዎች እንዲጠቀሙ ተብሎ ሲሸጡ፣ ሲለወጡ አይተናል:: እንደዚህ ዓይነቱ ነገር በአሁኖቹ ግዙፍ ተቋማት ላይ እንዳይደገም፣ ግለሰቦች የህዝቡን አንጡራ ሐብት ባልሆነ መንገድ እንዳይጠቀሙ፤ ግልፅ በሆነ፣ ሁሉም ሊያየው በሚችልበት መንገድ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው ነው ለሌላ ወገን መተላለፍ ያለባቸው:: አሁን ያልኩት ጥንቃቄ ግን ያስፈልጋል:: ተቋማቱን እንደተለመደው ኢህአዴግ ለራሱ ሰው መሸጥ የለበትም::

ግዮን፡- እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ ተቋማት ሲሸጡ፣ ተበዳዩ ሠራተኛውም ጭምር ነው የሚሆነው፤ ይህ ነገር ችግር አይፈጥርም?

ዶ/ር መረራ፡- ሠራተኛውም የተሻለ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበትን መንገድ እኮ ማየት ያስፈልጋል:: መንግሥት ተቋማቱን ለግል ባለሀብቶች ሲሸጥ ሠራተኛው ተጠቃሚ የሚሆንበትን፤ በዚያው መንገድ የሚሸጡት ድርጅቶች ለህዝቡ የሚሰጡትን አገልግሎት የማሳደግ ሥራ በእኩል ሁኔታ ማመጣጠን ይኖርበታል:: የሠራተኛ ጉዳይ ሳይታይ ዝም ብሎ የሚታለፍ መሆን የለበትም:: ሌሎች ሀገሮችም እንደዚህ ዓይነት እርምጃ ሲወስዱ ለሠራተኛው ዋስትና ቅድሚያ ይሰጣሉ:: ለምሳሌ፡- በነገሩ የሚገቡ ባለሐብቶች ሠራተኛውን አላስፈላጊ በሆነ መንገድ ዝም ብለው ሜዳ ላይ እንዳይጥሉና እንዳያባርሩ ተገቢ ድርድር ይደረጋል የሚል ግምት አለኝ:: በዚህ በኩልም በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል::

 

ግዮን፡- ትልልቅ ተቋማትን ደፍሮ ለግል ባለሐብቶች ማዘዋወር የጠ/ሚኒስትር ዓቢይ ፍላጎት ወይስ የህወሓት የቀደመ ልምድ ይመስልዎታል?

ዶ/ር መረራ፡- ብዙ ሰዎች ህወሓት ተሸንፏል ብለው ሲያወሩ እሰማለሁ:: ህወሓት ትንሽ ተገፍቶ ሊሆን ይችላል እንጂ አሁንም ህወሓት በኢህአዴግ ላይ የበላይነት ያለው ድርጅት ይመስለኛል:: በተለይ ወታደራዊና የደህንነት መዋቅሩን ከሞላ ጎደል የተቆጣጠሩት አሁንም የህወሓት ሰዎች ናቸው:: ይሄ ህወሓት ተሸንፏል የሚለው ነገር ገና ነው:: በባድመ ጉዳይም ሆነ በተቋማቱ ሽያጭ ላይ የእነሱ ስሜትና ፍላጎት ሳይሰማ የሚወሰን ነገር አይኖርም:: ህወሓት ተስማምቶበትና ፈልጎት የተደረገ ውሳኔ ነው::

ግዮን፡- እነዚህ ወደውሳኔ የመጡት ሁለት ጉዳዮች በህዝቡ ዘንድ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል፤ ከዚህ አንፃር ውሳኔዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ቀጣይ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥሩት ችግር ይኖራል?

ዶ/ር መረራ፡- እዚህ ሀገር መሠረታዊው ጉዳይ፣ የመቶ ሚልዮን ህዝብ ህልውና ጉዳይ የሆነውን ፖለቲካችንን ማስተካከል ነው:: ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር ነው:: ሁላችንንም የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው:: እዚያ ላይ ነው የጠ/ማኒስትሩም ሆነ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው:: ፖለቲካችንን አስተካክሎ፣ ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሮ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ይሁንታ ያገኘ ፓርቲ ሥልጣን ላይ የሚወጣበት፤ ይሁንታ ያጣ ፓርቲ ከሥልጣን የሚወርድበት፤ ዜጋን በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠርና ያለመፍጠር ጥያቄ ነው ወሳኙ ጉዳይ:: ይሄ አካሄድ ነው ለሁላችንም የሚጠቅመው:: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመፍጠር፣ ተግቶ በመሥራት እና መሠረታዊ ለውጥ እየጠየቀ ያለው ወጣቱ ተረጋግቶ ወደልማትና ወደሌሎች ነገሮች በሚሄድበት መንገድ ላይ መሥራቱ ነው እንጂ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ውሳኔ አይደለም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው:: ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ተወግደው በማያዳግም ሁኔታ አዲስ ታሪክ ይፈጠራል ብዬ እገምታለሁ::

ግዮን፡- እናመሰግናለን::

Share.

About Author

Leave A Reply