ኢህአዴግ ይታመናልን?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በዶክተር ዐብይ አሕመድ መመረጥ ልባችን ጮቤ ረግጧል:: ደማችን ሞቋል:: ወኔያችን ተነቃቅቷል:: የፈረሰው የኢትዮጵያዊነት ስሜታችን ተጠግኗል:: የመከፋፈል፣በብሔር ተቧድኖ የመጎሸማመጥ ፍላጎታችን እንደ አሮጌ ጨርቅ ተበጣጥሶ ተጥሏል:: አቶ ለማ ከወር በፊት እንዲያጎነቁል ያደረጉት ‹የኢትዮጵያዊነት ሱስ› አክለፍልፎ ‹ዐብይ ዐብይ ዐብይ› አስብሎናል:: በአንድ ጀንበር የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን፣የሀገር ሰፈሩ፣ የወጭ ወራጁ ወሬ ኢትዮጵያዊነት ሆኗል:: የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በቅጽበት ‹ተከርብቶ› የድል አጥቢያ አርበኛ መሆን ጀምሯል::

ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነት ከብሔርም፣ከጎጥም በላይ ነው ብሎ ሲጮህ ከነበረው ሀገር ወዳድ፤ ጎጠኝነትን ጠል ከሆነው ማኅበረሰብ ቀድሞ ‹ከኔ በላይ ኢትዮጵያዊ ላሳር› ብሏል:: እሰየው ነው:: ይሁን ግድ የለም:: ኢቲቪ ይልመድብህ ብለናል:: አንዳንድ ሰዎች አሉ በሰው ድግስ በባከነ ሰዓት መጥተው አንደኛ አድራጊ ፈጣሪ የሚሆኑ:: ወር ሙሉ የለፉ ሰዎች ሳሉ ባናቱ መጥተው ‹ከኛ ወዲያ ፉጨት አፍ ለማሞጥሞጥ ነው› የሚሉ:: በሰው ድግስ ውዳሴ ከንቱን የሚሸምቱ:: ይሁን ግድየለም:: ኢትዮጵያዊነት ሆደ ሰፊነት ነው:: (ሰሞኑን ኢትዮጵያዊነት የማይሆነው የለም) ግን ግን አቶ ዐብይ ኢሕአዴግ ናቸው:: ጭፍጉ ኢሕአዴግ፣ፊቱ የማይፈታው፣በጉልበት፣በጡንቻ የሚያምነው፣ቂመኛው ኢሕአዴግ:: ጠላቶቹን አሳዶ የሚያጠፋው፣ቀን ጠብቆ ጠልፎ የሚጥለው፣ከትንሽ ትልቁ ጋ ‹ና ይዋጣልን› ብሎ ለጠብ የሚጋበዘው ኢሕአዴግ:: እኔ ብቻ ትክክል ሌላው ወሽካታ፣ የኔ መንገድ ብቻ ቀና የሌላው ጎርበጥባጣ፣ በክፉ የሚያየኝ ዓይኑ ይጥፋ ባይ ተራጋሚ ኢሕአዴግ:: የቀድሞው ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በባሕሪያቸው ጠፍጥፈው የሠሩት ኢሕአዴግ:: ‹‹ደማችንን ያፈሰስንለት አጥንታችንን የከሰከስንለት፣ብዙ ጓዶች ሥጋቸውን አሞራ የበላው በየዳርድንበሩ የወደቁለት ፓርቲያችን…..›› እየተባለ 27 ዓመታት በሙሉ አዳዲስ አስተሳሰቦች እንዳይመጡ፣ ወጣት ምሁራን የሚያቀርቡት ተራማጅ ሐሳብ በኋላቀሩ ጎምቱ ሰዎች ሐሳብ የሚመታበት ኢሕአዴግ::

ለሩብ ክፍለ ዘመን ከገጠር እስከ ከተማ የተንሰራፋ፣ ድርቅ ያለ አመለካከት አራማጅ የሆነው የኢሕአዴግ ፓርቲ አባል ናቸው አቶ ዐብይ:: ብሎም ሊቀመንበር:: ታዲያ አቶ ዐብይን ከፓርቲያቸው ነጥዬ እንዴት ልመልከታቸው? ኢትዮጵያዊን እስካሁን የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር ሄዶበት በማያውቀው መንገድ ዶክተር ዐብይ ያውም የኢሕአዴግ ቁንጮ ሰው ሆኖ በአስተሳሳሪ መንፈስ ሊሰበስበው ቃጥቷል:: በሰንሰለቱ፣በአቀናጅ ዘለበቱ፣በአንጸባራቂ ሕብሩ፣በጠንካራ ገመዱ በኢትዮጵያዊነት:: የየዋሁን ሕብረተሰብ መንፈስ ቀድሞ የተረዳው ዶክተር ዐብይ ቁስሉን በማከክ የመንፈስ ሕብርን ፈጥሯል::

በለሰለሰ አንደበት ጠንካራ ምኞትን እውን ለማድረግ መንገድ ጠርጓል:: በዚህም በመከራ የፍጻሜ ጫወታ ላይ ጎል እንዳገባ ተወዳጅ ቡድን ከመቀመጫ ብድግ አስደርጎ እርሰ በርስ አስተቃቅፏል:: ግና ዶክተሩ የኢሕአዴግ ምልምል በመሆኑ፣ባለ ርዕዩን ቅዥታም የሚያደርግ ድርጅት አባል በመሆኑ፤ የዶክተሩ ንግግር መተግበሩ ሕልም ነው ብለን እንድንጠረጥር ሆነናል:: ምክንያቱም ኢሕአዴግ እስከዛሬ የመጣበትን መንገድ ዓይተናልና:: ኢሕአዴግ ለቀረጸው ርዕዮተ-ዓለም፣ ለድርጅቱ ሕግና ደንብ እንጂ ለሕዝብ ታማኝ ሆኖ አልመጣም:: የድርጅቱን ሕልውና ለማቆየት የቀረጸው መመርያ በአባላቱ ላይ የተተበተበ ድር ሆኗል:: ልክ እንደ አባባ ሽፋው ከዘራ:: መንፈሱን ፈርተው እንደተገዙለት እንጨት:: ‹‹አባባ ሽፋው›› የሸኽ ሸረፈዲን አንካሴ ነው:: ሸኽ ሸረፈዲን የቦረና ሸኽ ናቸው:: ይህ አንካሴ ሸኹ ለሽምግልና ሲሄዱም ሆነ ለጉዳያቸው በተንቀሳቀሱ ቁጥር ከእጃቸው አይለይም ነበር::

በሌላ ተረክ ሸኽ ሸረፈዲን ‹‹አባባ ሽፋው›› የሚባሉ አበጋር ነበራቸው:: በአንድ አጋጣሚ አበጋሩ ታሞ ይሞታል:: ይሄ አባባ ሽፋው ሸኹን ወክሎ ይሠራ በነበረው ሽምግልናም ሆነ ብዙ ሌሎች ጉዳዮች፤ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ ስለነበር ሕዝቡ በመሞቱ ኅዘን ይሰማዋል:: ለቦረናው ሸኽም ‹‹እንደ አባባ ሸፋው ሆኖ የሚያገለግለን ልጅ ይውለዱልን›› ይሏቸዋል:: ‹‹…ተናግሮ ሰው የማያስቀይም፣አብሉኝ አጠጡኝ ብሎ ሰው የማያስቸግር፣ ሞት የማያገኘው ይህንን አንካሴዬን ስለ ሸፋው ሰጥቼያችኋለሁ›› ብለው አንካሴያቸውን ባርከው ሰጧቸው:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንካሴያቸው ‹‹አባባ ሽፋው›› ተባለ ይለናል ዶክተር ሙሐመድ ዓሊ በቅርቡ በታዛ መጽሔት ባወጣው ጽሑፍ:: ታዲያ የዋሁ ሕዝብ ሸኽ ሸረፈዲን ከሞቱ በኋላ የተጣላን በማስታረቅ፣የተሰረቀን በማስመለስ፣የተጋደለን ደም በማድረቅ እስከ ዛሬም በአንካሴው ይገለገሉበታል ይለናል::

ይህ አንካሴ ከሰው ያልተናነሰ ክብር ተሰጥቶት ለሽምግልና ይዞራል፣የክብር ማረፊያ ቤት ተሠርቶለታል:: በአጠቃላይ ቅብጥ ብሏል:: አንካሴው ሳይሆን መንፈሱ ተፈርቶ:: ሰዎች ራሳቸው የፈጠሩትን ግዑዝ ነገር አምላኪ፣ለግዑዙ ተንበርካኪ ሆነው ሲኖሩ በተደጋጋሚ ያጋጥማል:: ኢሕአዴጋውያንም ነጻነታቸውን የሚገድብ ለራሱ ግን ከፍተኛ ነፃነት ሰጥተው የግዑዙ ሕግ ተንበርካኪ ሆነዋል:: ጭፍጉ ሕግ አንዴ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› ይሆናል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ› ሆኖ ብቅ ይላል›:: ኢሕአዴግ ለሕዝብ ፍቅር፣ ርሕራሄ፣ ሰብዓዊ ስሜት ኖሮት ሲያስተዳድር አላየንም:: ቋንቋው ከፋብሪካ እንደሚወጣ ፕላስቲክ ተመሳሳይ፣ አባላቱ ከመስመርህ እንዳትወጣ እንደተባለ ወታደር በአንድ አቅጣጫ ሲሄዱ ነው የምናውቃቸው::

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው ብሎ እንደማመኑ የሐሳቡ አራማጅ የሆኑት አቶ ዐብይ እንዴት የለውጥ ሐዋርያ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን? ወይስ ከኢሕአዴግ መስመር ያፈነግጣሉ? ነው ኢሕአዴግ ተለውጧል? የአስተሳሰብ የበላይነትን መያዝ፣በኔ መንገድ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው ብሎ ራስን ፍጹም አድርጎ ማቅረብ፣የሕዝብ አገልግሎት ተቋማትን ለሕዝብ ግልጋሎት ከመስጠታቸው በፊት የፓርቲው ጠባቂ ዘብ እንዲሆኑ ማስገደድ፣ፍርድ ቤቶች፣የሕግ አስከባሪ አካላት ታማኝነታቸው ከሕጉና ሕገ-መንግሥቱ ይልቅ የፓርቲው ሕልውና አስቀጣይ ሆነው መጓዝና እስከዛሬም መቀጠል፣ የሃይማኖት ተቋማት ኢሕአዴግ በሚፈልጋቸው ሰዎች ብቻ እንዲመሩ፣የትምህርት ተቋማት በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ከላይ እስከታች እንዲዋቀሩ ተደርጎ፤ በአቶ ዐብይ ንግግር ላይ ዕምነት እንዳያድርብኝ ወይም በጥርጣሬ እንድመለከተው አድርጎኛል::

የኢትዮጵያ ችግር በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው የሚፈታው ብሎ የሚያምነው ኢሕአዴግ የአስተሳሰብ ለውጥ አመጣ ወይስ ሕዝባዊ ወገንተኛ መስሎ ለመታየት ፈለገ? የዶክተር ዐብይን ንግግር በጽሑፍም፣በምስልም፣በድምፅም ይዤ ደጋግሜ ሳደምጠው ነበር:: ፓርቲያቸውን ሳያስገመግሙ ያመጡት ይሆን? ብያለሁ:: ቋንቋው ተቀይሮ መንፈሱ ልቆ መጥቷልና ጥርጣሬ እንዲያድርብኝ ሆኗል:: የሆነ ሆኖ ኢሕአዴግና የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቅርበዋል::

ተለጣፊ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሳይሆን የምር ኢሕአዴግን የሚገዳደሩ በመላው ዓለም የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢሕአዴግ ለዕርቅ እጁን ዘርግቶላቸዋል:: የይስሙላ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን:: የምር ለውጥ ከሆነ ቂመኛው ኢሕአዴግ እንደሞተ እንቆጥራለን:: ለዓመታት ሕዝብን ሲያሰቃዩ፣ በሕዝብ ሲሳለቁ የነበሩ የኢሕአዴግና የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በጡረታም ይሁን በዲፕሎማሲ ዘወር መደረጋቸው የሚጠበቅ ነው:: አዳዲስ ፊቶች በአመራር ልምድ ካላቸውና ሐሳባቸው በፓርቲ ተጽዕኖ ምክንያት የተገፋ ባለሙያዎች ወደፊት መምጣት አለባቸው:: ሃገራችንን የማዳን ኃላፊነት የሁላችንም ነው:: ሁሉም በሃገሩ ጉዳይ ተሳታፊ የሚሆንበት ዕድል ሊፈጠር ይገባዋል::

ፓርላማው ተጣብቶት የነበረው ድብታ ተላቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲጸድቅ ለመጀመርያ ጊዜ 88 የኢሕአዴግ አባላት እንደተቃወሙት ሁሉ፤ በሌሎች ሀገራዊ አዋጆችም ተከራክሮ የማይታመንበትን ገሸሽ አድርጎ ሊቀጥል ይገባዋል:: ጋዜጠኞች ሳይሳቀቁ መንግሥትንም ሆነ ኢሕአዴግን በጎ ሲሠራ አመስግነው፣ በጥፋቱ ተችተው መጻፍ ሊጀምሩ ይገባቸዋል:: የፍርሃት ድባብን ከላያችን ማንሳት ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል:: በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች በሀገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል::

ዶክተር ዐብይ የምራቸውን ከሆነ እውነተኛው ሕዳሴ አሁን መምጣት አለበት:: ኢትዮጵያውያን የምር እጅ ለእጅ ልንያያዝና ሀገራችንን ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት ከፍታ ልናደርስ ይገባል:: በሃይማኖት ይደረግ የነበረው ጣልቃ ገብነት መቆምና የግል ጥላቻቸውን በሕግና በመንግሥት ጥላ ሥር ተሸሽገው ይረጩ የነበሩ ሹማምንት ተገምግመው ተገቢው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል:: የትምህርት ፖሊሲው፣የፍርድ ቤቶች ነፃነት፣የማረሚያ ቤቶች አሠራር በሙሉ እንደ አዲስ ሊታይ ይገባዋል:: በጅምላ አስቦ በአንድ ድምጽ መወሰን ከቀረ ለውጥ በአንድ ጀንበር እንዲመጣ አይጠበቅምና በሂደት ሁሉንም እናያለን:: ቸር እንwሰንብት!

ግዮን መጽሄት

Share.

About Author

Leave A Reply