ኢትዮጵያ ሶስት ጋዜጣ ብቻ ቀሯት። እነሱም የመዘጋት አደጋ አንዣቦባቸዋል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢትዮጵያ ፕሬስ እንደ አጀማመሩ ቢሆን ዛሬ የት በደረሰ ነበር ብለው ይቆጫሉ – የነፃ ፕሬስ አቀንቃኞች፡፡ በሁለት አስርት ዓመታት ጉዞው ፕሬሱ ከማበብ ይልቅ ደብዝዟል፡፡ ከ100 በላይ የነበሩት የግል ፕሬስ ውጤቶች፤ ዛሬ በጣት የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ አሁን በአገሪቱ ውስጥ 3 የአማርኛ ጋዜጦች ብቻ ቀርተዋል፡፡ ያሉትም ቢሆኑ የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጦባቸው፣ ህልውናቸው አደጋ ላይ ነው ተብሏል፡፡

በየጊዜው የሚንረው የህትመት ዋጋ፣ የማተሚያ ቤት ችግር፣ የስርጭት ሰንሰለቶች አለመዘመን እንዲሁም የማስታወቂያ አቅርቦት ችግር … የግል ፕሬሱን ዕድገት አቀጭጮታል ይላሉ – ጥናቶች፡፡

ባለፈው ሀሙስ በአዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል “ሚዲያ ለፍትህና የህግ የበላይነት መረጋገጥ” በሚል ርዕስ በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ በቀረቡ ጥናቶች እንደተመለከተው፤ የግል ፕሬሱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡

በግል ፕሬሱ ዙሪያ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የ“ሰንደቅ ጋዜጣ” ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ፤ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ያለውን የግል ፕሬስ ጉዞ ቃኝተዋል፡፡

የደርግ አገዛዝ በተለወጠ ማግስት በተለይ በ1986 ዓ.ም የግል የህትመት ውጤቶች ብዛት አንድ መቶ አስራ ሰባት (117) እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፍሬው፤ ባለፉት 24 ዓመታት በገጠሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች በአሁኑ ወቅት ብዛታቸው ወደ 24 ማሽቆልቆሉን ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ በመደበኛ ህትመት ውስጥ የሌሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ታትመው የሚሰራጩ የአማርኛ ጋዜጦች፡- “ሪፖርተር”፣ “አዲስ አድማስ”፣ እና “ሰንደቅ” ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ጥናት አቅራቢው፤ እነዚህም ቢሆኑ ህልውናቸው አደጋ ላይ ነው ብለዋል፡፡

ከ97 ዓ.ም በፊት በሀገሪቱ የሚታተሙ የግል ፕሬሶች የስርጭት መጠን እስከ 120 ሺህ ይደርስ እንደነበር ያስታወሱት አጥኚው፤ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛው የስርጭት መጠን በሳምንት ቢበዛ 12 ሺህ ቢሆን ነው ብለዋል፡፡ ይህም ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ ለአዲስ አበባ ህዝብ፣ ለአንድ በመቶ ያህሉ እንኳ የሚዳረስ አይደለም ተብሏል፡፡ በአንፃሩ በጎረቤታችን ኬንያ “ዴይሊ ኔሽን” የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ፤ በየቀኑ 100ሺ ቅጂዎች እንደሚታተም ተገልጿል፡፡

ለሀገሪቱ የግል ፕሬስ ዕድገት መቀጨጭ በመንስኤነት ከሚጠቀሱት መካከል፡- ለፕሬስ ስራዎች ምቹ ምህዳር አለመኖር፣ የመንግስት ድጋፍ ማነስ፣ የህትመት ዋጋ ንረት፣ በቂ ማስታወቂያ አለማግኘት እንዲሁም የአሳታሚዎች የፋይናንስ አቅም ውስንነትና የስርጭት ሰንሰለቱ አለመዘመን እንደሚገኙበት በጥናቱ ተገልጿል፡፡

የጋዜጦች የህትመት ስርጭት በአብዛኛው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የታጠረ መሆንና የንባብ ባህል አለመዳበር፣ የስርጭት መጠኑ ከመጨመር ይልቅ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል ብለዋል – ጥናት አቅራቢው፡፡

የወረቀትና የህትመት ዋጋ እየናረ መሄድ፣ ለፕሬሱ ህልውና የዘወትር ስጋት ነው ያሉት አቶ ፍሬው፤ አንድ ነጠላ ጋዜጣ ለማሳተም 30 ብር እንደሚጠይቅና የሚሸጥበት ዋጋ 10 ብር መሆኑን በመጠቆም፣ በቂ ማስታወቂያ ሳይኖር ጋዜጣ አሳትሞ መሸጥ፣ ገንዘብን ሜዳ ላይ እንደመበተን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ያሉት ጥቂት ፕሬሶች የፋይናንስ አቅማቸው በየጊዜው እየተዳከመ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

መንግስት ለግሉ ፕሬስ ትኩረት ነፍጎት መቆየቱን የገለፁት አቶ ፍሬው፤ ከመንግሥት ተቋማት መረጃ በወቅቱ የማግኘት ችግር፣ ለግል ፕሬሱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበትም ያስረዳሉ፡፡

በሃገሪቱ ብቸኛ የሆነውና በመንግስት ልማት ድርጅትነት የተመዘገበው ማተሚያ ቤት፤ በየጊዜው ማሽኖቹ የሚበላሹ በመሆናቸው የተነሳ፣ ጋዜጦች በቀናቸው የማይወጡበት ጊዜ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ሲሆን ይሄ ደግሞ አንባቢያቸውን ከማሳጣቱም በተጨማሪ ለተደራራቢ ኪሳራ እየዳረጋቸው ነው ብለዋል – አቶ ፍሬው፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን ህዝባዊ ተቃውሞና አመፅ ተከትሎ መንግስት በወሰደው የፖለቲካ ማሻሻያዎች፤ በቅርቡ የተወሰኑ ጋዜጠኞች ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በስደት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችም ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲሰሩ በጠ/ሚኒስትር አብይ የቀረበው ጥሪ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የ“ሰንደቅ” ዋና አዘጋጅ አልሸሸጉም፡፡

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጂ በበኩሉ፤ “ጋዜጠኞችን ከእስር መልቀቅ ብቻውን ለፕሬስ ነፃነት ዋስትና አይሆንም፤ የዲሞክራሲ ማሻሻያዎች ተደርገው ፕሬሱ ያለገደብ የሚሰራበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል” ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማርኛ ቋንቋ ከሚታተሙት ሦስት ጋዜጦች በተጨማሪ “ካፒታል”፣ “ፎርቹን” እና “ሪፖርተር” የተሰኙ እንግሊዝኛ ጋዜጦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥናት ያቀረቡት የ“ድሬቲዩብ” ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ነገሱ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 4.7 ሚሊዮን ያህል የፌስ ቡክ ተጠቃሚ መኖሩን የገለፁት አቶ ቢኒያም፤ በማህራዊ ሚዲያ የሚለቀቅ አንድ መረጃ በአማካይ በቀን 2 ሚሊዮን ሰዎች ይመለከቱታል ብለዋል – ይህም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ካላቸው ተደራሽነት የማይተናነስ አሃዝ መሆኑን በመጠቆም፡፡

ከፌስ ቡክ ውጭ በኢትዮጵያ ሰፊ ተጠቃሚ ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች፡- ዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ቫይበር፣ ቴሌግራም፣ ቲውተር እና ዋትስ አፕ 15 ሚሊዮን ተጠቃሚ እንዳላቸው ገልዋል፡፡

“የሃገሪቱ መሪዎችም ፌስ ቡክን ከህዝቡ ጋር ለመገናኘት እየተጠቀሙበት ነው” ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ “የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሶሻል ሚዲያው ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፤ ፕሬሶች ግን ተሳትፎአቸው ያነሰ ነው” ብለዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

Share.

About Author

Leave A Reply