ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ድርድር ጀምራለች

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ኢትዮጵያ የቀጣናውን አገራት በኤሌክትሪክ ኃይል የማስተሳሰር ውጥኗን ለማሳካትና የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቷን ለማጠናከር ለታንዛኒያ ኃይል ለመሸጥ ድርድር መጀመሯ ተገለፀ፡፡ አገሪቱ ወደ ወጭ በምትልከው የኤሌክትሪክ ኃይል ላይም የታሪፍ ጭማሪ ሊደረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ቀደም ሲል ለሱዳንና ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጡን አስታውሰው፤ ወደ ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመላክም የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈርሞ 2000 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው መስመር በመዘርጋቱ በዚሁ ኤሌክትሪክ መስመር የሚተላለፍ ለታንዛኒያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ድርድር ተጀምሯል፡፡

ሥራ አስፈፃሚዋ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የምትሸጠው ኃይል በኬንያ ኔት ዎርክ ውስጥ ስለሚያልፍ ታንዛኒያ ክፍያ በመጠየቋ በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ከምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ኬንያ የምትጠይቀው ክፍያ ጫና እንደሚፈጥርባት በመግለጿ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ውይይት በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ ይገኝለታል፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ውጥኗ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ኢንጂነር አዜብ፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትብብሯን አቋርጣ ከነበረው ከኤርትራ ጋር በግልፅ የተጀመረ ሥራ ባይኖርም የመተሳሰር ውጥን እንደሚኖርም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ኢንጂነር አዜብ እንዳሉት፤ ወደ ውጭ በሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ከጂቡቲ እና ሱዳን ጋር በተገባው ውል መሰረት ላለፉት አምስት ዓመታት ኃይል ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፤ ታሪፍ መከለስም በውሉ የተካተተ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከሁለቱም አገራት ጋር ታሪፉን የመከለስ ሥራ ተጀምሯል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት ለሱዳን እና ለጂቡቲ ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ኃይል 82 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ ወደ ኬንያ ኃይል ለመሸጥም 2000 ሜጋ ዋት መሸከም የሚችል የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋቱ ይታወቃል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply