ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት ቪዛ በማጭበርበር ወንጀል አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጥፋተኛ ከሆኑ እስከ 30 ዓመት ሊፈረድባቸው ይችላል

ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያላግባብ የአሜሪካን የዲፕሎማት ቪዛ እንዲያገኙ አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረው፣ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት አስታወቀ፡፡

አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ምክትል ቆንስላ ጄኔራል የሆኑት ወይዘሮ ደስታ ወልደ ዮሐንስ፣ በሦስት የቪዛ ማጭበርበር ወንጀሎች ነው የተከሰሱት፡፡ ወንድማቸውን፣ የወንድማቸውን ሚስትና የወንድማቸውን ልጅ ያላግባብ የዲፕሎማቲክ ቪዛ እንዲያገኙ አድርገዋል ተብለው ነው የተወነጀሉት፡፡

ወይዘሮ ደስታ በቀረበላቸው ክስ መሠረት ወንድማቸውንና የወንድማቸውን ሚስት እኔ ላይ ጥገኛ የሆኑ የቤተሰብ አባል ናቸው፣ እንዲሁም የወንድማቸውን ልጅ የራሴ ልጅ ነው የሚል ደብዳቤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጽፈው ለአሜሪካ ኤምባሲ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2016 ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረትም የወይዘሮ ደስታ የቤተሰብ አባላት የአሜሪካን A-1 የተባለውን የዲፕሎማቲክ ቪዛ ማግኘቻው ታውቋል፡፡

ሆኖም የወይዘሮ ደስታ ወንድምና የወንድም ልጅ ወደ አሜሪካ ከገቡ አንስቶ በሎስ አንጀለስ ሳይሆን በዋሽንግተን ሲኖሩ እንደነበር መረጋገጡ ተገልጿል፡፡ ወይዘሮ ደስታ የቀረበባቸው ወንጀል ከተረጋገጠባቸው፣ በአሜሪካ ሕግ መሠረት እስከ 30 ዓመት በእስራት ሊቀጡ ይችላሉ፡፡ በወይዘሮ ደስታ ላይ የቀረበው ክስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዲፕሎማቲክ ደኅንነት አገልግሎት የወንጀል ምርመራ ቢሮ እያጣራው እንደሆነ ታውቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤትን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 

ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply