ኢትዮጵያ፡ ያለ ባሕር በር የባሕር ኃይል ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጎልማሳው የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ባልደረባ ትዝታ፣ ቁጭት እና ናፍቆቱን የሚወጣው በሙዚቃ ነው፡፡ የኪቦርዱን ቁልፍ እየጠቃቀሰ የሚያንጎራጉራቸውን ሙዚቃዎች ሌሎችም ይጠለሉባቸው ዘንድ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይጭናቸዋል፡፡

ከእነዚያ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ‹መልህቅ አርማዬ› የተሰኘው በጌታቸው በርሄ ተጽፎ በባህር ሃይል የሙዚቃ ቡድን የተዘጋጀው ለስላሳ መዝሙር ነው፡፡

ፒቲ ኦፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ ስለ ድሮ ባህር ሃይል ሲነሳ ግን የሙዚቃውን ተቃራኒ በእልህና በቁጭት ይሞላል ፣‹‹የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ከዓለም ተደናቂ ሃይሎች አንዱ የነበረ፣ ሰባቱንም ውቅያኖሶች ያቋረጠ ትልቅ የባህር ሃይል ነበር፡፡ ከወደብ ጠባቂ(ኮስት ጋርድ) ጀምሮ እስከ ትልቁ የጦር ሚሳኤል ድረስ ታጥቆ ይንቀሳቀስ የነበረ ሃይል ነው፣›› ብሎ እማኝነቱን ይሰጣል፡፡

ፒቲ ኦፊሰር ከሙዚቃ በተጨማሪ ባሰናዳው ድረ-ገፅ ሰርክ የሚዘክረው የባህር ሃይል ዛሬ የለም፡፡ ጃንሆይ በ1947 አቋቁመውት በደርግ ዘመን እስከ 3ሺ ጦር ድረስ የነበረው ሃይል በ1983 ምጽዋ በኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ከተያዘበት ጀምሮ ህልውናው ይስለመለም ገባ፡፡

ነባር መርከቦቹ ከየመን እና ዙሪያው ተሰብስበው፣ገሚሶቹ የጂቡቲን ዕዳ ለመክፈል ዋሉ፣ ገሚሶቹ የኤርትራ አዲስ መንግስትና ኢትዮጵያ ተከፋፈሏቸው፡፡ በ1988 ዛሬ የምስራቅ አፍሪቃ ተጠባባቂ ጦር ቅጥር ግቢ የሆነው የአዲስ አበባ ቢሮው ሲዘጋ የባህር በር ታሪክ የተደመደመ መሰለ፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ከሰሞኑ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በነበራቸው ምክክር የኢትዮጵያን ባህር ላይ የማደራጀት አላማ እንዳላቸው ስለማሳወቃቸው ተዘገበ፡፡

ዘገባውን ተከትሎ ተስፋ እና ጥያቄ ተከተለ፡፡ ከጠያቂዎቹ መካከል የቀድሞ የባህር ሃይል ባልደረባ ፒቲ ኦፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ ይገኝበታል፡፡

‹‹ካለ ባህር በር እና ባህር እንዴት ነው የባህር ሃይል የሚቋቋመው? ይሄ በእውነቱ ፌዝ ነው፡፡የባህር ሃይል ውስጥ የነበረ ሰው ይቅርና ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚቀበለው አይሆንም ፡፡›› ሲል ያሳስባል፡፡

ምንጭ፤ ቢቢሲ

Share.

About Author

Leave A Reply