ኢትዮጵያዊነትን የዘነጋውን ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት እና ሀገራዊ ቀውስን የማረም መንገድ (ፋንታሁን ዋቄ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ይህን ጽሑፍ ጫር ጫር ያደረግሁት በነሐሴ 14/2010 ከአንድ የግል ሚዲያ ጋር ልነጋገርበት ስዘጋጅ ነበር፡፡ በመርሐግብር አለመመቻቸት ንግግሩ ስላልተሳካ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብለትፈው ብዞ ዜጎች ይጋሩታል ብይ ስላሰብሁ አንሆ ለጥፌዋለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ የበለጠ አንዳስብ ምክኒየት የሆነኝ ወንደሜ አቶ አብዱልፈታህ አብደላህ የኢትዮጵያ ፍትህ ሥርዓቶች ማዕከል ሥራ አስኪያጅን በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለሁ፡፡ ሰፊ ውይይት የሚፈልግ ሰው ከአብዱልፈታህ እና ከእኔ ጋር መገናኘት ይችላል፡፡
1. የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ውስጥ በሀሪቱ የሚኖሩ የቤተ እምነቶችና የባህሎች ትውፊት፣ ታሪክና እሴት እንዲጠበቅና በመጤ ፍልስፍና እንዳይደመሰስ የዜጎች ተሳትፎ ምን መሆን ይገባዋል? እንዴት ?
2. በተደረጃ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ለልጆቻችን የሚቀረበው የትምህርት ሥርዓት ፍልስፍና ማንን ለማገልገል ነው የሚሠራው? እኛን በእኛነታችን ወይስ እኛን በባዕዳን አምሳል ሊቀርፀን?
3. በኢትዮጵያ የተጀመረውን አወንታዊ ለውጥ እንደ ዕድል በመጠቀም ራሳችንን ወደ መሆን ለመመለስ ከሚደረጉ ስልታዊ እርምጃዎች መካከል በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻው ላይ መሳተፍ አንዱ ነው፣ በመሆኑም የክርስትና፣ የእስልምና እና የባሕል እምነቶች፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያዊ ማንነት ዋጋ የሚሠጡ ባህላዊና አዲስ እየተፈጠሩ ያሉ እምነቶች ምን ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ? እንዴት?
እነዚህን ጥያቄዎች በጋራ እንደ ኢትዮጵያዊያን አንድ በሚያደርገን እሴት እና በተናጠል በየቤተ እምነታችን አዎንታዊ አስተዋፅኦ በማድረግ ማንነታችንን ጠብቀን፣ ለዓለም የምንሰጠውንና የምንቀበለውን በጭፍን ገልባጭነት ሳይሆን በማስተዋልና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ባደረግንበት መንገድ የወደፊቱን ትውልድ በራሳችን ርዕይ፣ ግብና ዓላማ ዙሪያ ለማሰለፍ መወያየትና ስልት መቀየስ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንደተለመደው ዘመናዊ ሴኩለር ምሁራ ብቻ በዩኔስኮ ፍልስፍና እየተመሩ የሚጥሉ ከሆነ የትምህርት ጥራት ትርጉሙ ራስን ማጣትና የሌሎች ማኅደር ከመሆን፤ ሰውን ሁሉ አምራች ማሽን እንጂ ሰብአዊ ትርጉምና ክብር ያለው ዜጋ ማድረግ አይታይም፡፡ ውጤቱም ራስ ወዳድነት፣ ግለኝት፣ ሙስና፣ አቋራጭ የብልጽግና ፍተወት ያሳወረው ሆዳም ትውልድ፣ በሱሰኝነትና በአልባሌነት የተሸነፈ ወጣት ማፍራት ይሆናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በባህል ብዝሀነትና መስተጋብር ያዳበርነው መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶች አሉን፡፡ እነዚህ እሴቶቻችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለሺዎች ዘመናት ሲሸጋገሩ የኖሩት በሚከተሉት መሣሪያዎችና ተቋማት በኩል ነው፡-
1. የማኅበረሰቡን አብዛኛውን ክፍል ማንነት የሚቀርፁ ቤተ-እምነቶቹ ባህላዊ ትምህርት ቤቶች በኩል በሚሰጥ የሃይማኖትና የሥነ-ጥበብ ትምህርቶች
2. በእምነት አባትነት፣ በሥጋ ቤተሰብነት፣ በአስተዳደራዊ ሥልጣን ተዋረዳዊ መከባበርና መደማመጥ፣ መመሪያ መቀበልና መተማመን
3. በማኅበረሰቡ ውስጥ በመዋለድ ብቻ ሳይሆነ በዕድሜ በሚገኝ ሥልጣንና እውቀት ታላቁ ታናሹን በቀደመ እሴተ እየመዘነና እያረመ በመምራት
4. ወላጆች በተረት፣ በእንቆቅልሽ፣ በጫዋታና ቤተስብ ውስጥ ታናሽ ሁሉ ታላቆቹን የማክበርና የማዳመጥ ሥርዓት ጸንቶ መኖሩ
5. በማኅበራዊ የደስታ፣ የሀዘን፣ የሥራ፣ የጦርነት ዘመቻዎች፣ የግጭትና እርቅ፣ የባህላዊ የአምልኮና የአስተዳደር ሥርዓቶች ውስት በሚፈጠር መስተጋብር
ሰንሰለታዊ ተጋምዶዎች ነበር፡፡
ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ የአብርሆት (enlightenment) ዘመን ተብሎ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ከተሰጣቸውና ሴኩላር የሆነው የምርምር መንገድ ብቸኛ የእውቀት ምንጭ ስለሆነ በሳይንስ ያልተረጋገጠ፣ ለሳይንቲስቶች አእምሮ የሚጎረብጥ፣ የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በሳይንሳዊ ግኝቶችና ምክር የሚመሩ መሪዎች ያልወደዱት ወይንም የማይገባቸው ማንኛውም ሀሳብ ሁሉ ዋጋው ዝቅ እንዲል ዓለምአቀፍ ንቅናቄ ተጀመረ፡፡ ይህ ንቅናቄ በተባበሩት መንግሥታት ሕገ ደንቦች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች ውስጥ የበላይነት በመያዛቸውና የድርጅቶቹ አባል ሀገራት መሪዎች የሚወክሉትን ሕዝብ እሴቶች ወደ ጎን በመተው የየሀገራቸውን የትምህርት ይዘት፣ የሕግ ድንጋጌ፣ የመብትና ሰው የመሆን ትርጉም፣ የእድገትና የሠልጣኔ ግቦችና ርዕይ ሁሉ በተውሶ እንዲሆን ተገፋፉ፡፡ በዚህ መሠረት የሁሉ መሠረት የሆነው የሰው ልጆችን የማሰብ፣ የመሆን ፍላጎት አቅጣጫና የድርጊት ውሳኔ የሚመራውን አስተሳሰብ የሚቀርፀው ትምህርት ዓለም አቀፋዊ አሀዳዊ ቅርፅ እንዲያገኝ ሆነ፡፡ ብዝሀነትን በአንደበት እየሰበኩ በተግባር ግን ተቃራኒ በዳርዊን፣ በማልቱስ፣ በኒውቶንና በሌች ሴኩላር አውሮፖዊ ፈላስፎች የሀሳብ ማህቀፍ የተሠራ አንድ ድፍን ሣጥን ውስጥ ሰዎችን ሁሉ በሕግና በሥልጣኔ ስም የመክተት ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሲሆን በዚህ ድርጅት ፍልስፍና መሠረት ሀገራዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ቤተሰባዊ እሴትና የመኖር ትርጉም ሁሉ በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ከሚሰጥ የትምህርት ይዘት ተጠራርጎ እንዲወጣ፤ ተማሪዎች እምነትን የሚያንጸባርቅ ልብስና ምልክት እንዳያደርጉ፣ መንግሥታት ሕጎቻቸውንና ሥርዓተ አስተዳደራቸውን ሁሉ ምዕራባዊ ፍልስፍና ላይ እንዲመሠርቱ ይሠራል፡፡ ይህ ጥረት በዓለም ባንክና የገንዘብ ድርጅት፣ በተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብት ድርጅት፣ የጤና ድርጅት፣ የንግድ ድርጅት ወዘተ ጥምረታዊና የተናበበ ጣልቃ ገብነት የሚከናወን ነው፡፡
በኢትዮጵያችን የዘመናዊ ትምህርት አገልግሎት በመንግሥት ጥረት፣ በዜጎች ግብር ከፋይነት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የተጀመረው ሀጋራዊ፣ ባህላዊና እምነታዊ እሴቶችን በማግለል ነው፡፡ የሀገራዊ ትምህርት፣ ባህል፣ ሥነ ጥበብና ፍልስፍና ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ ከሥርዓተ መንግሥት እንዲገለል የታቸለው ሁሉ ተደርጓል፡፡ የማንነታችን ምልክቶች እንጥፍጣፊ የሚታየው ቤተ-ክርስቲያንና መስጊዶች መንፈሳዊ፣ ሥነ-ጥበባዊና የእጅ ሥራዎችን በቤተሰብና በአምልኮ ቅጽሮቻቸው ብቻ ነው፤ ማንነት የሚታለፈው በጣም በተወሰነ ደረጃ ቤተ-እምነቶቹን በክህነትና በማስተማር አገልግሎት ለሚሰለፉ ለአገልጋዮች በሚሰጥ የትምህርትና የትውፊታዊ ሂደት እየተላለፈ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዘመናዊው መንግሥታዊ የትምህርት አቀራረብና መንግሥታዊ ሥርዓት ዝርጋታ ውስጥ አዋኅዶ ማደራጀት አልታየም፡፡ በቤተ-እምነት ስም በሥርዓተ-መንግሥት ሂደት የሚሳተፉ የቤተ-እምነት መሪዎች በፖለቲካ አስተሳሰብ የተጠለፉና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሳይሆን ዘመናዊውን ባዕድ ፍልስፍና የሚያገለግሉ ሆነው የተፈለገውን ሀገራዊ እሴት በሚገባ መጠበቅ ሳይችሉ ቀርተዋል1፡፡
1ማርክሳዊ ወጣት በሀገሪቷ ትምህርት ቤቶች ተፈልፍሎ እግዚአብሔር የለም፣ ሰው ዝንጀሮነው፣ ነጻነት የነበረውን መካድና በአዲስ መለወጥ ነው፣ ሠልጣኔ እንደሌሎች መሆን ነው፤ እኩልነት የወላጅና ልጅ፣ የሃይማኖት አባትና አማኒ ተከታይ፣ የመምህርና ተማሪ፣ የታላቅና ታናሽ፣ የሴትና ወንድ ድንበር መደምሰስና ሁሉን በዘፈቀደ እንደገባውና አስቀድሞ እንደተጨመረበት መረጃ አንዲያስብና እንዲያደርግ መፍቀድ ሆኖ ሲተረጎም አንድም የሃይማኖትና የባህል አባቶችና እናቶች በዝምታ አሳልፈውታል፡፡ በዩኒቭርሲቲዎቻችን የታሪክ፣ የማኅበረሰብ፣ የሥነ-ሰብእ፣ የፍልስፍና እና የፖለቲካ ሳጥንስ መምህራን ባዕዱን አስትምህሮ የሚሞግት፣ የሚያቀና፣ የሚያለማና የኢትዮጵያ የሚደርግ አንዳች አስተዋጽኦ ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ያንኑ እንግዳ ትምህርት ተቀብለው ጠበቃና ጠባቂ ሆነው ሲሟገቱ ታዩ (እጅግ ጥቂቶች ከሞባሉት በስተቀር)፡፡

በዚህም ምክንያት ክርስቲያንና ከእስላም ቤተሰብ ተወልዶ ወደ ዘመናዊው ትምህርት ቤት የተላከው ወጣት ዩነቨርሲቲ ውስጥ ለወላጆቹ ባዕዳ የሆነ ፍልስፍና ሲጋት የሀገሩንና የቤተሰቡን ተውፊት በንቀትና በኋላቀርነት እንዲመለከት፤ አልፎም ተቃርኖ እስከመቆም
የሥልጣኔ፣ የዝማኔ፣ የመልካም ኑሮ ትርጉም፤ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሰላም ምንጭ ተብሎ በመላው ዓለም የትምህርት ይዘትና በሥነ-መንግሥት መዋቅር ውስጥ መሠረታዊ ፍልስፍና ሆኖ እየመራ የሚገኘው ሴኩላር ሥርዓተ-እምነት በመሆኑ ማንኛውም የትውልድ ትምህርት ሀገራዊ ለዛ እንዲኖረው አስፈላጊ ነው፡፡
የሀገራችንን የማያባራ መከራ ለዘመናት ያስከተለው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር ብክለት፣ የባሕር መናወጥ፣ የበሽታ ወረረሽኝ ወይንም የቴክኖሎጂ ችግር አይደለም፡፡ በየትውልዱ በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት የአንድ ጊዜ ነጠላ ጉዳይ ችግር ለመፍታት፣ ልማት ለማምጣት፣ ሀገርን ለመምራትና እኩልነትና ፍትሕን ለማረጋገጥ በባዕድ ፍልስፍና ተውሶ በግልብ እይታ የሚቀዱ የሕዝብን እሴትና ስነ-ልቡና የሚቃረኑ ግልብ እውቀቶች ያስከተሉት ውዥንብር ነው፡፡
የተሳሳተ አስተምህሮ ውጤቶችን ብንመለከት፡-
 ብዙ ንብረት የወደመው፣ ጅምላ ጨራሽ ጦርነቶች የተጫሩት፣ ሰዎች በዘር፣ በቦታና በቋንቋ ተከፋፍለው እንዲጠፋፉ የተደረጉት፤
 ከምዕራብ ወደ አፍሪካና አሜሪካ በመጓዝ የሰው ልጆችን ባሪያ ማድረግ፣ እንደ ቀይ ሕንዶችና የአውስትራሊያ አቦረጂኖች ያሉት የሰው ልጆች በገዛ ሀገራቸው እንደ እንስሳ ታድነው የተጨረሱትና የተረፉት በእንስሳት ዙ (Zoo) ሲቀመጡና ሲዝናኑባቸው የኖሩት፤
 እኛ ዛሬ የሀገራችንን ጠረፋማ አካባቢ የሚኖሩ እንቶቻችንን የሰውነት መተልተልና እርቃንነት ባህል ተራድተን እንደማሻሻል ለቱሪስት ገቢ ስንል የሰሜንን ጭላዳ ዝንጀሮና ዋሊያ እንደምናሳይ ሁሉ ያላንዳች ሀፍረት የአስጎብኚ ድርጅት ፈጥረን ለፈረንጅ የምናስጎበኝበት ፍልሰፍና ያዳበርነው፤
 ለድህነት የሚዳርግና ጥገኝነት የሚያስከትል የምጣኔ ሀብት ሥርዓት የተመሠረተው፣
 ምግባረ ብልሹ ትውልድ እንዲፈጠር የሆነው፣ በሌብነትና ዘረፋ የሚሠማራ ባለሥልጣን፣ ስደትና ተስፋ መቁረጥ የተጫነው ማኅበረሰብ፣ በአቋራጭ ለመበልጸግ ሲባል የትውልድን ዘለቄታዊ የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ የሚጥሉ ማኅበረሰባዊና ምጣኔ ሀብታዊ መዋቅራት የተፈጠሩት፤ ወዘተ
በዚሁ የራሳቸውን መሠረት ሙሉ በሙሉ ዘንግተው በባዕዳን ትምህርት ውስጥ ብቻ በማለፋቸው የራሳቸውን ማንነት በናቁ ልሒቃንና ባልሥልጣናት የተሳሳተ ሀገራዊ መሠረት የሌለው እንግዳ ትምህርት የተመራ አስተዳደር፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ እና የልማት ርዕይና ግብ በመጣ ግራ መጋባት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ከመዘንጋታችን የተነሳ በጭፍን የሰማነውንና ያየነውን ሁሉ ሳንመረምርና አንደሚጠቅመን አድርግን ሳናቃናው ለመጠቀም መሞከራችን በባህል፣ በልማት፣ በአስተዳደር፣ በፖለቲካ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በትዳርና የቤተሰብ አስተዳደር፣ በመንፈሳዊ ህይወት፣ በታሪክ ትርክትና ትንታኔ አሁን የምንገኝበትን ግራ መጋባትና ጥፋት አስከትሎብናል፡፡ ሌሎችን ለመምሰል በመጣጣር የምናጠፋውን ጊዜና ሀብት ከእድገት ይልቅ በስነ-ልቡና፣ በማኅበረሰብ የመስተጋብር ጥራት፣ ከሁለገብ ምጣኔ ሀብታዊና ቴክኖሎጂ ጥገኝነት የሚያወጣን ሳይሆን ወደ ፍጹም ጥገኝነት እያንደረደረን ነው፡፡ ራሳችንን ችለን ለሌላ የመትረፍ ዝንባሌ ከመዳከሙ የተነሳ በማንኛውም ጥረት ውስጥ ማኅበረሰቡ ፍላጎቱን ዛሬ-እዚሁ- አሁን-ለእኔ በሚል ፍልስፍና ተይዟል፡፡ ለተስፋ፣ ለሌሎች፣ ለትውልድ የማሰብና የመሥራት የጤናማ ሰብአዊ አቅል ተዳክሟል፡፡ ይህ በተግባር ዛሬ በሀገራችን ተንሰራፍቶ የሚታየውን ሙስና፣ ዘረኝነት፣ የስነ-ምግባር ብልሽት፣ የፈጠራና የሥራ ባህል መዳከም፣ የማህበረሰብ በእድሜ፣ በሥልጣን፣ በእውቀት አቅም መከባበርና መደማመጥ ተዳክሞ ትውልዱ የዘመናዊ ሚዲያና መልዕክት ተከታይ በመሆነ ማንነቱን ጥሎ ይታያል፡፡ ለዚህ ምስክሩ፡-
1. ሕፃናትና ወጣቶች ከወላጆቻቸውና ከአካባቢ ሽመግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው ይልቅ የዘመናዊ ትምህርት ቤት መምህራንን፣ በመገናኛ ብዙሀን የሚመለከቱትን የሩቁንና ከእሴታቸው ጋር የማይኼደውን ባዕዳን ጀግኖች በአርአያነት የመከተል ዝንባሌ አላቸው፤

2. በየደረጃው ሕዝብ እንዲያስተዳድሩ እንዲመሩ የሚሾሙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሀገራቸው የተለያዩ ባህሎችና እምነቶች ውስጥ የሚገኙ ሁለገብ እውቀቶችና መላዎችን በማጥናትና በማደራጀት ሀገራቸውን ከመምራት ይልቅ ባህር ተሻግረው ከልምድ ለውውጥ ጉብኝት፣ ከሴሚናሮች፣ ከሚያስቀናቸውና ከሚያደንቁት ሀገርና ባዕድ መሪ በሚቃርሙት ከሀገራቸው ማንነት ጋር የማይጣጣም መፍትሔና አሰራር ላይ ጥገኛ ይሆናሉ

3. ተመራማሪዎችና መምህራን የሀገራቸውን ሁለገብ እውቀቶች በመመርመር፣ ከሌሎች ሀገራት ከሚያገኙት ጋር በማቀናጀት ትውልድን ከመቅረጽ ይልቅ ከሌላ የተቀዳላቸውን መልሰው መላልሰው ወደ ተማሪዎች በመገልበጥ፣ ተመራማሪዎችም የባእዳንን ስልትና የመመራመር መንግድ ብቻና ብቻ በመከተል ሀገሪቷን ተከታይ እንጂ የራሷ የሆነ የእውቀት መንገድና ምንጭ እንዳትሆን አድረገዋታል፡፡ መሠረታዊ ምርምር ቆሞ የሌሎችን የምርምር ውጤቶች ከሀገር ጋር የማላመድ (no basic research but adaptive) ብቻ ነው፡፡ለምሳሌ የግብርና ምርምራችን የማላመድ ሙከራ ላይ እንዲያተኩር በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር መመሪያ ሲሰጥ በመገናኛ ብዙሀን አዳምጠናል፡፡
ይህንን የውድቀት አዙሪት ለማስቆምና በመንፈስም በሥጋም ዘለቄታዊነትና ጥቅም ያለው፣ ከጥገኝነት ነፃ የሚያወጣ ኢትዮጵያዊ ጎዳና ለመጀመር ኢትዮጵያዊ የእውቀት፣ የፍልስፍና፣ የዘመናት ታሪካዊ እሴት በዘመናዊ የትምህርት አደረጃጀትና ይዘት ውስጥ ዋጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡
የዚህ ኢትዮጵያዊ እሴት ዋጋ ማግኘት ሊገለጽ የሚችለው ሕፃናትና ወጣቶች የሚማሩት የተደራጀ ሥርዓተ ትምህርት ለሀገራዊ እሴት፣ ልምድ፣ የባህላዊ ትምህርት አቀራረብ፣ ለቤተሰብ ትውፊት አስተላላፊነት እውቅና ተሰጥቶት የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት አካል እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የወለጅ ዜጎችን ሚና መውለድ፣ መጠለያ ማቅረብ፣ መመገብና ማልበስ ብቻ እንዲሆን፤ እውቀት መስጠት፣ ስነ-ልቡና መገንባት፣ ማንነትን መቅረጽ ሙሉ በሙሉ ባባዕዳን እርዳታና ፍልስፍና ለዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት ብቻ እንዲተውና ወላጅነት የሥጋ እንጂ የአእምሮና የመንፈስ እንዳይሆን መከላከል ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዳይቀጥል በዘመናዊ ትምህርት ስም የተዘጋጀ ጥፋት አስመስሎታል፡፡ ይህ የጥፋት መንገድ ያስገኘልን ውጤት ቢኖር፡-
1. በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዘለቄታዊነት የሌለው በሌሎች ሀገራት ኢንዱስተሪ ላይ የተመሠረተ አፈርን የሚበክል ማዳበሪያና ኬሚካል ተጠቅሞ የማምረት ጥገኝነት

2. ጥጥ በመፍተል ልብስ መስራት፣ በሸክላ ሥራ ማብሰያ ማዘጋጀትን፣ ቅልና ቀንድ ተጠቅሞ የመጠጫ ባለቤት መሆንን፤ ከቤተሰብ ተምሮ በወጌሻነት፣ በማዋለድ፣ በዕፅዋት በሽታ መፈወስን፣ በረት መቀጥቀጥን፣ እንስሳት ማከምን ወዘተ በማወራረስ፣ በማዘመንና ወደ ፋብሪካ ማሳደግን ሙሉ በሙሉ በማቆም ፋብሪካውም ጥሬ ዕቃውም፣ የፋብሪካው ጥሬ መለዋወጫውም የባእዳን እንዲሆንና ኢትዮጵያዊያኖች ሙሉ በሙሉ ጥገኛ፣ የራሳቸው የሆነ ምንም የሌላቸው ኦፕሬተሮች (በተነገራቸው ልክ ብቻ የሚሰሩ መሣሪያዎች) ወይንም የተፈጥሮ ሀብተና ጉልበት እየሸጡ ሸማቾች እንዲሆኑ፤

3. የሥርዓተ መንግሥት መሻሻልና መዘመን፣ የማኅበረሰብ አስተዳደር፣ የግጭት አመራርና ማልማት፣ የቤተሰብ አስተዳደርና ዳኝነት ወዘተ ሁሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ማኅበረሰቦች የዳበረ ባህል፣ እምነት፣ ጥበብ እየተቀዳ፣ እየለማና በዘመናዊ ዓለም አቀፍ እይታዎች እየተዳቀለ እንዳያድግ ከሕጻናት እስከ ክፍተኛ የትምህርት ደረጃ ድረስ ያለው እውቀትና ጥበብን ከማሳደግ በተጓዳኝ እሴትና ስነ-ምግባርን በተቃራኒው በመሸርሸር ኢትዮጵያዊ ማንነትን አዳክሟል፣ በወላጅና በልጆች መካከል መለያየትን አስከትሎአል፤ ዘመናዊው ሰው የሚከበርበትና የሀገር አባት የሚናቅበትን ስነ-ልቡና ፈጥሮ ይታያል፡፡
የትውልድ ሥርዓተ ትምህርትን ግብ፣ እሴትና ርዕይ የሚወስነው ማነው? ብሎ ለሚጠይቅ ምላሹ ሴኩላርን እሴትን ሉላዊ ለማድረግና ብዝሀነትን ለመደምሰስ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የባህል ድርጅት መሆኑን ከሕጎቹ፣ ከፍልስፍናዊ እና በየሀገራቱ የትምህት ሥርዓት መዋቅርና ይዘት ላይ ጣልቃ በመግባት በሚያደርገው ጫና መገንዘብ ይቻላል፡፡
ለእድገትና ለሠልጣኔ የተደራጀ (ፎርማል) ትምህርት መማር አስፈላጊና የግድ መሆኑ አያጠያይቅም፤ ይሁን አንጂ ይህ የትምህርት ይዘት የሚወሰነውና በማን እሴት፣ ምን ግብ ለማሳካት፣ በማን ርዕይ መምራት ይገባዋል? የሚለውን ጥያቄ በማያሻማ መንገድ ኢትዮጵያዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡ አሁን ያለው የትምህርት ግብና እሴት በዩኔስኮ ትዕዛዝ የሚመራና ፈጽሞ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከሚመሠርቱ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በጥንቃቄ የጸዱ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በትጋት የሚዋጉ ናቸው፡፡
ጊዜ፣ ሀብት፣ ቦታ፣ መሠረተ-ልማት የሚዘጋጀው፤ መገናኛ ብዙሀን፣ ኪነ-ጥበብና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚያገለግሉት፤ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚቀረጸው በማን እሴት፣ የማንን ርዕይና ግብ ለማሳካት ነው? የሚለውን ጥያቄ በማያጠራጥር መንገድ ኢትዮጵያዊያኖችን ነው ለማለት የሚለው ከውጭ የምንቀዳውን ያላአንዳች ማጣሪያና ግልጽ ፍልስፍና ያለው የመምረጫ መሥፍርት በትውልዱ ላይ ከመጫን ተቆጥበን ጠቃሚውን ከሀገራዊው ጋር አዋሕዶ መሥራት ጊዜው የሚጠይቀው ጥሪ ነው፡፡
በትምህርት ይዘት ቀረፃው ሂደት ውስጥ ሀገራዊ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የልምድ ሊቃውንት ፈጽመው የማይሳተፉበትና በባዕዳንና ዘመናዊ ድግሪ የያዙ ብቻ መሆናቸው የትምህርት ይዘት፣ አቀራረብ፣ የትምርቱን ግብና ርዕይ ባዕድ እንዲሆን አድርጎት ኖሮአል፡፡ ይህ ከማንነት የሚጋጭ አስተምሮ ዘመናዊያን ምሁራንና በየሚፈጥሩአቸው መንግሥታዊ ሥርዓት በሕዝቡ ልቡና ውስጥ ሥር ሰዶ፣ ከባህል፣ ከታሪክና እምነት ማንነት ጋር ተዋዶ ለልማትና ለሰላም በሚገባው ልክ እንዳያገለግል ምክንያት ሲሆን ኖሮአል፡፡
ይህን የስህተት መንገድ ለማቃናት ቁልፍ መግቢያ በሥርዓተ ትምህርት ቀረፃው ለዘመናት ይህችን ሀገር ተሸክመው የኖሩ ባህላዊ፣ መንፈሳዊና አካባቢያዊ እውቀቶችና ብልሀቶችን የሚወክሉ ሊቃውንት ማሳተፍ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በጥበብ፣ በፍልስፍና፣ በባህላዊ የግጭት አፈታት፣ በሕክምና፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በትምህርት አወቃቅርና አሰጣጥ የሚታወቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምሑራን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ምሁራን፣ የገዳ ሥርዓት አዋቂዎች፣ የአፋር የመድ-ዓ ሥርዓት አዋቂዎች፣ የኮንሶ፣ የሌሎች በጠረፋማ አካባቢ የሚኖሩና በጥበብ እውቀታቸው እውቅና ያለገኙ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች በአስቸኳይ ተለይተው ሀሳብ የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
እስከ አሁን ኢትዮጵያዊያን እንደ ዜጎች፣ እንደ ግብር ከፋይ፣ ለዚህ ሀገር ነጻነት ዋጋ እንደሚከፍል ዜጋ በትምህርት ይዘትና አቀራረብ ውስጥ ያለን ሚና ምን ያህል ነው? እሴታችን እንዴት እናስጠብቃለን? ለሚለው ግልጽ የሆነ በሀገሪቱ ሕግ የተገለጠ መመሪያና ፖሊሲ የለንም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ መሪ ይዘቶቹና ውጤቱን ስንገመግም እኛን የማይገልጠን ጠባይና ባህል አንድናዳብር ምክንያት ሆኖአል፡፡ የእነዚህም ኢትዮጵያዊ መሠረት የሌላቸው መገለጫዎች መካከል፡-
1. የተውሶ አመራርና ግራ መጋባት (ማርክሲዝም፣ ሊበራሊዝም፣ ጎሣዊነት፣ መናፍቅነት፣ ክህደት፤ ጦርነት፣ ጥልና መጠላላት፣ ግልብ ርዕዮተ-ዓለማዊ ምሪት ውስጥ መጋጨት፣ ታሪክን ከእውነትና ከመንፈሳዊነት በማጽዳት ለጊዜአዊ ፖለቲካዊ ግብ መጠቀም )፤ በዚህ ብዙ የሰው ልጆች ሕይወት ጠፍቷል፤ ማኅበረሳባዊ ምስቅልቅል ተከትሏል፤ ሀገር በነጻ አውጭና ነጻ ወጭ በሚል በባዕዳን የመገዳደያ መሣሪያና ፍልስፍና ሲናወጥ ኖረዋል

2. ማኅበረሰቡ በማይረዳውና በማያውቀው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ቆሞ — የሚያስበው፣ የሚናገረውንና የሚመኘውን፣ እንዲሁም የሚያደርገውን ሁሉ ከትምህርት ቤትና ከመገናኛ ብዙሀን፣ ከመንግሥት ሕግና ደንብ ብቻ የሚቀዳና የራሱ መልሕቅ የሌለው ተደርጓል፤ በዚህም ምክንያት ያለ መንግሥት መኖር ይችል የነበረው ማኅበረሰብ በፖሊስና ወታደር ጥበቃ ካልሆነ የመጠፋፋት፣ የመዘራረፍና የመጠላላት መግለጫ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ልጆች አፍርቶአል፡፡

3. በሀገሪቷ ከሃይማኖት፣ ከሀገራዊ ልማድ፣ ከተዋረዳዊ የዕውቅት ቅብብሎሽ፣ ከዕድሜና ከክህነት ክብር፣ ከትውፊታዊና ታሪካዊ ማንነት በሚመነጭ የሕሊና ሕግ ጸንቶ የሚኖር ትውልድ እየተደመሰሰ፣ በራስ ወዳድነትና በበላይነት ስነ-ልቡና የታወረ፣ ለሽሚያ የተሰለፈ፣ ዛሬን እንጅ ነገን፣ ሆድን አንጂ ሰብአዊ እሴቶችን የማይገነዘብ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡

4. ትውልዱን የደስታና የጥሩ ኑሮ ትርጉም ሙሉ በሙሉ አካላዊና ስሜታዊ እንጂ መንፈሳዊና ተስፋ ላይ የተመሠረተ መሆኑ እየተዳከመ ሄዶአል፤ በዚህም ደስታን በመደንዘዝና በጫጫታ ውስጥ መፈለግ ያስከተለው ሱሰኝነትና የሥነ-ምግባር መውደቅ፤ በአቋራጭ ደስታንና ምቾትን ለማግኘት ሲባል በሚደረግ ሙከራ ስደት፣ ዘረፋና ሌብነት ተንሰራፍተዋል፡፡ ቅድስና፣ ራስን መግዛት፣ በእምነት መጽናት ኋላቀርነት፣ ስንፍና፣ አለመሠልጠን የሚሰኙበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

ይህን ውድቀት ያስከተለው መደበኛ የትምሀርት ሥርዓት ለመሆኑ በ Federal Democratic Republic of Ethiopia፣ Ministry of Education Curriculum Framework for Ethiopian Education፣(KG – Grade 12)፣ May 2009 በመመልከት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ሰነድ የተመለከተው ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ መሠረቱን ያገኘው ዩኔስኮ ከሚመራትና ኢዩጄኒሰት (የዘረኝነት ሳይንስ) ከሆነው የመጀመሪያው ዳይሬክትር ጁሊያ ሁክስሌይ ነው፡፡ ጁሊያን ሁክስሌይ ቀመር ላይ የተመሠረተው የዩኔስኮ ፍልስፍና ለዓለም ሰላምን ለማምጣትና ዓለምን አስቀድሞ ወደ ሚፈለገውና ወደ ታቀደ ግብ ለማድረስ የሚያስችል የትምህርትና የባህል ማህቀፍን ሴኩላር እና ሉላዊ ማድረግ፤ ሰው የመሆንን ትርጉምም አንዲሁ በዳርዊን ዝግመተ-ለውጣዊ መላምት ላይ እንዲመሠረት፣ የተለያዩ እምነቶችና ማንነቶች ቀስበቀስ አሀዳዊና ሴኩላር እንዲሆኑ ማደርግ ነው፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ዶግማ ያላቸው እንደ ክርስትናና እስልምና ያሉትን፣ ጠንካራ የሃይማት ፍልስፍና ላይ የተመሠረቱ ባህሎችን ከትምህርት ይዘት ውስጥ በማስወገድ ከወላጆች ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይተላለፉ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት
በዚህ መሠረት UNESCOን ለመፍጠር በOxford በ1941 Council for Education in World Citizenship በተባለ የመጀመሪያው በአውሮፓ መምህራን፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የሚሠሩ ሠራተኞች ተሰብስበው የወጠኑት ሀሳብ በ1942 መጨረሻ Allied Ministers of Education (CAME) ደርጅት ፈጠሩ ይህ ወደ ዩኔስኮ በማደግ አሁን ልጆቻችን የሚማሩትን ሥርዓት ትምህርት ለመወሰን የበቃ ጉልበት አገኘ፡፡
የዩኔስኮን ፍልስፍና የቀረፀው ሁክስሌይ እንዲህ ያስባል፡-
በጣም ልዩ በሆነ የዓም ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አብዮት የተፈጠረ የአስተሳሰብ አብዮት አለ፡፡ —- ከአሁን በኋላ ማሰብ ያለብን በለውጥ መንገድ (ስለመለወጥ) ነው፡፡ ይህ ለውጥ የሰው ልጆችን የሕይወት ዘርፍ ሁሉ ትምህርትን፣ መኖርን በእቅድ መምራት ያካተተ መሆን ይገባዋል፡፡ ሰው የግል፣ የጋርዮሽና አጠቃላይ የታቀደ ማኅበረሰብ ቅርፅን ለመፍጠር በአስተሳሰቡም፣ በአደረጃጀቱና በአጠቃላይ በሚኖረው ማኅበራዊ ሕይወት ሁሉ የታሰሰበበትና የታቀደ ዝግመተ ለውጣዊ መሆን ይገባዋል፡፡
አንድ የዓለም ዜግነትን በዚህ ፍልስፍና ለመምራት ዩኔስኮ የየሀገራትን መንግሥታትና ሀብቶቻቸውን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተጽእኖ በመፍጠር ሂደቱን ለማፋጠን ዓለም አቀፍ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥልጣን መሠረት ይሆናል፡፡ የዩኔስኮን ፍልስፍና በሁሉም ዘርፍ ለመደገፍ የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶች ሁሉ ቀጥተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሁክስሌይ ዩኔስኮን መምራት ለሌሎች አስረክቦ ሲለቅ የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ (World Wildlife Fund) እንዲመሠረት፤ ይህ ሰው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሞራላዊ ሕብረት (International Humanist and Ethical Union) መሥራች አባል ሆነ፡፡ በእርሱና የዓለም አቀፍ ተቋማት ፍልስፍና ቀማሪዎች አመለካከት መላው የሰው ልጅ አንድ አይነት ከዝግመተ ለውጣዊ አስተሳብ ጋር የሚስማማ አንድ አይነት እሴት ባለቤት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ደኅንነትን መጠበቅ በሚል ሽፋን የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጡራ በታች ወይንም እኩል የማስመሰል አስተሳሰብ በዓለም ማስፈን ግባቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ የዩኔስኮ መሠረታዊ ፍልስፍና የቁሳዊና መንፈሳዊ ዓለም ዝግመተ ለውጣዊነት ነው (the evolution of both matter and spirit)፡፡ ዩኔስኮ የሚመራው በዓለም አቀፋዊ ዝግመተ ለውጣዊ ሳይንሳዊ ሰብአዊነት ነው (ሁክስሌይ አንዲህ ይላል፡-the general philosophy of Unesco should, it seems, be a scientific world humanism, global in extent and evolutionary in background)፡፡ የዚህ ድርጅት ፈጣሪዎቸና መሪዎች የኢዩጄኒስት ማህቀፈ-እሳቤ ያለቸው ናቸው፡፡ ኢዩጄኒዘም ዘረኝነትን ሳይንሳዊ የማድረግ ጥረት ነው፤ ግቡም (1) ምርጥ የሰው ዘር ማባዛት፣ (2) ሰውን ለመቆጣጠር የሰውን ምግብ ምንጭ መቆጣጠር፣(3) ከተመረጡት ዝርያዎች ውጭ የሚገኙ ሰዎች የማይባዙበተን የሕክምና፣ የትምህርትና የፖሊሲ ሥርዓት በመዘርጋት መገደብ፤ (4) የሀገር የሰብልና የእንስሳት ዝርያን ማቆየት፣ ሀገር በቀል የምርምርና ራስን የመቻል መንገዶችን ማዳከም፣(5) ብዙሀኑን ዜጎች አምራች መሣሪያና እውር ፈጂዎች (blind consumers) በማድረቅ ጥቂቶችን ሊህቃን ብቻ መሪና አሳቢ ማድረግ፤ (6) የህን ሁሉ ዓላማ ለማሳካት በዘመናዊ የተደራጀ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ያሉ አራት ምሰሶዎች (ሥነ-ልቡናዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ እና ፍልስፍናዊ መሠረቶች) ሙሉ በሙሉ ሴኩላር በመሆን የዩኔስኮን ፍላጎት እንዲያሟላ መቆጣጠር፡-
አራቱም የሥርዓተ ትምህርት ምሰሶዎች ትርጉም የሚያገኙት የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጣዊ ሂደት ከእንስሳ በረጅም ዘመን ውስጥ አሁን ወደ ሚገኝበት የአስተሳሰብ ደረጃ ደረሰ፤ ይህ ሂደት ለወደፊትም ይቀጥላል፤ ሂደቱን በታቀደና በአዋቂዎችና መሪዎች ውሳኔ አስቀድሞ ወደ ተወሰነ ግብ መምራት ያስፈልጋል ከሚል አጠቃላይ ማህቀፈ-እሳቤ ይነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ነባር፣ ሀገራዊ፣ መንፈሳዊ መሠረት የነበራቸው አስተሳሰቦች መወገድ እንደሚገባቸው አጠንክሮ ይሠራል፡፡
በሥርዓተ-ትምህርት መዋቅርና ይዘት ውስጥ ሀገራዊ የየሀገራት እምነት፣ ትውፊት፣ ባህል፣ ፍልስፍ፣ እውቀት፣ ስነ-ልቡና፣ ማኅበራዊ እሴቶችና ርዕዮት ሚና የሚኖረው ከሆነ ዩኔስኮ እንዲፈጠር ለሚያልመው ዓለም አቀፋዊ ዝግመተ ለውጣዊ ሳይንሳዊ ሰብአዊነት እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገራዊ እውቀትና እሳቤ በጥንቃቄ ከዘመናዊ ትምህርት ይዘትና አቀራርብ ፈጽሞ ማስወገድ የግድ ነው፡፡ ከትምህርት ይዘት በተጨማሪ የአንድን ሕዝብ ማንነት የሚያስተላልፉ መስመሮች
1. በቤተሰብ ደረጃ በወላጆችና በልጆች መካከል የሚደረግ መስተጋብር
2. መንፈሳዊና ማኅበራዊ በዓላት
3. ታሪካዊ የሥነ-ጥበብ፣ የሥነ-መንግሥት፣ የሥነ-ቅርጽ፣ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶችና ሀብታት
4. የአምልኮ መገለጫ፣ የቀኖናዊ ሕይወት ማስጠበቂያ መንፈሳዊ ሕግጋቶችና ድርጊቶች
5. ማኅበራዊ ሕጎችና ደንቦች — በጥምረት ተጋምደውና ተሰድረው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

መፍትሔ ሀሳብ፡-
1. የትምህርት ፍልስፍናውን ከሃይማኖትና ከባህል፣ ከታሪክ ፈልፍሎ የራሳችንን መልሰን መቅረጽ፤ ከዘመናዊው የባዕዳን ፍልስፍና ጋር የሚዛመድበትን ፊትና ጎን አጥንቶ በራስ መመራት
2. ሀገራዊ ሊቃንት በትምህርት ሥርዓትና አቀራረብ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲኖራቸውና እንዲሳተፉ ማድረግ
3. የኢትዮጵያን እውቀቶች በሁሉም ዩነቭረሲቲዎች የሚቆጥር፣ የሚመዘገብ፣ የሚተነትን፣ የሚመረምርና የሚያለማ ዘርፍ መመሥረት
4. መምህራንና በዘመናዊና ባህላዊ እውቀት ማበልጸግ
5. የእድገት፣ ሥልጣኔና የልማት ፍልስፍናን ከሴኩላር ሰብአዊያን መንገድ አውጥቶ ኢትዮጵያዊ ትርጉም ላይ ማቆምና ትምህርትን ከዚያ አንጻር መዘርጋት
6. ሙያ እና ቴክኒክ የሀገረ ስብ ሙያዎችን እንዲያሳድግ በዩኒቭሲቲዎች ቆጠራና ምርምር፣ ማሻሻልና ከውጭ ጋር ማዳቀል እንዲሠሩ ማድረግ፤ ሙሉ በሙሉ በጭፍን የመገልበጥና የራስን ሙሉ በሙሉ ወደ ማጥፋት የሚደረገውን ሩጫ ማስቆም
7. የትምህርት ፖሊሲው ከመከተል ውደ መወዳደርና መቅድም የሚልም ሆኖ አንዲቀረጽ በማድረግ ፖሊሲውን የሚተረጉምሰተራትጂና ስልቶችን መተግበር
8. በዓለም አቀፍ እርፈዳታ ምሪት ላለፉት ከ40 ዓመታት በላይ የተካሄደውን ትምህርት በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን ጎን ለጎን በኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ፣ በኢትዮጵያዊጣን ሊቃውንት፣ በኢትዮጵያዊያን ሀብት ብቻ በውጭ ተጽእኖ የሚጠበቅ የጥምህርት ሥርዓት መዘርጋት

ከላይ የተገለጹትን ምክረ-ሀሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት የጀመረው ፍኖተ ካርታ ሀገራዊ ትምህርት ለማልማት ፍላጎት የሚሳይ የፖሊሲ ዓረፍተ ነገርና የ15 ዓመት ግቦችን እንዲያመለክት ተደርጎ እንዲካተት ማድረግ::

Share.

About Author

Leave A Reply