ኢትዮጵያ ከተደቀኑባት አደጋዎቹ አንዱ “መንጠራራት” ይመስለኛል። – መሳይ መኮንን

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰማይን በእጃችን ለመንካት የሚከጅለን፡ ትንሽ ጭብጨባ ስናገኝ የንግስና አክሊል ለራሳችን ደፍተን የሀገር ዋርካ ለመገንደስ የምንፍጨረጨር በዝተናል። ልካችንን አናውቅም። አቅማችንን የት ድረስ እንደሆነ አልተገለጠልንም። እንጠራራለን። የማንደርስበትን ለመንካት እጃችንን እንወጥራለን።

አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው። ድምፃዊ መሀሙድም እንዳለው ታላቅ ችሎታም ነው። አሻሮ ጨብጠን ቆሎ የምንደፋ ከሆነ ከንቱነት ነው። በትንሽ ስራ እንደተራራ ተቆልለንና ተኮፍሰን ትልልቆቹን ለመዝለፍና ለመዘርጠጥ የምንነሳ “የመንጠራራት” በሽታ ተጠቂዎች አወዳደቃችን አጉልና በውርደት የታጀበ ነው። ትንሽ ጭብጨባ የአረቄ ስካር ናት። ልቦና ትጋርዳለች። አለመጥን ታንጠራራለች። ወዳጃችን ገጣሚ Nuredin Issa በጥቂት ቃላት ግዙፍ መልዕክት አስተላልፏል።

አልሆንህ ካለህ መተለቅና መግዘፍ

ከትልልቆቹ መሃል አንዱን መርጠህ ዝለፍ

የዘመኑ የብሄር አቀንቃኞች አቋራጭ የእውቅና መንገድ መንጠራራት ነው። ትልልቆችን መዝለፍ ነው። አቅምን ሳያውቁ አደባባይ ወጥቶ የሀገር ዋርካን፡ የትውልድ አድባርን ለመንካት እጅን መዘርጋት ነው። ልጅ ሆኖ ለእናት ምጥ የሚያስተምር መብዛቱ የጤና አይደለም። ከሌሎች ኢትዮጵያ ላይ ከተደቀኑ ወቅታዊ አደጋዎች ባልተናነሰ “መንጠራራትን” ልንዋጋ ይገባል።

በመዝለፍ የሚሸመት እውቅና የለም። ትልልቆችን በማንጓጠጥ ትልቅነት አይገኝም። አቅማችንን እንወቅ። በልካችን እንራመድ። መንጠራራት ለማንም አይጠቅምም። የዛሬዎቹ ትልልቆች ትልቅ ቦታ የደረሱት ከእነሱ በፊት የነበሩትን ትልልቆች አክብረው፡ ተገቢውን ቦታ ሰጥተው ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply